Saturday, 16 January 2016 10:27

1.6 ቢሊዮን ዶላር - ሬከርድ የሰበረ ሎተሪ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

               ታላቁ እጣ ሐሙስ ማታ ወጥቷል።
                ከ33 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ነው።
                ግማሹን መንግስት በታክስ ቆርጦ ይወስዳል።
                በሎተሪው የማሸነፍ እድል በጣም ትንሽ ነው።
                    300 ጊዜ በመብረቅ የመመታት አደጋ ይበልጣል።
    ከሳምንት ሳምንት የሽልማቱ መጠን እየጨመረ፣ ብዙ ሲወራለት የሰነበተው ታላቁ የአሜሪካ ሎተሪ፣ የ1.6 ቢሊዮን እጣ በማውጣት ሐሙስ ማታ እልባት አግኝቷል።
የሎተሪው ሽልማት ከሦስት ሳምንት በፊት ከ$250 ሚሊዮን በታች ነበር። እጣው ወጣ። ያሸነፈ ሰው አልነበረም። የእጣው ቁጥር ሲታይ፣ ያልተሸጠ ቲኬት ነው። ግን፣ በዚያው ጭጭ ብሎ አይቀርም። በጥቂት ቀናት ውስጥ፣ እጣው እንደገና እንዲወጣ ይደረጋል። እስከዚያው፣ የትኬት ሽያጩ ይቀጥላል - የእጣ ማውጫ ቀን (ሐሙስና ቅዳሜ) ድረስ።
ቀኑ ደርሶ፣ የሎተሪው አንደኛ እጣ ወጣ። ሽልማቱ ወደ 300 ሚሊዮን አድጓል።  ማን አሸንፎ ይሆን? እንደገና አሸናፊ የለም ተባለ። እንዲህ፣ ከሐሙስ ወደ ቅዳሜ፣ ከዚያም ወደ ሃሙስ እየተሸጋገረ፣ የትኬት ሽያጩ እየተስፋፋ፣ ሽልማቱም እያደገ ቀጠለ። ወደ 350 ሚሊዮን ዶላር፣ ወደ 450 ሚሊዮን ዶላር... ብዙም ሳይቆይ ግማሽ ቢሊዮን ደረሰ። ከዚያማ፣ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው፤ ከቢሊዮን ዶላር በላይ ለመሄድ የደረሰው - ባለፈው ቅዳሜ።
ትኬት የቆረጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በጉጉት ቢጠብቁም። በቅዳሜውም እጣ፣ አሸናፊ አልነበረም። ያው፣ ሐሙስን መጠበቅ ነው። ሳይሸጡ የቀሩ ትኬቶች፣ እንደ ጉድ ሲቸበቸቡ... ትናንት በእጣ ማውጫው እለት፣ ሽልማቱ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ደረሰ። እጣው ሲወጣም፣ አሸናፊው ቁጥር ታወቀ።

ሎተሪ ማሸነፍና በመብረቅ መመታት
ቲኬት የገዛ ሰው፣ የአንደኛ እጣ አሸናፊ የመሆን እድሉ ምን ያህል ነው? እጅግ በጣም ቅንጣት እድል እንደሆነ ለማሳየት፣ በታላቁ ሎተሪ አሸናፊ የመሆን አጋጣሚን፣ በመብረቅ ከመመታት አጋጣሚ ጋር አነፃፅሮታል - ኤንቢሲ።
እጣው በየእለቱ ቢወጣ እንኳ፣... እርስዎም ሳያዛንፉ በየእለቱ ትኬት ቢገዙ እንኳ፣... በ800ሺ ዓመታት ውስጥ፣ አንዴ ብቻ አሸናፊ ይሆናሉ። በእነዚሁ አመታት ውስጥ ግን፣ 300 ጊዜ በመብረቅ የመመታት አደጋ ይደርስብዎታል።
ሽልማቱም ተቀናሽና ተቆራጭ ይበዛበታል
የ1.5 ቢሊዮን ዶላሩ እጣ ቢያሸንፉ፣ ገንዘቡ ሙሉ ለሙሉ ወደ ባንክ ሂሳብዎ ይተላለፋል ማለት አይደለም።
አንደኛ ነገር፤ ሽልማቱን የሚወስዱት፣ ደረጃ በደረጃ በሰላሳ ዓመታት ነው (በአማካይ፣ በየአመቱ 50 ሚሊዮን ዶላር)።
“ትዕግስት የለኝም፤ አንዴ ሽልማቴን አፈፍ አድርጌ ልውሰድ” የሚሉ ከሆነም ይችላሉ። ነገር ግን፤ 900 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው የሚደርስዎት።
በእርግጥ፣ ከዚሁም ውስጥ መንግስት የተለያዩ አይነቶ ታክሶችን ይቆርጣል። ቢያንስ ቢያንስ 400 ሚሊዮን ዶላር ያህል ይወስዳል።
ቢሆንም፣ 500 ሚሊዮን ያህሉ የእርስዎ ይሆናል። ‘ኢንቨስት’ ቢያደርጉትና ቢሰሩበት... ይህም ባይሆን፣ እንዲሁ ‘ያለ ሃሳብ’፣ ባንክ ቢያስቀምጡት እንኳ፣ በየአመቱ፣ 20 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ያስገኛል። ‘መታደል ነው!’ ያሰኛል።
ግን፣ በርካታ የሎተሪ ባለእድለኞች፣ ያን ያህል ‘እድለኞች’ አይደሉም ይላል ትናንት የወጣው የዩኤስ ቱዴ ዘገባ። አንዳንዶቹ፣ ድንገት እጃቸው የገባው ገንዘብ፣ መጥፊያቸው ይሆናል። እንደ ዘበት የተገኘን ገንዘብ፣ እንደ ዘበት እየበተኑ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባዶ እጃቸውን ይቀራሉ። በሶስት ሺ የሎተሪ እድለኞች ላይ የተደረገው ጥናትም፣ የሎተሪ ገንዘብ በሰዎች ኑሮ ላይ ብዙም ለውጥ እንደማያመጣ ያረጋግጣል ብሏል ዩኤስቱዴ። አስር የሎተሪ እድለኞችና ሌሎች አስር ሰዎች... ከጥቂት ዓመታት በኋላ የሚኖራቸውን ኑሮ ብታነፃፅሩ፤ ከሁለቱም ወገን፣ ስኬታማ የሚሆኑ ይኖራሉ፤ ከሁለቱም ወገን ችግረኛ የሚሆኑ ይኖራሉ።    

Read 2584 times