Saturday, 02 January 2016 11:35

የቻይናው ኩባንያ በኦጋዴን 2 የተፈጥሮ ጋዝ ጉድጓዶችን ቁፋሮ አጠናቀቀ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

በዚህ አመት ማምረት እንደሚጀመር ይጠበቃል
     ፖሊ ጂሲኤል ፔትሮሊየም ግሩፕ የተባለው የቻይና የነዳጅ አምራች ኩባንያ በኦጋዴን አካባቢ የሚገኙ ሁለት የነዳጅ ጉድጓዶችን የቁፋሮ ስራ ማጠናቀቁንና በቅርቡም የጉድጓዶቹን የተፈጥሮ ጋዝ ይዞታ መጠን ይፋ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ ትናንት ዘገበ፡፡
ኩባንያው የጉድጓዶቹን የተፈጥሮ ጋዝ ይዞታ መጠን የማጥናት ስራ መጀመሩንና ውጤቱንም በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ የገለጹት የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ዋጋሪ ፉሪ፣ በዚህ አመት የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ልንጀምር እንችላለን ብለዋል ለሮይተርስ፡፡
እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ የተፈጥሮ ጋዝ እንዳላቸው በጥናት ከተረጋገጠውና በካሉብ እና ሂላላ አካባቢዎች ከሚገኙት ሁለቱ ጉድጓዶች፣ 4.7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝና 13.6 ሚሊዮን በርሜል ጋዝነት ያላቸው ተያያዥ ፈሳሾች ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ኩባንያው በ4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አምስት ጉድጓዶችን የመቆፈር እቅድ እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፣ ፕሮጀክቱ አካባቢውን ከማልማት በተጨማሪ፣ በጅቡቲ የፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ መገንባትንና ከኦጋዴን እስከ ጅቡቲ የሚዘልቅ የፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ መስመር መዘርጋትን ያካትታል ብሏል፡፡
ኩባንያው የፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ የማምረት ስራውን እስከ 2018 መጨረሻ የመጀመር እቅድ እንዳለውና በአመት 3 ሚሊዮን ቶን በማምረት ጀምሮ፣ በሂደት አመታዊ የምርት መጠኑን ወደ 10 ሚሊዮን ዶላር የማሳደግ ዕቅድ መያዙን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 4042 times