Tuesday, 29 December 2015 07:28

“ሙዳይ በጎ አድራጎት” በስጋት ላይ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

“ሰኔ ሲመጣ ተረጂዎቹን እበትናቸዋለሁ?”

    ያብሥራ የዘጠኝ ዓመት ህፃን ናት፡፡ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ከመጣች አንድ ዓመቷ ነው፡፡ ያብሥራ ስትወለድ ከአንገት በታች አካሏ እስከ እግሯ ድረስ አይንቀሳቀስም፡፡ የእግሯ ጣቶቿ ብቻ ይንቀሳቀሳሉ። በእግር ጣቶቿ ሥዕል ትሰልባቸዋለች፡፡ በጥርሶቿ ትጽፋለች፡፡ የጥርስ ጽሑፏ ታዲያ በጣም ያምራል፡፡
የሱነህ አሥራት በዚህ ወር 7ኛ ዓመቱን ያዘ፡፡ የሱነህ ሲወለድ ጀምሮ ዓይኖቹ አያዩም፣ አይናገርም አይንቀሳቀስም፡፡ ወላጆቹ በልጃቸው ሁኔታ ከመገረም በስተቀር ህክምናም ሆነ እንክብካቤ አላደረጉለትም፡፡ ሲርበው ብቻ በጡጦ ወተት አድርገው ይሰጡታል፡፡
የሕፃኑን ሁኔታው የምታውቅ የጎረቤት ሴት “እንዲህ ዓይነት ህፃን አለ፤ ትረጂዋለሽ ይምጣ?” በማለት ወ/ሮ ሙዳይን ጠየቀቻት፡፡ ወ/ሮ ሙዳይም፤ ወላጆቹ ከፈቀዱ እረዳዋለሁ አለቻት፡፡ ሴትየዋም የተባለችውን ለእሱነህ ወላጆች ነገረች፡፡ ወላጆቹ ፈቃደኞች ነን በማለት ፈርመው ልጃቸውን ለወ/ሮ ሙዳይ አስረከቧት፡፡
የሱነህ ወደ ሙዳይ በጎ አድራጎ ሲመጣ ሁለት ዓመቱ ነበር፡፡ እንክብካቤና ሕክምና በማግኘቱ አሁን ይንቀሳቀሳል፡፡ በየጊዜው ፊዚዮ ቴራፒ ስለሚደረግለት አሁን በድጋፍ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ ሐኪም ቤት ተወስዶ ሲመረመር፣ ሐኪሞቹ “ዓይኑ ንፁህ ነው ምንም አልሆነም። የማያየው በጭንቅላቱ ውስጥ ያለው ውሃ ስለተጫነው ነው፡፡ አሁን ኦፕሬሽን ማድረግ አይቻልም። 10 ዓመት ሊሞላው ኦፕሬሽን ይደረጋል። አሁን የምንሰጠውን ኪኒን እየወሰደ ይቆይ” እንዳሏት ወደ ማዕከሉ ከመጣ ጀምሮ ሞግዚቱ የሆነችው ወጣት ተናግራለች፡፡
ሞግዚቷ፣ የሱነህ አሁን ብዙ ለውጥ አለው፡፡ ድምፅ መለየት ጀምሯል፡፡ የሚያውቀው ድምፅ ሲሰማ ይፈነድቃል፡፡ የማያውቀው ከሆነ ድምፁን ወደሰማበት አቅጣጫ ጆሮውን ይቀሰራል፡፡ የሚወደውንና የማይፈልገውን ምግብ ለይቷል፡፡ የማይወደውን ምግብ ካበላሁት ያለቅሳል፣ ያኮርፋል፡፡ ሙዚቃ ካልሰማ በስተቀር ኩርፊያውን አይተውም፡፡ ብርሃንና ጨለማም እየለየ ነው፡፡ ውጭ ሳወጣው ዓይኑን ይጨፍናል፡፡ … ብላለች ሞግዚቷ፡፡
ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ፊት - ለፊት ገባ ብሎ በተከራየው 1000 ካ.ሜ ግቢ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ግቢው፣ ለሚያከናውነው የበጎ አድራጎት ሥራ ስለጠበበው እዚው አካባቢ ሌላ ግቢ ተከራይቶ እየሰራ ነው፡፡ ለሁለቱ ግቢ በወር 60 ሺህ ብር እየከፈለ ነው አገልግሎቱን የሚሰጠው፡፡ ሙዳይ በጎ አድራጎት ከፍተኛ ጭንቀትና ስጋት ውስጥ ነው። የግቢው ባለቤቶች ምንም ሳያሳውቋቸው ቦታውን በላያቸው ላይ ሸጠዋል፡፡ ገዢው ቦታውን ሊረከብ ሲመጣ ባየው ነገር በጣም ደነገጠ፡፡ ዕቅዱ በቦታው ነዳጅ ማደያ ማቋቋም ቢሆን ተረጂዎቹን ሜዳ ላይ መበተን ስለከበደው እስከ ሰኔ እንዲቆዩ ፈቀደላቸው፡፡ “ሰኔ ሲመጣ ተረጂዎቹን እበትናቸዋለሁ? ወይስ ምን አደርጋቸዋለሁ? ይህ በጣም ከባድ ፈተና ሆኖ እያስጨነቀኝ ነው” በማለት ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ገልጸዋል፡፡
ለት/ቤቱና ለዕደ ጥበብ ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም በወር 20ሺህ ብር ይከፈላል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ወርሃዊ ወጪ ከ350 ሺህ ብር በላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር በውጪም ሆነ በአገር ውስጥ ድርጅት አይረዳም፡፡ ድርጅቱ ለበጎ አድራጎት የሚያውለውን ገቢ የሚያገኘው የድርጅቱ መስራች ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ በግሏ ከምትሰራው የተለያዩ ሥራዎችና ከብድር ነው፡፡
ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ለ739 አባላት (ህፃናት፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች) ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ሰምተናል፡፡ 17 ወላጅ አልባ ሕፃናትና ሦስት የወ/ሮ ሙዳይ ልጆች ግቢው ውስጥ ያድራሉ፡፡ ሌሎቹ ግን ቤት ተከራይታላቸው ነው የሚኖሩት፡፡ ማኅበሩ ከነርሰሪ እስከ 8ኛ ክፍል ያስተምራል፡፡ ለ27 የት/ቤቱ መምህራንና ለ4 የአስተዳደር ሰራተኞች ደሞዝ ይከፍላል። 205 ተማሪዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ይማራሉ፡፡ 700 የቤት ኪራይና የህክምና ወጪ የሚሸፈንላቸው ወላጆችና አሳዳጊዎች አሉ፡፡ በ2ኛ ደረጃ፣ በፕሪፓራቶሪና በኮሌጅ ደረጃ የሚማሩ አሉ፡፡ ከ4-7 ዕድሜ ያላቸው 70 ተማሪዎች በነርሰሪ፣ በኬጂ 1 እና ኬጂ 2 ተከፍለው ዩኒፎርም ተሰፍቶላቸው፣ በቀን ሦስቴ እየተመገቡና የመማሪያ ቁሳቁስ ተችለው በነፃ እየተማሩ ነው፡፡
“እኔ ብዙ ነገር እሰራለሁ ከአየር በአየር ጀምሮ የማልሰራው ሥራ የለም፡፡ ለምሳሌ ቤት አሻሽጣለሁ ገዢና ሻጩን በስልክ አገናኝቼ ገዢው ቤቱን ከወደደውና ተስማምቶ ከገዛው በኋላ ኮሚሽኔን እቀበላለሁ፡፡ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ፣ የውበት ሳሎን፣ የከብት እርባታ… አለኝ፡፡  ብድር አትፈራም፤ የተጨበጨበልኝ ተበደሪ ነኝ፡፡ ሰውም አይጨክንብኝም አሁን እንኳ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማህበር የተበደርኩት 2 ሚሊዮን ብር አለብኝ። ተበዳሪ ብቻ ሳልሆን በወቅቱም ብድሬን እከፍላለሁ። ውጭ ስሄድ አንዳንድ ሰዎች የሚሰጡኝም አለ፡፡ ከማህበሩ የእደጥበብ ሙያ ከሚሰሩ ባህላዊ ሥራዎች (ከሸክላ ውጤቶች በዘንባባ ከሚሰሩ የተለያዩ ቁሳቁሶች፣ ከጥጥ ውጤቶች…) ሽያጭ የሚገኝ ገቢም አለኝ፡፡ እንግዲህ በዚህ በዚህ ነው ድርጅቱን የማስተዳድረው፡፡ አሁን ግን እየቃተኝ ስለሆነ ደጋፊ እፈልጋለሁ” ብላለች፡፡
ሙዳይ በጐ አድራጐት ማህበር ከመንግሥትና ከህብረተሰቡ ድጋፍ እያፈላለገ ነው፡፡ ወርሃዊ የቦታ ኪራይ ወጪ በየጊዜው ቀጣይና እየናረ ስለሚሄድ መንግስት ለማህበሩ ማዕከል ግንባታ ቦታ እንዲሰጠው ይፈልጋል። ሌላው ደግሞ አቅም ያላቸው ሰዎች የአንድ ተማሪን ወርሃዊና አመታዊ ወጪ በመሸፈን እንዲረዱ፣ የተለያዩ ድርጅቶች የሚያመርቷቸውን የምግብና የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች በአይነት እንዲለግሱ፣ ህብረተሰቡ የተማሪዎቹ ወላጆችና አሳዳጊዎች ማህበሩ በሰጣቸው የእደጥበብ ሙያ ስልጠና የሰራቸውን ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶች እንዲገዛ ጠይቋል፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ ተረጂ ወገኖች ለእነሱ ጊዜ ሰጥቶ የሚያነጋግራቸውና የሚጐበኛቸው ሰው በጣም ስለሚፈልጉ ህብረተሰቡ ወደ ማዕከሉ መጥቶ ፍቅር እንዲሰጣቸው ጋብዟል፡፡
“ሙዳይ በጐ አድራጐት ማህበር” እስካሁን በተለያየ መንገድ ድጋፍ ላደረጉለትና ለረዱት ግለሰቦችና ድርጅቶች ሰሞኑን በሃርሞኒ ሆቴል ባዘጋጀው ፕሮግራም አመስግኗል፡፡    

Read 6173 times