Saturday, 19 December 2015 11:02

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ከ134 ሚ. ብር በላይ ማትረፉን አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ባለፈው ዓመት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ134 ሚ. ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሚሊኒየም አዳራሽ ባካሄደው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ፤ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ማርሻል ፍቅረማርቆስና የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ እሸቱ ፋንታዬ ለባለአክሲዮኖች ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ ባንኩ፣ በዓመቱ ባደረገው እንቅስቃሴ ከታክስ በኋላ 134.5 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገልፀዋል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ትርፍ ለአጠራጣሪ ብድሮች መጠባበቂያና የእርጅና ክፍያ ተቀንሶ፣ 181.9 ሚሊዮን ብር እንደነበር ጠቅሰው፣ ከዕቅድ በላይ 6.5 ሚሊዮን ብር ወይም 3.7 በመቶ እንዲሁም ከዓምናው የትርፍ መጠን ጋር ሲነፃፀር የ74.2 ሚሊዮን ብር ወይም የ69 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ከአምናው 607 ሚሊዮን ብር ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምሮ 1.35 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ በዓመቱ 3.44 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 3.50 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንና የ57.8 ሚሊዮን ብር ወይም የ1.7 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ 1.45 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር የተሰጠ ሲሆን 797.3 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከደንበኞች መሰብሰቡን፣ ይህም በበጀት ዓመቱ ለመስጠት ከታቀደው ብድር ጋር ሲነፃፀር 196.3 ሚሊዮን ብር ወይም የ15.6 በመቶ፣ የተሰበሰበው ብድር ደግሞ 406.8 ሚሊዮን ብር ወይም 104.2 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 1.49 ቢሊዮን ብር ወይም 49.5 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 4.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ይህም ከዓመቱ ዕቅድ 4.45 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ54.8 ሚሊዮን ወይም የ1.2 በመቶ ብልጫ እንዳለው፤ ባንኩ በዓመቱ ከመንግሥት የገዛው ቢል 413.76 ሚሊዮን ብር ዋጋ እንዳለውና ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የ68.4 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን፣ ይህ መጠንም የአጠቃላይ ብድሩን 43 በመቶ ሲይዝ የአጠቃላይ ሀብቱን ደግሞ 23 በመቶ እንደሚሸፍን፤ በአንድ አክሲዮን የተገኘው የትርፍ መጠንም 28.7 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባንኩ በበጀት ዓመቱ 20 አዳዲስ ቅርንጫፎች በመክፈት የቅርንጫፎቹን ቁጥር  80 ማድረሱንና 747 ቋሚ የሰው ኃይል  እንዳሉት ታውቋል፡፡

Read 2941 times