Saturday, 19 December 2015 10:17

ከሟች ላይ የጠፋው 5 ግራም የጆሮ ወርቅ ሆስፒታሉንና ቤተሰብን እያወዛገበ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(29 votes)

    ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ታመው ተክለሃይማኖት ጠቅላላ ሆስፒታል ከገቡትና ለ10 ቀናት በህክምና ላይ ቆይተው ጥቅምት 6 ቀን ህይወታቸው ካለፈው ወይዘሮ አየለች ደግፌ ጆሮ ላይ የጠፋው 5 ግራም የጆሮ ወርቅ፤ ሆስፒታሉንና የሟች ቤተሰብን እያወዛገበ ነው፡፡ የሆስፒታሉ የፅኑ ህሙማን ክፍል ኃላፊ ሲስተር አስናቀች ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “ወርቁ ከአስከሬኑ ጋር አብሮ የተገነዘ በመሆኑ መቃብሩ ይቆፈርልኝ” ማለታቸውን የሟች ልጅ አቶ ሰለሞን ጌታቸው ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
እናቴን “ለመጨረሻ ጊዜ ፅኑ ህሙማን ክፍል ገብተን ስናያት ወርቁ ጆሮዋ ላይ መሆኑን ተመልክቻለሁ” ያለው አቶ ሰለሞን፤ “ከሞተች በኋላ ወርቁን ስጠይቅ ከአስከሬኑ ጋር ተገንዟል ተባልኩኝ፤ እውነቱ እንዲወጣ ስለምፈልግ መቃብሩ እንዲቆፈር ብፈቅድም እስካሁን ምንም ምላሽ አላገኘሁም” ብሏል፡፡
“ዛሬ ነገ እያሉኝ በመመላለስ ብዙ ተንከራተትኩ፤ እኔ ጉዳዬ ከወርቁ አይደለም፤ ነገር ግን መቃብሩ ተቆፍሮ እውነቱ እንዲወጣና ለሌሎችም ትምህርት እንዲሆን እፈልጋለሁ” ይላል አቶ ሰለሞን፡፡ ሆኖም ሥራዬንና ጊዜዬን ከማባከን በቀር እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አልቻልኩም ሲል አማርሯል የሟች ልጅ፡፡
የሆስፒታሉን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ስዩምን አነጋግሬ ነበር ያለው አቶ ሰለሞን፤ “ኃላፊዋ ወርቁን እንድትከፍል ወስነው ነበር፤ ነርሷ ዋጋውን ከጠየቀችኝና ከነገርኳት በኋላ ነው መቃብሩ ይቆፈር ያለችኝ” ብሏል፡፡ እኔ ከራሴ ጋር እየታገልኩም ቢሆን እውነት እንዲወጣ፣  ወጪውን ሸፍና ቁፋሮውን እንድታካሂድ ብፈቅድም ኃላፊዋ የተለያዩ ምክንያቶች እየፈጠረች ጊዜዬን እያባከነች ነው ያለው አቶ ሰለሞን፤ ሆስፒታሉ ለጉዳዩ እልባት የማይሰጠኝ ከሆነ ማስረጃዎቼን ይዤ ወደ ፍርድ ቤት አመራለሁ ብሏል፡፡
አንድ ህመምተኛ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል (ICU) ሲገባ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ የጠይቀናቸው የህክምና ባለሙያ እንደነገሩን፤ ህመምተኛው “እንኳን ጌጣጌጥ ከቤቱ ያመጣውን ፒጃማ እንኳን መልበስ አይችልም፤ ብዙ ጊዜ ፅኑ ህሙማን በማሽን ስለሚተነፍሱና የልብ ምታቸው በየጊዜው ስለሚታይ በአብዛኛው ደረታቸው ክፍት መሆን አለበት፤ ስለዚህ በአንሶላና በብርድልብስ ብቻ ይሸፈናሉ” ከዚህ አንፃር ህመምተኞች ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል ሊገቡ ሲዘጋጁ ማናቸውም ጌጣጌጥና ብራስሌት ወላልቆ ለቅርብ ቤተሰባቸው እንደሚሰጥ የጠቆሙት ባለሙያዋ፤ ይህም የፅኑ ህሙማን ክፍል ኃላፊዎች ሥራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  
“የጆሮ ጌጡ ከአስከሬኑ ጋር ተገንዞ ቢሆን እንኳን የፅኑ ህመምተኛ ክፍል ኃላፊዋ ስራቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ከተጠያቂነት አያመልጡም” ብለዋል - ባለሙያዋ፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ስዩም ምላሽ እንዲሰጡን ጥረት ብናደርግም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

Read 9025 times