Saturday, 19 December 2015 10:11

“ሚሊኒየም የገና ገጸ በረከት” ፌስቲቫልና ኤክስፖ ቅዳሜ ይከፈታል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

     በንግድ ትርኢትና የተለያዩ ገጽታዎች ባሏቸው የመዝናኛ ዝግጅቶች ለ12 ቀናት የሚካሄደው “ሚሊኒየም የገና ገጸ በረከት” ፌስቲቫልና ኤክስፖ በመጪው ሳምንት ቅዳሜ ይከፈታል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበርም በቀጣዮቹ 12 ቀናት፣ የተመሠረተበትን 80ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር የፌስቲቫሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳዊት ውብሸት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ፌስቲቫሉና ኤክስፖው ከበዓል ዕቃዎች ግብይት በተጨማሪ የተለያየ ፋይዳ ያላቸው አዝናኝና ቁምነገር አዘል ሁነቶች ይካሄዱበታል የተባለ ሲሆን ከነዚህም መካከል የንባብ ባህልን ለማስፋፋት በርካታ መጻሕፍት ቤቶች እንደሳተፉና “ንባብ ለሕይወት” በሚል መርሕ በርካታ መጻሕፍት በሽልማት እንደሚበረከቱ የኮሚቴው ሰብሳቢ ገልጸዋል፡፡
የአዘጋጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጨምረው እንደገለፁት፤ አንጋፋው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመተባበር ከፌስቲቫሉ መክፈቻ አንስቶ እስከሚጠናቀቅበት ዕለት ድረስ የደም ልገሳ ፕሮግራም ያካሂዳል፡፡
ፌስቲቫሉ ኪነ - ጥበብን በማበረታታቱ ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረጉን የተናገሩት አቶ ዳዊት፣ ለዚህም ሲባል በሚሊኒየም አዳራሽ ግቢ ትልቅ አርት ቪሌጅ መሠራቱን፣ ሠዓሊያን ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ከፍተኛ ዕድል መስጠቱን ጨምረው አብራርተዋል፡፡ ከወላጆቻቸው ጋር የሚመጡ ልጆችም እየተዝናኑ የሚማሩበት የራሳቸው ቦታ ተከልሎ መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
የሚድሮክ ግሩፕ በርካታ ኩባንያዎች በሚሳተፉበት በዚሁ ፌስቲቫል የሙዚቃ ኮንሰርቶች የሚካሄዱ ሲሆን ድምፃውያኑ አብነት አጎናፍር፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ጸደንያ ገ/ማርቆስ፣ ሸዋንዳኝ ሀይሉ፣ ሀመልማል አባተ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ “የማያውቁት አገር አይናፍቅም” በሚል ዘፈኑ የሚታወቀው የጥላሁን ገሰሰ የበኩር ልጅ ምንያህል ጥላሁን ገሰሰና ከ16 ዓመታት የውጭ ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራዋን የምታቀርበው ማርታ አሻጋሪ ይሳተፉበታል፡፡ የኮንሰርቱ ገቢም ለስፖርት ማህበሩ ማጠናከሪያና ለሚያሰራው ግዙፍ ስታዲየም ግንባታ እንደሚውል ተጠቁሟል፤ ፌስቲቫሉ ከተዘጋም በኋላ ማህበሩን ይበልጥ የሚያስተዋውቁ ፕሮግራሞች ዓመቱን ሙሉ እንደሚካሄዱ የኮሚቴው ሰብሳቢ አስታውቀዋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርን የ80 ዓመት ታሪክ የሚያወሳ መፅሀፍ ተዘጋጅቶ በቅርቡ እንደሚመረቅ የገለፁት ሰብሳቢው፤ የማህበሩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ጨምሮ በ80 ዓመት ጉዞው የተሸለማቸው ዋንጫዎችና ሜዳሊያዎች የሚታዩበት ዐውደ ርዕይም የፕሮግራሙ አካል ሆኖ እንደሚቀርብ አቶ ዳዊት ውብሸት ተናግረዋል፡፡

Read 1952 times