Saturday, 05 December 2015 09:09

የሼህ ሑሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች

Written by  (ባዩልኝ አያሌው)
Rate this item
(1036 votes)

        በሥነ ግጥም ሐሳብን ቢሉ ስሜትን መግለጽ እንደ ዛሬው የጥቂቶች መሰጠት “ከመሆኑ” በፊት በቀደሙት ዘመናት፣ ግጥም ሀበሾች ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሐሳባቸውን የሚቀነብቡበት፣ ስሜታቸውን የሚገልጹበት… አንደበታቸው እንደነበረ መዛግብትም ሊቃውንትም ይናገራሉ፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ ማህበረሰቡ ሐሳቡን ቢሉ ስሜቱን በግጥም ይነግር የነበረው አፍታ ወስዶ፣ አሰላስሎና ወረቀት ላይ አስፍሮ ሳይሆን ስሜቱን ልብ ባለበት ቅጽበት፣ እንዲሁ በቀጥታ፣ ደግሞም በቃሉ… ልቡ ያቀበለውን በመተንፈስ ነበር፡፡ ለዚህ እማኝ ጥራ ከተባልኩ በየዘመናቱ ለየክስተቱ ማህበረሰቡ የተቀኛቸውንና እየተንጠባጠቡ ለዘመናችን የደረሱትን “ቃል ግጥሞች” እጠራለሁ፡፡
ያም ሆኖ “እም ኮከብ ኮከብ ይሔይስ ክብሩ” (ከአንዱ ኮከብ ክብር የሌላው ይበልጣል እንደማለት) ከየማህበረሰቡ እጅጉን ጎልተው የወጡ ሐሳብ ሰናቂ፣ ቃላት ጠንቃቂ… ባለቅኔዎች በዚችው በእኛዋ ሀገር አልፈዋል፡፡ እኒህ ጠቢባን በግጥሞቻቸው ትናንታቸውን ዘክረዋል፤ ዛሬያቸውንም ከትበዋል። ጥቂቶቹ ደግሞ ከዚህም አልፈው ተራቀዋል- በግጥሞቻቸው የትውልዱን ነገ እስከመተንበይ ድረስ፡፡…  
እንዳለመታደል ሆኖ በሀገራችን ክስተቶችንና ሁነቶችን ዘግቦ መሰነድ (የጽሕፈት ታሪክ አላልኩም) እጅግ የቅርብ ጊዜ ታሪክ በመሆኑ ይመስላል፣ የጠቢባኑ ብሂሎችና ቅኔያት እንዲሁም ሌሎች “ሜዳ ሙሉ ዕውቀቶች” ሳይደርሱንና ሳይተርፉን አምልጠውናል፡፡ ይህም ማን ምን ሠርቶአል? የቱስ የማን ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች እርግጥ የሆነ መልስ እንዳይኖረን ይልቁንም ግምቶችና መላምቶች ላይ እንድንቆም አድርጎል፡፡ ይህ እንግዲህ መዝግቦና ቀርሶ የመሰነድ ባህላችን ጠንካራ ባለመሆኑ የገባንበት ውዥንብር መሆኑ ነው፡፡
በዚህ ጽሑፍ ከቀደምት ልበ ብሩህ ባለቅኔዎቻችን አንዱ የሆኑትን ሼህ ሑሴን ጅብሪልን እና ትንቢታዊ ግጥሞቻቸውን በጨረፍታ እናያለን፡፡ ለዚህም ሰውየው ማን ናቸው? የሚለውን ገር ጥያቄ አስቀድመን፣ መቆያችንን ትንቢታዊ ግጥሞቻቸው ላይ እናደርጋለን፡፡ ስለሼህ ሑሴን ማንነት፣ ክህሎትና ትንቢታዊ ግጥሞች የተለያዩ ጸሐፍት (ቦጋለ ተፈሪ፣ ኤሏ ፊኬ፣ ጌቴ ገላዬ፣ ጥላሁን ብርሐነ ሥላሴ፣ ብርሃኑ ገበየሁ) እጃቸው የገቡ መረጃዎችን መነሻ በማድረግ ጽፈዋል፡፡ የእኔም ቅኝት እማኝ የሚያደርገው ጸሐፍቱ ያቀበሉንን መረጃዎች ይሆናል፡፡
ሼህ ሑሴን ጅብሪል በ1811 በወሎ ክፍለ ሀገር፣በወረሄመኖ አውራጃ እምበለ ሴዳ ተብሎ በሚጠራ ቦታ እንደተወለዱና በ1908 ዓ.ም በ97 ዓመታቸው ማረፋቸውን ቦጋለ ተፈሪ “ትንቢተ ሸህ ሑሴን ጅብሪል” በተባለው መጽሐፋቸው ያወሳሉ። ሼህ ሑሴን ግጥሞችን መድረስ የጀመሩት የሰባት ዓመት ልጅ ሆነው ነው፡፡ እጅጉን ያስከበራቸው፣ ታዋቂ ያደረጋቸውና ተከታዮችን ያፈራላቸው ግን ወደ ፊት ስለሚፈጸሙ ነገሮች በግጥሞቻቸው መተንበያቸውና ትንቢቶቹም ጊዜያቸውን ጠብቀው መፈጸማቸው ነው፡፡
ሼሁ ግጥሞቻቸውን “ይነግሩ (ይደርሱ)” የነበረው በቃላቸው ነው፤ እዛው ስሜቱ በተፈጠረበት ቦታና ቅጽበት፡፡ ግጥሞቹን ሲነግሩም ብርዝ ጠጅ በእጃቸው ይዘው እየተጎነጩ ነበር ይሉናል፤ የሼሁን ታሪክና ግጥሞችን ያጠኑት ቦጋለ ተፈሪ፡፡… የሼህ ሑሴን ግጥሞች ናቸው ተብለው ከተለያዩ ምንጮች ተገኝተው የተመዘገቡት ግጥሞች ከ220 በላይ ናቸው፡፡ ግጥሞቹ የተደረሱት በቃል እንደሆነ ሁሉ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ (የሼህ ሑሴን ግጥሞች በተለይ በወሎ ማህበረሰብ ዘንድ በሰፊው ይታወቃሉ) የኖሩትም እንዲሁ በቃል ነው። ይህም ግጥሞቹ ተንጠባጥበው እንዲቀሩ እንዲሁም (ህልውናቸው በቃል በመሆኑ) እንዲቆነጻጸሉ ምክንያት ሆኖአል፡፡
የሼህ ሑሴን ግጥሞች አብዛኞቹ ትንቢታዊ እንደሆኑ፣ ይዘታቸውም ከዘመነ መሳፍንት (1769) እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ በኢትዮጵያ የተከሰቱ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች እንደሆኑ  “Poems of the Prophesier Sheikh Hussein Jibril” የተባለው ሥራ ይገልጻል፡፡ ግጥሞቹ በወቅቱ እየሆነ ያለውን ከመንገር አልፈው የነገሥታቱንም ሆነ የሀገሪቱን እንዲሁም የህዝቡን መጻኢ እጣ በፍጹም ነጻነት፣ ፊት ለፊት በሆነ ቋንቋ ተንብየዋል። አንዳንዶቹ ግጥሞችም የደመቀ ትችትን ያቋቱ ናቸው፡፡ በርካታ ጉዳዮችን ከከተቡት የሼህ ሑሴን ግጥሞች መካከል ትኩረታቸውን በየዘመናቱ በተነሱ ገዢዎችና መንግሥታቸው ላይ ያደረጉትን ጥቂት ግጥሞች እያነሳሳን እንቆይ፡፡
ሼህ ሑሴን በዘመናቸው ከነበሩት ከአጼ ዮሐንስ ጋር በአብዛኛው ግጭት ውስጥ ነበሩ፡፡…  በዚህም ይመስላል ንጉሡን ተችተው ግጥሞችን ገጥመዋል። ከግጥሞቹ መካከል “የንጉሡን ፍጻሜ የተነበዩበት” የሚመስለው ግጥም ይህን ይላል፡፡ የግጥሙን ኃይልና ጉዳዩን ልብ እንል ዘንድ ግጥሙን አንብበን በታሪክ የሆነውን እናስታውስ፡፡
አራት ወር ሲቀረው ምኒልክ ሊነግሥ
በመተማ በኩል ትጨሳለች ጭስ
ጭሷ በራስ ገብታ የምታስነጥስ
እጅግም አትበጀው ለአጼ ዮሐንስ
አላህ ሽቶበታል አንገቱን ሊቀምስ፡፡
የሼህ ሑሴን ግጥሞች በአድናቆትም ይሁን በትችት ያልጎበኙት ንጉሥ የለም ማለት ይቻላል። በዘመናቸው የነበረውን ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት የሚነግሠው ንጉሥ ማን እንደሆነ ከመንገር ጀምሮ፣ አገዛዙ ምን እንደሚመስልና ፍጻሜውም ምን እንደሚሆን በፍጹም ነጻነትና እጅግ ኪናዊ በሆነ መንገድ ተንብየዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ያልነበሩት ሼሁ፤ ወደ ፊት ይፈጸማል ያሏቸውን ጉዳዮች የቋጠሩባቸውን ሁለት ግጥሞች እነሆ፡-
የአላህን ትተው በውሻ የሚመሩ
በሐበሻ መሬት ግፍን የሚሠሩ
ቁመታቸው አጭር መልካቸው የሚያምሩ
አይነግሡም ብላችሁ አትወዳደሩ
ሃምሳ ዓመት ይነግሣል እግረ ውትርትሩ፡፡
ወሎ በረሃብ አልቆ ሞት የበዛ እንደሆን
የሸዋ መኳንንት ዳርቻው ምን ይሆን?
(በቁም ይጋለጣል ይሆናል እንዳይሆን
ተፈሪ የዚያን ቀን ምን ይበጀው ይሆን?)
የጁን አግኝቶታል እንግዲህ ሰው አይሆን::
ሼህ ሑሴን እንደሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ክስተቶች ሁሉ ምናልባትም እሳቸው ካረፉ ከሀያ ዓመታት በ|ላ (በ1928) በኢትዮጵያ ላይ ስለተደረገው የጣሊያን ወረራና ፍጻሜው በግጥማቸው ተንብየዋል። በግጥሙ ላይ በተለይ ዓመታትን በተመለከተ የተነገረው ከሆነው ጋር በትክክል መግጠሙ ሰውየው እውነት ገጣሚ ብቻ ነበሩ ወይስ ምን? የሚል ጥያቄን ይጋብዛል፡፡
ሥራቸው ባለጌ አህያ የሚበሉ
ባሕር ወዲያ ማዶ ክፉ ሰዎች አሉ፣
ሐበሻን ለመውረር ሐሳብ ያስባሉ
የኋላ የኋላ መምጣት ይመጣሉ
አምስት ዓመት ገዝተው ወዲያው ይሄዳሉ፡፡
በጽሑፉ መግቢያ ላይ እንዳወሳሁት፣ የሼህ ሑሴን ግጥሞች ከዘመነ መሳፍንት እስከ አሁን ዘመን ድረስ ስለተፈጸመው፣ ወደ ፊትም ስለሚፈጸመው ጭምር የሚተነብዩ ናቸው፡፡ ቀጣዩ ግጥም፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ ያለውና ለበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋት፣ መሰደድ… በምክንያትነት ስለሚጠቀሰው የደርግ ዘመን መምጣት፣ ባህሪውና ድርጊቶቹ ያወሳል፡፡
ይመጣሉ እነዚያ፣ እነ አይራራ እነጨካኝ፣
ደርጎች የሚሏቸው
ዱአ አድራጊ በቀር የለም የሚችላቸው
እነዚያ ኃይለኞች እነዚያ ጨካኞች
እነዚያ አሽብሮች እነዚያ አንበሶች
በክፉ ያዩትን እነዚያ እርጉሞች
በደግ ለታያቸው እነዚያ ደጎች::
ደርጎች አይቀሩም ይመጣሉ፣
ዝመቱ፣ መንገድ ሥሩ፣ መሬትን ክፈሉ እኩል
የሚሉ
ሰማዩን በባላ ገድፉት ባይሉ፡፡
በሼህ ሑሴን ግጥሞች ይሆናሉ ተብለው የተነገሩትን አንዳንድ ጉዳዮች ከክስተቶቹ ጋር ስናነጻጽር፣ ጉዳዮቹ በታሪክ ጥናት ያልተረጋገጡና ማስረጃ ያልቀረበባቸው ቢመስሉም ቅሉ ግጥሞቹ የክስተቶቹን ዋና ዋና ጉዳዮች ፍጹም አይስቱም። ይልቁንም በአንዳንዶቹ ግጥሞች የተጠቀሱት ቁጥሮች፣ ጊዜና ስሞች ጭምር ፍጹም ይገጥማሉ፡፡…
ምንም አይነት መረጃ ሳይኖረው የሼሁን ግጥሞች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያነብ አንባቢ ግጥሞቹ ታሪኮቹ ከተፈጸሙ በ|ላ ባለ ዘመን የተጻፉ ናቸው ከማለት ያለፈ ሐሳብ አይዝም፡፡ የዚህም ምክንያቱ በግጥሞቹ ቀድመው የተባሉት ጉዳዮችና የተፈጸመው ፍጹም በመግጠሙ ቀድመው ነው የተጻፉት ብሎ ለማመን ስለሚገዳደር ነው፡፡… ሁሉ አይወሳምና ግጥሞቹንና ክስተቶቹን በማንጸር ፍካሬዎቹ ላይ መድረስን አንባቢ ይትጋበት፡፡ ከሼሁ ግጥሞች መካከል ዛሬያችንን የከተበ በሚመስለኝ ግጥም ልሰናበት፡፡
የከተማ ወንፊት በርበሬ እየነፋ
ንፋስ የመጣ እንደሁ ነፊው ዓይኑ ጠፋ
ዓይኑን እስከሚያሸው ነፊ አጥቶ ተደፋ
ንፋስ እያየ ነው በርበሬ የሚነፋ
ፍሬው ካልወደቀ ገለባ አይነፋ፡፡
መልካም ሰንበት!

Read 101755 times