Saturday, 05 December 2015 08:50

በአዲስ አበባ በ41 ሺህ ብር የሆቴል ዕዳ የተያዙት የኬንያ ብሔራዊ ቡድን መሪ ተለቀቁ

Written by 
Rate this item
(14 votes)

ከቡድኑ ጋር ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ፣ ፓስፖርታቸውን ተነጥቀው ነበር
  በሴካፋ ዋንጫ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን የኬንያ ብሄራዊ ቡድን ልኡካን የመሩት የክለቡ ማናጀር ዊሊስ ዋሊያውላ፤ ስድስት የቡድኑ ልኡክ አባላት ለአስር ቀናት አርፈውበት ለቆዩት “እንዳለ እና ቤተሰቡ ቸርቺል ሆቴል መከፈል የነበረበትን 41 ሺህ 154 ብር መክፈል ባለመቻላቸው፣ ከሆቴሉ እንዳይወጡ ታግደው ከቆዩ በኋላ ከትናንተ በስቲያ ተለቀቁ፡፡
የኬንያው ብሄራዊ ቡድን “ሃራምቤ ስታርስ” ከሩብ ፍጻሜ ውድድሩ ውጭ ሆኖ ባለፈው ረቡዕ ምሽት ወደ አገሩ ቢመለስም፣ ዊሊስ ዋሊያውላ ግን ከቡድኑ ጋር የመጡት ስድስት ተጨማሪ የልኡካን ቡድን አባላት በሆቴሉ የቆዩበትን ወጪ መክፈል ባለመቻላቸው ከሆቴሉ እንዳይወጡ ታግደው ከቆዩ በኋላ፣ የኬንያ የስፖርት ሚኒስቴር ክፍያውን በመፈጸሙ ትናንት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን “ሲቲዝን ቲቪ” የተባለው የአገሪቱ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡ የቡድኑ መሪ የሆቴሉን ዕዳ ሳይከፍሉ ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ ፓስፖርታቸውን ተቀምተው ነበር ያለው ዘገባው፤ የኬንያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የልኡካን ቡድኑን ለመሩት ለእኒሁ ግለሰብ ወጪውን እንዲሸፍኑ 250ሺህ የኬንያ ሽልንግ መላኩን ጠቁሟል፡፡
የሴካፋ አዘጋጆች፤ ኬንያ 20 ተጫዋቾችንና አምስት የልኡካን ቡድን አባላትን ብቻ እንድትልክ ቢያስታውቁም፣ የኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን 23 ተጫዋቾችንና የልኡካን ቡድን አባላትን በመላኩና ተጨማሪ ስድስት አባላት በመኖራቸው የገንዘብ እጥረቱ ሊከሰት እንደቻለ ዘገባው ጠቁሟል፡፡

Read 4031 times