Saturday, 28 November 2015 14:35

ቻይና የመጀመሪያዋን ወታደራዊ ካምፕ በጅቡቲ ለማቋቋም አቅዳለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- በውጭ አገራት ወታደራዊ ካምፖችን እንደማታቋቁም በተደጋጋሚ ስትገልጽ ነበር
- ለመርከቦቼ ነዳጅ መሙያና ለጦር መኮንኖቼ መዝናኛ ላደርገው ነው ብላለች

   በውጭ አገራት ወታደራዊ ካምፖችን የማቋቋም ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ ስትገልጽ የቆየችው ቻይና፣ የሎጅስቲክስ ማዕከል ነው ያለችውን የመጀመሪያውን ወታደራዊ ካምፕ በጅቡቲ ለማቋቋም ከአገሪቱ መንግስት ጋር እየተነጋገረች እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ወታደራዊ ካምፑ ለቻይና የባህር ሃይል መርከቦች የነዳጅና የሌሎች ሎጅስቲክሶች አቅርቦት የማሟላትና አገሪቱ በኤደን ባህረ ሰላጤ በምታከናውናቸው የጸረ-ስለላ ተልኮዎች ላይ ለተሰማሩ የጦር መኮንኖችና መርከበኞች በመዝናኛ ማዕከልነት የማገልገል አላማ ይዞ እንደሚቋቋም የቻይና የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡
ወታደራዊ ካምፑ መቋቋሙ የቻይና የጦር ሃይል አለማቀፍ ግዴታዎቹን እንዲወጣ እንዲሁም አለማቀፍና ክልላዊ ሰላምና መረጋጋትን በማስጠበቅ ረገድ የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ  የሚችልበትን ዕድል ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል፡፡
የቻይና የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማቲክና ወታደራዊ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ፣ አገሪቱ ለረጅም ጊዜያት ስትከተለው የኖረችውን በሌሎች አገራት ላይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ያለማድረግ ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እየተዳፈረችው እንደሆነ ያሳያል ብሏል ዘገባው፡፡
በቅርቡ በማሊ በተከሰተውና 19 ሰዎችን ለህልፈት በዳረገው የሽብር ጥቃት፣ 3 ቻይናውያን መሞታቸውን ተከትሎ፣ ቻይና ጽንፈኛ ቡድኖች በአፍሪካ አገራት የሚያደርሱትን ጥቃት ለመታገል ከአህጉሪቱ ጋር ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ዜጎቿ የሞቱባት ቻይና ከጸረ-ስለላ ተልዕኮ በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን፣ በማሊና በሌሎች የአፍሪካ አገራት በተሰማሩ የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ወታደሮቿን ማሰማራቷን ያስታወሰው ዘገባ፣ በጅቡቲ ከዚህ ቀደም የተቋቋሙ የአሜሪካ ጥምር ግብረ ሃይልና የፈረንሳይ ወታደራዊ ካምፖች እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2424 times