Saturday, 28 November 2015 14:26

ዳሽን ባንክ 729 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ዳሽን ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ ከታክስ በፊት 964 ሚሊዮን ብር (ከታክስ በኋላ 729) ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ፣ 19ኛውን የባለአክሲዮኖች ዓመታዊ ጉባዔ በሳምንቱ አጋማሽ በሸራተን ሆቴል ያካሄደ ሲሆን የባንኩ የዲሬክተሮች ሊቀመንበር አቶ ተካ አስፋው፤ በተጠናቀቀው 2014/15 በጀት ዓመት ባንኩ ያደረጋቸው አብዛኞቹ እንቅስቃሴዎች ዕድገት ያስመዘገበባቸው ስለሆኑ ዓመቱ ለባንኩ ጥሩ ነበር ብለዋል፡፡
የአገር ውስጥ ኢኮኖሚ አድጓል፡፡ የብር የምንዛሬ ዋጋ ከዋናዎቹ የውጭ ገንዘቦች ጋር ሲነፃፀር የተረጋጋ ነበር ያሉት አቶ ተካ፤ በዚህም ዘንድሮ ከታክስ በፊት የ964 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገብ ችለናል ብለዋል፡፡ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ1 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ባንኩ፣ በታክስ መልክ 235 ሚሊየን ብር የከፈለ ሲሆን እስካሁን ለመንግሥት በታክስ የተከፈለው 1.67 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የአንድ እጣ የትርፍ ክፍያም 589 ብር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በ18ኛው ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ባለአክሲዮኖች የባንኩን የተከፈለ ካፒታል እንዲያሳድጉ በተወሰነው መሠረት ጁን 30 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ወደ 1.2 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ ይህም የባንኩን የመጀመሪያ (ፕራይመሪ) ክፍያ ወደ 2.38 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ሲያደርገው፣ ባንኩ ለአንድ ተበዳሪ የሚሰጠው የብድር ጣሪያ ወደ 594 ሚሊዮን እንዲያድግ አድርጎታል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው ያሉት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ፤ ባለፈው ዓመት ብሔራዊ ባንክ በአራተኛው ሩብ መንፈቅ ባደረገው ጥናት በዓመቱ 485 አዳዲስ ቅርንጫፎች መቋቋማቸውንና በተጠናቀቀው ዓመት 2,693 ቅርንጫፎች መከፈታቸውን ገልጸዋል፡፡ “ዘንድሮ ከታክስ በፊት ያገኘነው 963.8 ሚሊዮን ትርፍ ከአምናው ትርፍ በ6.2 ሚሊዮን ብር ይበልጣል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ እሴት በ12.8 በመቶ አድጎ፣ 24.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ተቀማጫችን ደግሞ 19.8 ቢሊዮን ሲሆን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ12 .1 በመቶ ዕድገት አለው” ብለዋል፡፡
በተጠናቀቀው ዓመት ለደንበኞቻቸው ተደራሽነትን ለማስፋፋት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች 23 ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመክፈት (ከውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ጋር) የቅርንጫፎቻቸውን ቁጥር 161 ማድረሳቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ የካርድ ሲስተማቸው ተቀባይነት በማግኘቱ ኤቲኤም ወደ 220፣ ፓስ ማሽን ወደ 873 ማሳደጋቸውን ገልጸዋል፡፡

Read 1662 times