Saturday, 28 November 2015 14:25

ዋው ፕራይም የገበያ ማዕከል - ዛሬ ይመረቃል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

  የተሸጠ ዕቃ ይመለሳል
                         
      በሁለት መቶ ካ.ሜ የተንጣለለው ክፍል መስተዋት በመስተዋት ሲሆን በመብራት ተንቆጥቁጧል፡፡ የቤት ዕቃዎች እንደየዓይነታቸውና እንደየፈርጃቸው ተሰድረው ሲያዩ ዋው! በማለት ይደነቃሉ፡፡
ይህ የገበያ ማዕከል (ሞል) ቤት ሠርተው ሲያበቁ ለማጠናቀቂያ (ፊኒሽንግ) የሚያስፈልጉ የተለያዩ የቤት ዕቃዎች  የሚሸጡበት ነው፡፡ ቀደም ሲል መብራት ከአንድ ቦታ፣ ኬብል ከሌላ፣ ቲቪ፣ ፍሪጅ፣ መጋረጃ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ የኪቺን ዕቃዎች… አንዱን መርካቶ ሌላውን ፒያሳ፣ የተቀረውን ቄራ፣ ካዛንቺስ፣…እየተሄደ ነበር የሚገዛው፡፡ ይህ ደግሞ ጊዜና ገንዘብ ያባክናል፤ አሁን ግን እድሜ ለዋው ፕራይም! አማርጠው ከአንድ ስፍራ ይገዛሉ፡፡
ወደ ውስጥ ሲገቡ መጀመሪያ ባለው ክፍል የደንበኛ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ እንግዳው ምን እንደፈለገ ይጠየቅና የፈለገው ዕቃ ወዳለበት ክፍል ወስደው እዚያ ካለ ባለሙያ ጋር ያገናኙታል፡፡
መጀመሪያ የሚያገኙት የኤሌክትሪክ ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል 425 ዓይነት መብራቶች ይገኛሉ፡፡ ቀጥሎ ያለው የሶላር ኤነርጂ ክፍል ነው፡፡ በሶላር ኤነርጂ የሚሠራ ቦርድ በኤል ዲ፣ በኖርማል መብራቶች የሚሠራ የመኝታ ቤት፣ የሳሎን፣ የኮንፈረንስ መብራቶች ያገኛሉ፡፡
የኤሌክትሮኒክስ ክፍሉ ሁለት ነው፡፡ አፒላንስ ወይም ዶመስቲክ በተባሉ ዕቃዎችና በኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ተከፍሏል፡፡ ሆም አፒላንስ በተለያዩ የፊሊፕስ ዕቃዎች ተሞልቷል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ክፍል ለኪቺንና ለሆቴል በሚሆኑ ዕቃዎች ተሞልቷል፡፡ ኦል ኢን ዋን የተለያዩ ብራንዶችን በአንድ ማግኘት ስለሆነ ዕቃው አንድ ዓይነት ሆኖ በተለያዩ አገሮች የተረመቱ ብራንዶችን ይይዛል፡፡ የተለያዩ አገራት ብራንድ የሆኑ ምድጃዎች፣ ልብስ ማጠቢያዎች፣ ቲቪዎች፣ በዚህ ክፍል ይገኛሉ፡፡ ቲቪ ከ24 ኢንች እስከ 55 ኢንች ይገኛል፡፡
የፈርኒቸር ክፍል በሦስት ይከፈላል፡፡ የሆቴል፣ የቤትና የኪችን ዕቃዎች አሉ፡፡ ለባለ 5ም ሆነ ለባለ 4 ኮከብ ሆቴል የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን የያዘ ናሙና ቀርቧል፡፡ የተለያዩ መጋረጃዎች፣ መዝጊያዎች፣ ሴራሚክስ፣ የተለያዩ ጃኩዚና ሳውናዎች፣ በአጠቃላይ ለቤት ማጠናቀቂያ ያልቀረበ ዕቃ የለም።
በኢትዮጵያ ነጋዴው ጥሩ ሰው ከሆነ “የተሸጠ ዕቃ አይመለስም” የሚል ማስጠንቀቂያ ሱቁ ፊት ለፊት ይለጥፋል፡፡ በአውሮፓና አሜሪካ ከሳምንትና ከ15 ቀን በኋላ የገዙትን ዕቃ “አልፈልገውም” ብለው መመለስ መብትዎ ነው፡፡ ብቻ የገዙበትን ሪሲት ማቅረብና በዕቃው ላይ ያለው ታግ መኖር አለበት፡፡
“እኛም ጋ ደንበኞቻችን የገዙትን ዕቃ እስከ 15 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ አይተው ካልፈለጉት በሌላ ዕቃ መቀየር ይችላሉ ወይም የከፈሉትን ገንዘብ በክብር እንመልሳለን” ይላሉ የዋው ፕራይም ኦል ኢን ዋን ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማይ ኃይሉ፡፡
ለሁለት ዓመት ማኅበረሰቡ በተለይም ቤት ሠሪው ያለበትን ችግር በማጥናት በቦሌ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ በተሰራውና አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለበት ሕንፃ ምድር ቤት በ2000 ካ.ሜ ቦታ ያረፈ “All in one” የተሰኘ ሞል ማደራጀታቸውን የጠቀሱት አቶ ግርማይ፣ በአንድ ዓመት ለውስጥ ዲዛይን 10 ሚሊዮን ብር መውጣቱንና ሥራ ለመጀመር ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በአዲስ አበባና በክልሎች ተመሳሳይ የገበያ ማዕከል ለመክፈት ማቀዳቸውን ጠቅሰው፣ ወደፊት በምሥራቅ አፍሪካ ተመሳሳይ የሽያጭ ማዕከል ከፍተው የኢትዮጵያን ምርቶች ኤክስፖርት እንደሚያደርጉ፣ ከእህት ኩባንያቸው ጋር በመሆን በገላን ከተማ በወሰዱት 10ሺህ ካ.ሜ ቦታ ላይ የኮንስትራክሽንና የፊኒሺንግ (የቤትና የቢሮ ዕቃዎች) ለማምረት ግንባታ መጀመራቸውን አቶ ግርማይ ኃይሉ አስታውቀዋል። 

Read 3050 times