Saturday, 28 November 2015 14:10

እየሱሳዊ ሽጉጥ ወግ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(4 votes)

    ሌላው አይነት ጨዋታ ሰለቸን፡፡ እኔ እና ጱጳን፡፡ ጱጳ የጐረቤት ልጅ ነው፡፡ እንደኔው ሥራ ፈት ነው፡፡ እንደኔው ቁማር ይወዳል። ምናልባት ህይወታችን በአጠቃላይ በእርግጠኝነት ላይ የተመሰረተበት ጊዜ ኖሮ ባለማወቁ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ ህይወታችንን ነቃ ለማድረግ ቁማር የሆነ ጨዋታ እናዘወትራለን፡፡
የምናውቃቸው የቁማር አይነቶች ሰለቹን፡፡ ከመጫወት ብዛት እርግጠኛ እየሆንን መምጣት ስንጀምር አንገሸገሹን፡፡ ሌላ አይነት ጨዋታ እየፈለግን ሳለን ኤስ ትዝ አለኝ፡፡ ሽጉጥ ልሰራ ነው ሲል ነበር፡፡ ተሳክቶለት ከሆነ ከኤስ ፈጠራ ውስጥ አዲስ የቁማር አይነት መገኘቱ አይቀርም፡፡ ደወልኩለት፡፡
“ያን እሰራዋለሁ ያልከውን ነገር ጀመርከው?” አልኩት፤ የእቃውን ስም ለመጥራት ሳልከጅል፡፡ የሽጉጥን ስም መጥራት የካርታ ቁማርን መጫወቻ እንደመጥራት ለምን እንዳልቀለለኝ እንጃ፡፡
“ጀምሬ ከጨረስኩት ይዤው እመጣለሁ” አለኝ ኤስ፤ በተለመደው ቀጥተኛነቱ፡፡
“መቼ ይዘኸው ትመጣለህ?”
“ዛሬ ከስራ ስወጣ” ስልኩን ዘጋ፡፡
በሽጉጥ ለመጫወት እንዴት ይቻላል ብዬ አሰብኩ፡፡ ጱጳን አማከርኩት፡፡ ጱጳ በልጅነቱ የሽቦ መኪና እየነዳ፣ የሚነዳው እውነተኛ ያልሆነ መኪና፣ እውነተኛ ስለመሆኑ ለሚመለከቱት ሁሉ ለማረጋገጥ ጮክ ያለ የክላክስ ድምፅ ጱ…ጱ…ጱ!! እያለ ሲያሰማ በሰፈሩ ይውል ነበር፡፡ ጱጳ የሚለውን ስም ያገኘው ከዛ መከራው ውስጥ ነው፡፡
“ሩሌት ለምን አንጫወትም” አለኝ፡፡
“የትኛው አይነት ሩሌት?” አልኩት፡፡
የሩሲያውን ሩሌት እያለኝ እንደሆነ አውቃለሁ። ግን የማውቀውን በሱ አንደበት ስሰማ… መሳደብ የፈለግሁትን የብልግና ስድብ ሌላ ሰው ሲሳደብልኝ የሚሰማኝን ከተጠያቂነት ነፃ የመሆን ስሜት ይሰጠኛል፡፡ “ያው የሩሲያውኑ ሩሌት ነዋ” አለኝ፤ ድምፁን ዝቅ አድርጐ፡፡ ሁለታችንም ደፋር ስለመሆናችን እናወራለን፡፡ ወይንም “ፍርሐት የለብንም” የሚለውን ለማስመስከር ያለማሰለስ እንተጋለን፡፡ በውስጣችን ያለውን እውነተኛ ፍርሐት በትጋታችን ለማድበስበስ፡፡ ነገር ግን እስከዛሬዋ እለት ድረስ በውስጣችን ያለውን ፍርሐት በውጭ አውጥቶ ለመፈተን የሚመጥን ጨዋታ አግኝተን አናውቅም። እስካሁን ድረስ ፍርሐታችንን ለማይጠቅሙ… እንዲሁም በማይጐዱ ፉክክሮች ነበር የምንፈትነው። ፈተናችን ደግሞ ፍርሐታችንን ሸፍኖ ያባብሰዋል እንጂ መፍትሔ ሰጥቶት አያውቅም፡፡
እንደአጋጣሚ ሆኖ፤ ዛሬ የሚመጥን ጨዋታ አገኘን፡፡ ሩሌት የደፋሮቹ ጨዋታ ነው፡፡ የድፍረት ጨዋታ በአእምሮ ሳይሆን በልብ የሚደረግ ነው። ከዚህ በፊት ቼዝ እንጫወት ነበር፡፡ የሚያስብ ማሸነፍ የሚችልበት የጨዋታ አይነት ነው፡፡ የማያስብ ደግሞ ሁሌም በቼዝ ጨዋታ ይሸነፋል። ኤስ ሁሌ ሁለታችንንም ያሸንፈናል፡፡ እኔ እና ጱጳ የምንወደው የእድል ጨዋታ ነው፡፡ ማሰብ ያስጨንቀናል መሰለኝ። ኤስ በሌለበት ግን ቼዝ ራሱ ለእኔ እና ለጱጳ የእድል ጨዋታ ይሆንልናል፡፡ እኔ ያላየሁትን ጠጠር ጱጳ ይበላል፡፡ እኔም የእሱን እንደዛው፡፡ የደፈጣ ጨዋታ ይሆናል የሃሳብ ሰሌዳው። መጽሐፍን እንደ መደባደቢያነት እንደመጠቀም፡፡ በእርሳስ መፃፍ ሳይሆን መወጋጋት፡፡ በዚህ መልክ ቼዙን ዳማ አድርገን ለተወሰነ ጊዜ ተደበርንበት፡፡ ሲደብረን ተውነው፡፡
ኤስ ስለ ሽጉጥ የተናገረው ነገር ትዝ አለኝ። መጀመሪያ አስቦ ነው ነገርዬውን ለመፍጠር የወሰነው፡፡ እሱ እንደዛ ነው ተፈጥሮው፡፡
“ሁሉም ነገር ጨዋታ ነው” አልኩኝ የኤስን ቋንቋ ተጠቅሜ፡፡ ኤስ የሚናገራቸውን መድገም ጀምሬ… ቀጥያለሁ፡፡
“ሁሉም ነገር ጨዋታ ነው፡፡ ሁሉም ጨዋታዎች በጨዋታው ሰዓት የተጫዋቹ አሻራ ያርፍባቸዋል፡፡ የጨዋታው ህግ ከተጫዋቹ እጣ ፈንታ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ የጨዋታው ህግ ደግሞ ከመጫወቻው እቃ ጋር የጠበቀ ቁርኝት አለው” የሚለው ኤስ ነው፡፡
የኤስን አባባል ለጐረቤቴ ልጅ ደግሜ ነገርኩት፡፡
“በሽጉጥ ለመጫወት የምንችለው የሞት ጨዋታን ብቻ ነው” አለ ጱጳ፡፡
“የሞት ጨዋታ ቢሆንም፤ መንግስት ወይንም ፖሊስ ወይንም ሌላ መሳሪያ ተሸካሚ በተለምዶ እንደሚጫወተው አድርገን መጫወት የለብንም” አልኩት እኔ፡፡
“ምን እንጨምርበት?” አለኝ፡፡
“ሩሌት እንጫወት” አልኩት፡፡
ሩሌት ምን ማለት እንደሆነ አስረዳሁት። ያስረዳሁትን ሁሉ አስቀድሞ የሚያውቀው ቢሆንም፡፡ “በሽጉጡ የጥይት ቋት ውስጥ አንድ ጥይት ይቀመጣል፡፡ በካርታ ህግ ካየኸው… ይህ በቋቱ ውስጥ ያለ አንድ ጥይት እንደ ጆከር ነው የሚቆጠረው፡፡ ጆከሩ የደረሰው ሰው ይሞታል፡፡ መሞት ማሸነፍ ወይንም መሸነፍ ነው… የሚለውን የሚወስነው ራሱ ተጫዋቹ ይሆናል” አልኩት፡፡
“መሞት እንዴት ማሸነፍ ይሆናል” አለኝ፤ ያልገባው ቢመስልም ገብቶታል፡፡ እኔ የማወራው ሁሉ ኤስ ሲፈላሰፍ ከተናገረው እየተዋስኩ ነው፡፡ ኤስ ለእኔ በሚናገርበት ወቅት ደግሞ ጱጳም ሰምቷል። ነጣጥሎ የነገረን ነገር የለም፡፡ ከኤስ በስተቀር እኔ እና ጱጳ የተነጣጠለ ማንነትም ሆነ ዕውቀት በራሳችን አላዳበርንም፡፡ ፍርሐታችንም አንድ አይነት ነው፡፡ ምናልባት ያለን ብቸኛ ልዩነት ፍርሐታችን በተናጠል፣ በእየራሳችን አካል ውስጥ መገኘቱ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ የጠየቀኝን ጥያቄ በኤስኛ መለስኩለት፡፡
“እንደ ካርታው ጨዋታ ነው፡፡ እያንዳንዱ የካርታ…የኮንከር ተጫዋች የደረሰውን ካርታ የሚያውቀው ራሱ ነው፡፡ “ኤ” ጦር ለእኔ ጆከር ለአንተ ዶፒዮ ሊሆን ይችላል። በሽጉጡ ካርታ ውስጥም ጥይቷ እንደ አንድ ካርታ ናት፡፡ “ሳትፈልጋት የምትደርስህ ወይንም እየጠበቅካት… እየተመኘኻት የማትደርስህ፡፡…ስለዚህ የሚደርስህ ሞት ከሆነ ትፈልገው ይሆን አይሆን የምታውቀው ራስህ ብቻ ነህ”
“አይ እኔ ጨዋታው ነው ደስ የሚለኝ መሞት አልፈልግም…” አለ ጱጳ፡፡
“መሞት የማይፈልግ ሰውማ መኖርም የለበትም ብሏል ኤስ” አልኩት ከአፉ ተቀብዬ፡፡
“አሁን ዛሬውኑ…በማይረባ ጨዋታ መሞት አልፈልግም ነው ያልኩህ” አለ፡፡
“አሁን መሞት ካልፈለክ ሩሌት መጫወት የለብህም…ለጨዋታው አትመጥንም፡፡ ያንተ መጠን ካርታ ነው ማለት ነው፡፡ ብር መበላት ወይንም መብላት ነው የድፍረትህ አቅም” እንዲህ እየተከራከርን፣ እየተፈላሰፍን ኤስ መጣ፡፡ ቱታውን አጥልቋል፡፡ የሚሰራበት መስሪያ ቤት ከተቀጠረ ዘጠኝ ወር ገደማ ሆኖታል፡፡ የተቀጠረ ቀን የለበሰውን ቱታ ለማሳጠብ ብቻ ያወልቀዋል፡፡ በተረፈ ግን ሁሌ ለብሶት ይተኛል፣ ለብሶት ይውላል፡፡
ኤስ ሁሉንም ስራ ይሞክራል፡፡ የሚሞክረው ግን ጠንቅቆ እስኪያውቀው ድረስ ብቻ ነው፡፡ ሲያውቀው እርግፍ አድርጐ ይተወዋል፡፡ ሃይማኖተኛ ሆኖ ያውቃል፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ ያውቃል፣ አሳ አጥማጅ የነበረበት ወቅትም ነበረ፡፡ የእሱን ጊዜያዊ ወረቶች ቆጥሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ በአስራ ሦስት አመቱ አንድ የድርሰት መጽሐፍ ፅፎ ነበር፡፡ ድርሰቱ ላይ ያሉት ገፀ ባህሪዎች አሁንም ትዝ ይሉኛል፡፡ ኤስ ግን የድርሰቱን ዘመን እንድናነሳበት አይፈቅድም፡፡ ለእሱ ሁሉም ነገር ያለው አሁን የተጠናወተው አባዜ ላይ ነው፡፡ ለዘጠኝ ወር የ tool room ማሽኒስት ሆኗል፡፡ ገና እንደጀመረ…ሁለት ወር ሳይሞላው በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ማሽኖችን በጠቅላላ ማንቀሳቀስ ችሎ ነበር፡፡
ከዛ ወደ ስድስተኛው ወር ገደማ የራሱን ፈጠራዎች መስራት ጀመረ፡፡ በጥገና ላይ የተጣሉ ብረቶችን፣ የመሳሪያ ቅሪቶችን ገጣጥሞ የሆነ ነገር ሰርቶ ይመጣል፡፡ ሲሰና ሰርቶ እስኪጨርስ ባለው ወቅት ማውራትም መስማትም የሚችለው ስለሚሰራው ነገር ነው፡፡ አንድ ሰሞን ስለ ሽጉጥ ነበር ወሬው፡፡ ሽጉጥና የሽጉጥን፤ ምንነት፤ መግደልና መገደል፡፡ የሚሰራውን ነገር ከአገልግሎቱ ነጥሎ አያየውም፡፡ እና ስለ ሽጉጥ አውርቶ ከሄደ በኋላ እኔ እና ጱጳ አግኝተነው አናውቅም፡፡ ዛሬ በጨዋታ ስም እስክንደውልለት ድረስ፡፡
መጣና ቱታውን ለመጀመሪያ ጊዜ አወለቀ፡፡ አውልቆ ተቀመጠ፡፡ እጁ በግራሶ ተጨማልቋል፡፡ ባወለቀው ቱታው አንድ ከመአት የብረት ቁርጥራጭና የመኪና ኩሽኔት የተቀጣጠለች የምትመስል ሞዛዛ ብረት አወጣና በቱታው ይወለውላት ጀመር፡፡
“ዛሬ እኮ ነው ሰርቼ የጨረስኩት… ስትደውልልኝ ገርሞኛል” አለኝ፡፡
“አዎ ሩሌት ልንጫወትበት ፈልገን ነበር… ግን ጱጳ ፈራ” አልኩት፡፡
“ከእኔ ጋር እንጫወታ… ጱጳ ዳኛ ይሆናል፤ እንዲያውም ሽጉጡ እንደሚሰራ መሞከር እየፈለኩ ነበር። መሞከር የፈለኩት ደግሞ በራሴው እጅ ነው”
“በራስህ እጅ ማን ላይ?” አልኩት፡፡ እንደለመደው መፈላሰፍ ጀመረ፡፡
“ይሄ ሃሳብ ነበር ከመጀመሪያውም ሲጨንቀኝ የቆየው። ሽጉጥ መስራት ምንም አዲስ ነገር የለውም። ሽጉጥ በሁሉም ጉልበተኛ እጅ አለ፡፡ ይኸኛው የኔ ፈጠራ ትንሽ የሚበልጠው በሌሎች ላይ ሳይሆን ወደ ራስ የሚተኩስ መሆኑ ላይ ብቻ ነው፡፡ የሚሞክረው ሰው በሌሎች ላይ ሳይሆን በራሱ ላይ ነው ሙከራውን የሚያደርገው፡፡ በሌሎች ህይወት ላይ መድፈር ቀላል ነው፤ በራስ ላይ ግን ከባድ ነው፡፡ ከባዱን ሙከራ ነው የማደርገው ዛሬ”
“አንተ ለራስህ ሙከራ ብለህ ነው የሰራኸው፤ እኔ ግን ጨዋታ እንድንጫወትበት ነው የፈለኩት… ሩሌት…”
“ሩሌት መጫወት አንችልም አየህ… ሩሌትን የሚጫወቱት እኮ ድሃ ሩሲያዊያን ናቸው፡፡ በቂ ጥይት የሌላቸው፡፡ መሳፍንቶቹ ሩሌት ሳይሆን ዱዌል ነበር ይጫወቱ የነበረው፡፡ ሩሌት ለመጫወት… የሽጉጡ መሃደር ከአንድ በላይ ጥይት መያዝ የለበትም፡፡ ስድስት ጥይት በሚይዘው መሃደር አንድ ጥይት አድርገህ በማሽከርከር ትበውዘዋለህ… የተበወዘውን ባለ ተራው በራሱ ላይ ይሞክራል፡፡ ሲሞክር ሞት ይኑረው አይኑረው አያውቅም፡፡ ለመሞት አንድ ስድስተኛ እድል አለው፤ በእያንዳንዱ ፕወዛና ሙከራ፡፡ ይኼ ነው ትክክለኛው የሩሲያዊያን ሩሌት…”
“ታዲያ እንደዛ ለምን አንጫወትም እኛም”
“እንደዛ እንዲሆን አይደለም የተፈጠረው ሽጉጡ… አንድ ስድስተኛ ሞት ማለት… አንድ ስድስተኛ ቆራጥነትም ነው፡፡ አንደኛው ሞካሪ ፍርሀቱን በአንድ ስድስተኛ ድፍረት አካፍሎ… ራሱ ተርፎ ሌላኛው ተፎካካሪ እንዲሞት ነው የሚመኘው። የሩሲያ ሩሌት ጨዋታ ስኬትም ይሄው ሲሆን ነው፡፡ ምኞቱን የሚያሳካው ደግሞ በእድል አማካኝነት ነው። ስለዚህ የሩሌት ጨዋታ እንደ ተራው ሽጉጥ በሌላ ላይ ተኩሶ ራስን ጀግና ከማድረግ የተለየ አይደለም፡፡
“እኔ የሰራሁት ሽጉጥ… ራስን መመርመሪያ ነው። አንድ ሰው ከአንድ ፍርሃቱ ጋር የሚፋጠጥበትን አጋጣሚ የሚለግስ ነው፡፡ አንድ ሰው ሌላው ላይ ተኩሶ መግደል እንደተካነበት ሁሉ፣ በራሱ ላይ ተኩሶም ክህነቱ በርቀት የሚሰራውን ያህል በቅርበትም ይሰራ እንደሆነ የሚያረጋግጥበት ነው… ይኼንን ጨዋታ ለመጫወት… ሌላ ተፎካካሪ አያስፈልግም፡፡ ጨዋታው ከራሱ ጋር ነው። የዚህን ሽጉጥ እጀታ የያዘ ሰው፤ አፈ ሙዙን ወደ ሌላ ሳይሆን ወደ ራሱ ብቻ ነው መቀሰር የሚችለው፡፡ የሽጉጡ አሰራር ለዚህ ብቻ እንዲሆን ተደርጐ የተነደፈ ነው፡፡”
ግራ አጋባኝ፡፡ የሚያኮራ ሳይሆን የሚያስፈራ ፈጠራ ነው፡፡ ሌላውን ለማስፈራራት ራስን ለማጀገን የሚመዘዝ አይነት መሳሪያ አይደለም፡፡
“እና አንተ በራስህ ላይ ልትሞክረው ነው” አልኩት፤ ኃይለኛ ቁማር ሆነብኝ፡፡ በሁሉም አቅጣጫ የሚሸነፍበትን ቁማር ፈልስፎ ለመጫወት የደፈረ ሰው አይቼ አላውቅም፡፡
“አዎን…በሰራሁት ሽጉጥማ መጀመሪያ መሞት ያለብኝ ራሴው ነኝ፡፡ ሽጉጡን ለመስራት እንደደፈርኩት ለመሞከርም መድፈር አለብኝ አይደል? ሽጉጡ አንድ አፈ ሙዝ፣ አንድ ጥይት ብቻ በአንድ ጊዜ የሚይዝ ነው። የሽጉጡን እጀታ አንድ ሰው ነው የሚጨብጠው፣ የሽጉጡ አፈሙዝ የሚያመለክተው ደግሞ አንድ እጀታውን በያዘው አንድ ሰው ላይ ነው፡፡ በፈጠራነቱ አዲስ መሰለኝ። እንደዚህ አይነት የኤጐ ቅስምን የሚሰብር፣ እኔነኛዊነትን የሚያፈርስ መሳሪያ ከዚህ ቀደም ስለ መፈጠሩ እጠራጠራለሁ፡፡
“እና አሁን ስሞክረው ስኬታማነቴን በራሴ ሞት አረጋግጣለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉ ሽጉጦች ሁሉ የፈሪ ናቸው፡፡ የፈሪ ሽጉጦች በእየሱሳዊ ሽጉጥ የቀድሞ ህልውናቸው ከእንግዲህ አጠራጣሪ ይሆናል”
“አሁንስ ያበድክ መሰለኝ ፈራሁህ! በል እስካሁን ስንቀልድ ነው ይኼንን ሁሉ ያወራነው፡፡ አንተም እየቀለድክ መሰለኝ፡፡ ወይንም መስሎኝ ነበር፡፡ እየቀለድክ ቢሆን ይሻላል፡፡ ለሁላችንም፡፡ እውነትህን ከሆነ ግን ይገርማል…”
“እውነቴን ነው፤ ከመቼ ወዲያ ነው ደግሞ እንደዚህ አይነት ቀልድ ስቀልድ የምታውቀኝ?” የመገረም ቅላፄ ያለው ጥያቄ ቢሆንም… በገፅታው ላይ ግን እርግጠኝነት ነበር የሚነበበኝ፡፡
ሰው ግራ ሲገባው ይደነግጣል፤ ሲደነግጥ ይናደዳል፤ ሲናደድ ይሳደባል፡፡ በአንድ ቅጽበት በራሴ የስሜት መዝገብ ላይ ሁሉም ስሜቶች ተንዠዋዠው፡፡
“በል ወዳጄ እዚህ ቤት ውስጥ ይኼንን ሽጉጥህን… ስሙን ምን ነበር ያልከው…?”
“እየሱሳዊ ሽጉጥ”
“ይኼንን እብደትህን ሌላ ቦታ ሄደህ ሞክር፤ አንተ ህይወትህን ጠልተህ በሞትከው እኔ ወህኒ መግባት አልፈልግም፡፡ እኛ ገና ራሳችንን አልጠላንም፡፡ አንተ ከጠላህ ወደ ሌላ ቦታ ሄደህ በራስህ ላይ ያለህን ቂም በራስህ መስዋዕትነት ቂምህን ተበቀል” አልኩት፡፡ ድንገት ለኤስ የነበረኝ አክብሮት በፍርሃቴ ምክንያት ተደመሰሰ፡፡  ለሀሳቡ ያለኝ አክብሮት ተሰረዘ፡፡ ተሸናፊ በመሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ ራሱን ለማጥፋት ይኼንን ያህል የሚያስብና ሃሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ የዚህን ያህል ርቀት የሚጓዝ ሰው ተሸናፊ ነው፡፡ ተሸናፊና እብድ፡፡ አመናጭቄ ከቤቴ አባረርኩት፡፡ ቱታውን መልሶ ሳያጠልቅ በቱታው ውስጥ እየሱሳዊ ሽጉጡን ጠቅልሎ ታቅፎ ነበር፡፡ ያለ ምንም ስንብት በሩን ከኋላው ዘግቶ ወጥቶ ተሰወረ። በቤቱ ውስጥ የጱጳ ወፍራም ትንፋሽና የእኔ ዝምታ ብቻ በዝምታም ሆነ አብዝቶ በመተንፈስ የማይደበቅ ፍርሐትን አክሎ… በቁማር ጨዋታ የማይለጐም መሆኑን እያረጋገጠ ከእኛ ጋር ቀረ፡፡    

Read 3083 times