Saturday, 21 November 2015 13:57

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ አግሮ - ኢንዱስትሪ ፎረም ልታዘጋጅ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ለማሳወቅና ለማስገንዘብ፣ መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) በጋራ ያዘጋጁት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ አግሮ ኢንዱስትሪ ዘንድሮ ፎረም ከሚያዝያ 24 እስከ 26 በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተባለ፡፡
ባለፈው ረቡዕ በሂልተን ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኢንቨስትመንት ፎረሙ፣ ዩኒዶ፣ ከአገሪቷ ጋር በጋራ የሚሠራበት ፕሮግራም አካል ሲሆን፣ የውጭ ኢንተርፕሪነሮች ኢትዮጵያ በገበያና በኢንቨስትመንት መዳረሻነት ያላትን አቅም እንዲገነዘቡ የሚያስችል ልዩ ዕድል ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡ ከዚህም በላይ በኢትዮጵያ ገንዘባቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮች፤ በኢንዱስትሪና በቢዝነስ ሽርክና፣ በእርሻ ምግብ አዘገጃጀት፣ በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች፣ አብሮ ለመሥራት ያለውን ዕድል በተጨባጭ ለመፈተሽና ለማጥናት ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት በፈጣን ዕድገት ላይ ያለች አገር ስትሆን በዓለም ላይም ለውጭ ኢንቨስትመንት እጅግ አመቺ ናት፤ በዚሁ ዓይነት መንገድ ትቀጥላለች” ያለው መግለጫው፤ የረዥም ጊዜ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ለመድረስ፣ በአጭር ጊዜ ዓመታዊ ዕድገት ላይ ማተኮር ወሳኝ ነው፤ መንግሥት ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፎ ወደ ተግባር ገብቷል፤ ቀጣይነት ያለውና ሁሉን አቀፍ በሆነ የኢንዱስትሪ ዕድገት ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ለሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ስትራክቸራል ትራንስፎርሜሽን፣ ለቴክኖሎጂ ለውጥና ለፈጠራ፣ ኤክስፖርትን ለመጨመር በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) ላይ ማተኮር ያስፈልጋል በማለት አስገንዝቧል፡፡
በሚያዝያው ጉባኤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ኢንተርናሽናል የፋይናንስ ተቋማት፣ የልማት ባንኮች፣ ኢንቨስተሮች፣ መልቲ ናሽናል ኩባንያዎች፣ ጥቃቅንና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና የኢንዱስትሪ ማኅበራት ይተሳተፋሉ ተብሏል፡፡

Read 1332 times