Saturday, 14 November 2015 09:50

ወደራ ዩኒዬን በ163 ሚ.ብር የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ይገነባል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

     በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረብርሃን ከተማ የሚገኘው ወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት ዩኒዬን በ163 ሚሊዮን ብር የዱቄትና የመኮረኒ፣ የፓስታና የብስኩት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፡፡ ዩኒዬኑ ባለፈው ሳምንት የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት በ28 ሚሊዮን ብር ባስገነባው የራሱ ህንፃ ውስጥ አክብሯል፡፡
ከ80 በላይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራትንና ከ80ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በስሩ ያቀፈው ወደ ራ ዩኒዬን፤ ከ10 ዓመት በፊት ሲመሰረት 720ሺህ ብር ካፒታል የነበረው ሲሆን በአሁን ሰዓት ካፒታሉን ወደ 44.5 ሚሊዮን ብር ማሳደጉን የዩኒዬኑ ስራ አስኪያጅ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ዩኒዬኑ በከተማውና በዙሪያው የምግብ እህሎች የዋጋ ንረት ሲያጋጥም ገበያ በማረጋጋትና ከክምችቱ አውጥቶ በተመጣጣኝ ዋጋ እህል በማቅረብ፣ ለነዋሪው ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የዞኑ አስተዳደር አቶ ግርማ የሺጥላ በእለቱ ተናግረዋል፡፡
 ዩኒየኑ የራሱን የዱቄት ፋብሪካ ከፍቶ የከተማው ህዝብ በተመጣጣኝ ዋጋ ዱቄት እንዲያገኝ ሳያደርግ መቆየቱ የተገለፀ ሲሆን ለ154 ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠሩም ተገልጿል፡፡
ዩኒየኑ ያስገነባው ባለ ሶስት ወለል ህንፃ፣ ከ350 እከከ 400 ሰው የሚያስተናግድ የስብሰባ አዳራሽ፣ ለቢሮ የሚያገለግሉ ክፍሎችንና የተለያዩ መጋዘኖችን የያዘ ሲሆን እስከዛሬ ለጠቅላላ ጉባኤ፣ ለውይይት የስብሰባ አዳራሽ ይከራዩ እንደነበር የገለፁት የዩኒዬኑ ስራ አስኪያጅ፤ አሁን ይሄ ሁሉ ቀርቶ በራሳቸው አዳራሽ፣ ቢሮ፣ መጋዘንና ሌሎችንም አገልግሎቶች ማግኘት መጀመራቸው ዩኒዬኑ በአስር ዓመት ውስጥ ካስመዘገበው ስኬት ውስጥ በዋናነት የሚጠቀስ ነው ተብሏል፡፡
 ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብራቱ መለሰ፤ ህንፃውን መርቀው የከፈቱ ሲሆን ዩኒዬኑ ከዞኑ አስተዳደር በነፃ ባገኘው 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ163 ሚ ብር ለሚያስገነባው የፓስታ፣ የዱቄት፣ የመኮረኒና የብስኩት ማቀነባበሪያ ፋብሪካም የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
ሚኒስትር ዲኤታው በዩኒዬኑ ስኬት መደሰታቸውን ገልፀው፤ በሚያደርገው እንስቅስቃሴ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከጐኑ እንደሚቆም ተናግረዋል፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ በበኩላቸው፤ ደብረ ብርሃን ከአዲስ አበባ ቅርብ ከመሆኗም ባሻገር በርካታ የቱሪስት መስህቦች ያሏትና ለኢንዱስትሪ አመቺ በመሆኗ፣ በዞኑ ለመስራት የሚፈልግ ካለ በደስታ እንደሚቀበሉ ተናግረዋል፡፡     

Read 2109 times