Saturday, 14 November 2015 09:37

በቂና ተገቢ ምላሾች ያልተሰጡበት የፌደሬሽኑ መግለጫ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

• ሶስት ግለሰቦች ተጠያቂዎች ሆነዋል፡፡ የስራ አስፈፃሚው አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ከሃላፊነት
ሲታገዱ ሁለቱ ሰራተኞች የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ዘሪሁን ቢያድግልኝና፣ የአይቲ
ባለሙያዋ ዘውድነሽ ይርዳው ደግሞ ተባርረዋል፡፡
• ከስራ አስፈፃሚው አባላት አንዱ ይቅርታ ሲጠይቁ፤ ፕሬዝዳንቱና ሌሎቹ አመንትተዋል
• ጠቅላላ ጉባዔ እንደማይጠራም ተገልጿል፡፡

    በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ  ላይ የፌዴሬሽን አስተዳደር ባደረሰው ከባድ ጥፋት ዙርያ በትናንትና እለት በኢንተርኮንትኔንታል የተሰጠው መግለጫ በቂና ተገቢ ምላሾች  ሳይሰጡት ቀረ፡፡ የሴቶች እግር ኳስ ባለድርሻ አካላት፤ የስፖርት ቤተሰቡ፤ የሚዲያ አካላትና ሌሎች ባለሙያዎች በሉሲዎች የውድድር ተሳትፎና የወፊት አቅጣጫዎች ላደረሱ ጥፋቶች አጠቃላይ አስተዳደሩ ተጠያቂ መሆን እንደሚገባውና በይፋ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት ሲያሳስቡ ቢሰነብቱም መግለጫውን የሰጡት የፌደሬሽኑ አመራሮች ለደረሱት ጥፋቶች ሶስት ግለሰቦችን ተጠያቂዎች አድርገው በርካታ ጉዳዮችን አድበስብሰው አልፈዋል፡፡
ትናንት በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በተካሄደው ጋዜጣው መግለጫ 4 የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባላት ተገኝተዋል፡፡ እነሱም ፕሬዝዳንቱ አቶ ጁነዲን ባሻ፤ እንዲሁም ሌሎች የስራ አስፈፃሚው አባላት ኢንጅነር ጆን ቼቤ፤ አቶ አበበ ገላጋይ፤ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው እና አቶ አሊ ሚራህ ነበሩ፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ስራ አስፈፃሚዎቹ ሉሲዎች ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ውድድር ውጭ የሆኑባቸውን ጥፋቶች የፈፀሙት 3 ግለሰቦች መሆናቸውን እንዳረጋገጡ ሲገልፁ አንደኛው የስራ አስፈፃሚ አባል እንደሆኑና፤ ሁለቱ የፌደሬሽኑ ሰራተኞች ናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የመጀመርያው ጥፋተኛ  ተብለው ከሃላፊነታቸው የታገዱት የስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ  አባል የነበሩት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ናቸው፡፡ አቶ ዮሴፍ በመግለጫ ላይ ተገኝተው ለሚዲያ ቃላቸውን እንዲሰጡ እድል ተሰጥቷቸው እንደነበር ውሳኔውን ያሳለፉት የስራ አስፈፃሚ አባላት ገልፀዋል፡፡ መረጃዎች እንዳመለከቱት ግን ይህ እድል እንደተነፈጋቸውና ከስራ ካገዳችሁኝ ሃላፊነቱን እለቃለሁ ማለታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ለእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከካፍ የተላኩትን የውድድር ተሳትፎ ማረጋገጫ 4 ደብዳቤዎች በአግባቡ ባለመመልከታቸው ሁለት የፌዴሬሽን ተቀጣሪዎች ተጠቃቂ ተደርገዋል፡፡ ሁለቱ ሰራተኞች ለአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  በተገቢው ጊዜ ምላሾችን ባለመስጠታቸው፤ ከሚመለከታቸው ጋር በቅርበት ባለመስራታቸውና ስለ ውድድር የተሳትፎ ማረጋገጫ ማሳወቅ ቢኖርባቸውም ግድየለሽነት በማሳየታቸው ከስራቸው እንዲባረሩ ተወስኖባቸዋል፡፡ የመጀመርያው የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ ሲሆኑ ፌደሬሽኑ እንዳሰናበታቸው ከማሳወቁ በፊት የስራ መልቀቂያ አስገብተው ነበር ተብሏል፡፡ ሌላዋ ተጠያቂ ሆና ከስራዋ እንድትሰናበት የተወሰነባት ደግሞ ለረጅም ዓመታት በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የቀድሞ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆና በርካታ ስራዎች ስታከናውን የነበረችው የፌደሬሽኑ የአይቲ ዲፓርትመንት ሃላፊ ዘውድነሽ ይርዳው ናት፡፡ ዘውድነሽ በደረሰው ጥፋት ከካፍ በቀጥታ ይደርሷት የነበሩትን ደብዳቤዎች በግድየለሽነት ተመልክታለች፤ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሳይሆን የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፎን የሚመለከት ደብዳቤ ነው በሚል አዘናግታለች በሚል ጥፋተኛ መደረጓን በመግለጫ ላይ የነበሩት የስራ ሃላፊዎች አብራርተዋል፡፡
ከ1፡30 በላይ በፈጀው ጋዜጣዊው መግለጫ ላይ ከ30 በላይ የስፖርት ሚዲያዎች ተገኝተው ነበር፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ  መድረኩ ለሁሉም ጥያቄዎች ዕድል መስጠት የማይቻበት መሆኑን በተደጋጋሚ በመግለፅ፤ የምናካሂደው ጋዜጣዊ መግለጫ እንጂ ስብሰባ አይደለም በማለት ሲናገሩ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ጋዜጣዊ መግለጫው በርካታ ጥያቄዎች ያልተመለሱበት፤ በርካታ አሳሳቢ አጀንዳዎች ማብራርያ ሳይሰጥባቸው የተድበሰበሱበት በስፖርት ሚዲያውና በፌዴሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች መካከል የተለያዩ ውዝግቦች የ የተንፀባረቁበትና አለመደማመጥ የሰፈነበት  ነበር፡፡
በመግለጫው ላይ ከተገኙ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ኢ/ር ጆን ቼቤ ብቻ በይፋ ይቅርታ ቢጠይቁም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ እና አብረዋቸው መግለጫ ላይ የነበሩት ሦስት የሥራ አስፈጻሚ አባላት  ይቅርታ ለመጠየቅ እንዳዳገታቸው ለመታዘብ ተችሏል፡፡ አንድ ሁለት ሰው ባጠፋው ሁሉም መወንጀል የለበትም፤ የሚል አቋማቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የስፖርት ሚዲያዎች ፌደሬሽኑ ለደረሱት ጥፋቶች በይፋ ይቅርታ እየተጠየቀ ነው አይደለም በሚልም ግራ መጋባታቸውን በተለያየ መንገድ ቢገልፁም፤ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ይህን አስመልክቶ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ፤ በቂ ማጣራት እና ምርመራ አድርጎ መግለጫ ከመስጠት በላይ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ፤ ጥፋተኞችን ከስራ በማገድ እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎቹን ለመወሰን ምክክር በማድረግ የተከተልናቸው እርምጃዎችን መገንዘብ አለባችሁ ከዚህ በላይ ይቅርታ ለማለት ያዳግተናል ብለዋል፡፡
ከጋዜጣዊ መግለጫው በፊት ባለፈው ሰሞን ክለቦች አቋማቸውን ያሳወቁባቸውን ደብዳቤዎችን ማሰራጨታቸው የሚታወስ ነበር፡፡ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ በጉዳዩ ላይ አፈጣኝ ማብራርያ እንደሚያስፈልግ ሲያሳስብ የቡና ስፖርት ማህበር ደግሞ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ጠይቋል፡፡  የቅዱስ ጊዮርጊስ ህዝብ ግንኙነት እንደ ክለብ ወደ ውድድር የየምንገባበት ለብሔራዊ ቡድን አስተዋፅኦ ማድረግ ቢሆንም በእቅዳችን መሰረት ስኬታማ ካልሆንን ተጫዋቾቻችን ሀገር አለመወከላቸው ያሳዝነናል ብሎ ሲያስታውቅ የቅድስተ ማርያም ኮሌጅ፤ የዳሸን ክለቦችም በደረሰው ጥፋት ያደረባቸውን ቁጭት ከገለፁት መካከል ይገኙበታል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው  ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ከላይ የተዘረዘሩትን የክለቦች አቋሞች በተመለከተ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ምላሾችን ሲሰጡ  ቡድን መስርተው እና በጀት መድበው ከሚሰሩ ክለቦችና ኃላፊዎቻቸው ጋር በቀጥታ ግንኙነት እያደረግን ለመግባባት  የምንችልባቸውን ሁኔታዎች እንፈጥራለን ብለው፤ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት የማያስፈልግ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በማያያዝ ሌላው የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ አበበ ገላጋይ በበኩላቸው ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት የሚቻለው በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት እንደሆነ ገልጸው አንድ ወይም ሁለት ክለብ ስለጠየቀ ሳይሆን ከጠቅላላ ጉባኤው አካላት ሁለት ሦስተኛው እንዲጠራ ከወሰኑ ብቻ ሊፈፀም የሚችል መሆኑን ሊያስገነዝቡ ሞክረዋል፡፡
በሌላ በኩል የስፖርት ሚዲያው በመግለጫው ካነሳቸው ጉዳዮች ዋንኛው በአጠቃላይ በስልጣን ላይ ያለው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በሴቶች እግር ኳስ በቂ ትኩረት አልሰጠም የሚለው ነበር፡፡ አሁን የታገዱት የቀድሞው የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ፌደሬሽኑን በመወከል፤ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የሴቶች ልማት ኮሚቴ አባልነት መመደባቸው፤ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ተሳትፎ ዙሪያ ከአራት ጊዜ በላይ ደብዳቤ ተልኮ በቂ ትኩረትና ምላሽ አለመሰጠቱ፤ በአጠቃላይ በፌዴሬሽኑ አመራር ውስጥ ሴቶች አለመኖራቸው ለደረሱት ጥፋቶች አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን የዳሰሱ ሃሳቦች በሁሉም ጥያቄዎች ተንፀባርቀዋል፡፡
በእነዚህ ሁኔታዎች ላይ ፕሬዚዳንቱ አቶ ጁነዲን ባሻና ሌሎቹ የስራ አስፈፃሚ አባላት በሰጧቸው ማብራሪያዎች በጥቅሉ ለሴቶች እግር ኳስ በቂ ትኩረት አልተሰጠም መባሉን አልተቀበሉትም፡፡ በአገሪቱ እግር ኳስ ታሪክ በሀ-20 ደረጃ ብሔራዊ ቡድን ተቋቁሞ እስከ ዓለም ዋንጫ ዋዜማ በማጣሪያ ውድድሮች መጓዝ መቻሉ፤ በሀ-17  በአገር ውስጥ ውድድሮች መካሄዳቸውና በአህጉራዊ ውድድር ተሳትፎ እንዲኖር መደረጉን የጠቀሱት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት፤ በዋናው ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ደግሞ የዋና እና  ረዳት አሰልጣኞች  ኃላፊነት ላይ ሴቶች መሾማቸው እንዲሁም የደመወዝ መሻሻሎች መደረጋቸው እንደውጤት መታየት አለበት ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ ይሁንና ካለፈው ሰሞን አስተዳደራዊ ጥፋት በኋላ ክለቦች በሴቶች እግር ኳስ ለመስራት ያላቸው ፍላጎት መቀነሱ፤ አንዳንድ ክለቦች ከወዲሁ ቡድኖቻቸውን እያፈረሱ መሆናቸውን፤ በጉዳዩ ላይ ጠበጠቅላላ ጉባኤ እንምከርበት የሚሉት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ሳይገኝባቸው  ተድበስብሰዋል፡፡
የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስተዳደራቸው የፈፀመውን ጥፋት በሦስት የተለያዩ ኃላፊዎች ላይ ብቻ በመጫን ለማለፍ መሞከራቸውና በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ በተደጋጋሚ የቀረበላቸውን ጥያቄ አልወደዱትም፡፡ ፌዴሬሽኑ አስተዳደራዊ ስህተት መሰራቱን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጠበት እና ጥፋት በፈፀሙት ሦስት ኃላፊዎቹ ላይ እርምጃ ከወሰደ በቂ ይሆናል ብለው ተሟግተዋል፡፡
ስልጣኑን በገዛ ፍቃዱ መልቀቅ እንደሌለበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባንፀባረቀው አቋም ያረጋገጠው የፌዴሬሽኑ ሥራ አመራር ከክለቦች ጋር በምን አይነት ሁኔታ እንደሚመካከር የወጣቶቹ ሉሲዎች ቡድን እስከ ዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያ በመጓዝ ላሳየው ጀግንነት ምን አይነት ማበረታቻና ማፅናኛ ለማድረግ ማሰቡን ሳይገልጽ ነው ያለፈው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በተሰጣቸው ኃላፊነት የፌዴሬሽኑ ሥራዎች በትክክል መከናወናቸውን ማረጋገጥ፤ የሥራ አስፈጻሚውን አባላት የማስተባበር የመምራት የመቆጣጠር ድርሻ ቢኖርባቸውም ይህን አለመፈፀማቸው በአንደኛ ደረጃ ተጠያቂ ሆነውበት ከሥልጣን መልቀቅ እንደነበረባቸው የስፖርት ሚዲያው ሊያመለክት ሞክሯል፡፡ ይሁንና ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጠው የፌዴሬሽኑ የሥራ አመራር በአጠቃላይ ያስተዳደር ችግር እንዳለበት ሥልጣን ልቀቁ ከማለት መዋቅሩ የሚስተካከልበትን ሁኔታ መመልከት አለብን በሚለው ማስተባበያቸው አቶ ጁነዲን ባሻ ሌሎቹ የስራ አስፈፃሚ አባላት  መግለጫውን አገባደውታል፡፡

Read 4375 times