Saturday, 07 November 2015 09:48

የጤና መድህኑ ህልም ሳይሆን ተጨባጭ ሀቅ ነው!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

      አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 20 ባወጣው እትሙ፤ ‹‹ህልምና ኑሮ ሲምታታ እንዲህ ነው - ከእውነት ዓለም ጋር የተላተመው የጤና ኢንሹራንስ!›› በሚል ርዕስ ዮሐንስ ሰ. የተባሉ ጸሃፊ አንድ ጽሁፍ ለንባብ አቅርበው ነበር፡፡ ጸሃፊው የጤና ኢንሹራንስ ጉዳይ አብከንክኗቸው፣ ተግባራዊነቱ ላይ ጽልመትና ጥላቻ የጋረደበት ትችታቸውን ቢሰነዝሩም ጉዳዩን እንደ ጉዳይ ማንሳታቸው በራሱ ሊያስመሰግናቸው ይገባልና በቅድምያ ላነሱት ርዕሰ ጉዳይ ልባዊ ምስጋናችንን በኤጀንሲው ስም ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡
እኛ እንደምንገምተው፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ነገሮችን በመረጃ አስደግፎ ለአንባቢ እውቀት የሚያስጨብጥ ጋዜጣ ነው፡፡ ሆኖም ዮሐንስ ሰ. (መረጃ ለማግኘት መሯሯጡ ዳገት ሆኖባቸው ነው መሰል) በወፍ በረር ስለ ጤና ኢንሹራንስ በሰሙት ወሬ ተደግፈው የጻፉት ጽሁፍ ትክክል ባለመሆኑ ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ተገደናል፡፡
በበቂ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ ጽሁፍ፣ ጸሃፊውንም ሆነ አንባቢውን ማምታታቱ አይቀርም። ዮሐንስ ሰ. ስለ ጤና ኢንሹራንስ ለመጻፍ ሲነሱ በቂ መረጃ ይዘው ስላልነበረ የጽሁፋቸውን ርዕስ ‹‹ህልምና ኑሮ ሲምታታ እንዲህ ነው!!›› ብለው ለመጀመር ተገደዋል፡፡ ሃቁን  ለመናገር ከእውነት ዓለም ጋር የተላተመው የጤና ኢንሹራንስ ሳይሆን መረጃን በበቂ ሁኔታ ባለማሰባሰብ ከገሃዱ ጋር የተላተሙት ራሳቸው ለመሆናቸው ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ የሚመስል የፈጠራ ስራቸው ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡
ጸሃፊው በመግቢያቸው ‹‹የቤተሰብዎን ጤንነት (ጥርስ ከማስተከል በቀር…) ሁሉም አይነት ምርመራ፣ህክምናና መድሃኒት ያገኛሉ - ነጻ ወይም ደግሞ 25 ብር ባልበለጠ የወር መዋጮ፡፡ ይህን ይመስላል መንግስት የጀመረው አስደናቂ የጤና ኢንሹራንስ›› በሚል የጤና ኢንሹራንሱ ምናባዊ የህልም ዓለም እንደሆነ ስላቅ አዘል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ጸሃፊው በምናባዊ ዓለም ውስጥ ሆነው በመጻፋቸው መንግስት ሃገሪቱ ውስጥ ለመተግበር ያቀደው የጤና መድህን ሁለት አይነት መሆኑን እንኳን ከሚያውቁ ሰዎች ለመጠየቅ ዕድል አልነበራቸውም። ዮሐንስ ሰ. ያልተገነዘቡት በማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓትና በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን መካከል ያለውን ልዩነት ነው። የማህበራዊ የጤና መድህን ማለት በመደበኛው ክፍለ-ኢኮኖሚ ለተሰማሩ (ደመወዝ ተከፋይ የሆኑ ሠራተኞች) 3%  ከደሞዛቸው  መዋጮ በማድረግ፣አሰሪያቸውም ተመሳሳይ ፐርሰንት እያዋጣላቸው ዜጎች ያልተጠበቀ ድንገተኛ ህመም ሲገጥማቸው ከኪስ የሚወጣ የገንዘብ ክፍያ ሳይኖር የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት የጤና መድህን ሥርዓት ነው፡፡ ይኸኛውን የመድህን ስርዓት መንግስት ገና በሃገሪቱ ተግባራዊ አላደረገውም።  በመጪው ጥር ወር ለመጀመር ቅድመ ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ እዚህ ጋ ጸሃፊው ባልተጀመረ ነገር አስተያየት መስጠታቸው ትዝብት ላይ ሳይጥላቸው አልቀረም።
ሁለተኛው የጤና መድህን ስርዓት ደግሞ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የሚባለውና መደበኛ ከሆነው ክፍለ-ኢኮኖሚ ውጭ በተለይም በግብርና ላይ ለተሰማሩ ዜጎች የሚያገለግልና ቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ ዓመቱን ሙሉ ያልተጠበቀ ህመም ሲከሰት የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ነው፡፡ ይሄም ቢሆን በአባላት መዋጮ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን እስከ 25 % በሚደርስ የመንግስት ድጎማ የተደገፈ ነው፡፡ ይህ የመድህን ስርዓትም ቢሆን ገና በሙከራ ደረጃ ላይ ያለና በሚታዩ ድክመቶች ዕርማት እየተወሰደ የማስፋፍያ ስራ የሚሰራበት ነው፡፡
እዚህ ጋ ጸሃፊውን ዮሃንስ ሰ.ን ለመጠየቅ የምንፈልገው ለመተቸት የፈለጉት ገና ያልተጀመረውን የማህበራዊ የጤና መድህንን ነው ወይንስ በሙከራ ትግበራ ላይ የሚገኘውን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓትን?...
በጽልመት ከታጀበው ጽሁፋቸው ለመረዳት እንደሞከርነው ጸሃፊው ‹‹የህልም ዓለም!›› በማለት ለመንቀፍ የሞከሩት የመድህን ስርዓት፤ ገና በሙከራ ትግበራ ላይ የሚገኘውን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓትን ይመስለናል፡፡ በእርግጥ የጸሃፊው ትኩረት በዚህ መድህን ስርዓት ላይ ከሆነ ሥለ መድህን ሥርዓቱ ምንም አይነት ግንዛቤ የላቸውምና ስለ ሂደቱ ጥቂት ማውጋቱ ለአንባቢ ትክክለኛውን መረጃ ከማቀበል ባሻገር ጸሃፊው ለሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይደግሙ አጋዥ እርምጃ ይሆናል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ኢትዮጵያ ውስጥ የሙከራ ትግበራውን የጀመረው ከዛሬ አራት አመት በፊት በአማራ፣በትግራይ፣ በኦሮምያና በደቡብ  ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልላዊ መንግስታት  በሰኔ ወር 2003 ዓ.ም ነበር - በ 13 ወረዳዎች ፡፡  በእነኚህ ወረዳዎች የተጀመረው የሙከራ ትግበራ፤ ጠንካራና ደካማ ጎን እየታየ በተደረገ የማስፋፍያ ሥራ በአሁን ሰአት ይህ የሙከራ ትግበራ ወደ 198  ወረዳዎች አድጓል፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ሂደቱ ከችግር የጸዳ ነበር ብለን ወገባችንን ይዘን አንሞግትም፡፡ የተወሰኑ ችግሮች እንደነበሩ መንግስትም ሆነ ሥራው የሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት በትክክል ይረዳሉ፡፡ ግን ደግሞ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም መልክዐ - ምድራዊ ችግሮች ባሉባት ሀገር አዲስ የሆነን ነገር  መሞከር ቀርቶ በረቀቀ ቴክኖሎጂ የሚታገዘው የናሳ ስፔስ ሺፕም ከስህተት የጸዳ ሊሆን እንደማይችል ለሁላችንም ግልጽ ይመስለናል፡፡
የሙከራ ትግበራው ያመጣውን ውጤት ከመዘርዘራችን በፊት የጤና መድህን ሥርዓትን በሃገራችን ለመተግበር ለምን አስፈለገ? የሚለውን መመለሱ ተገቢ ይመስለናል፡፡ ጸሃፊ ዮሃንስ ሰ. እንዳሉት ‹‹የህልም ዓለም ›› ለመፍጠር መንግስት በከንቱ ጊዜውንና ገንዘቡን ለማባከን ወይንስ የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት የሃገሪቱን የጤና ስርዓት ሌሎች ሃገሮች ወደሚከተሉት አቅጣጫ ለመምራት?
የጤና አገልግሎትን ማግኘት የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ይህ መብት እንዲከበር ደግሞ ሦስት ነገሮችን በሚዛናዊነት ሳይነጣጠሉ ማስኬድ ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ ሃብታም ከደሃ ሳይለይ ዜጎች ህመም ሲገጥማቸው አገልግሎት የሚያገኙበት መብት (Equity)፣ ሁለተኛ ዜጎች ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት የጤና አገልግሎት ( Quality Health Services )፤ ሦስተኛ አገልግሎቱን በጥራት መስጠት የሚያስችል የጤና ፋይናንስ ( Health Financing )፡፡ እነኚህ ሦስት ነገሮች የጤና አገልግሎት ለሚሰጡ አካላት አንድም ሦስትም ነገሮች ናቸው፡፡
እነኚህን ሦስት ነገሮች ማንጸርያ አድርገን የሃገራችንን የጤና አገልግሎት ስንቃኝ፣ መንግስት ለሁሉም ዜጎች ጤናን ለማዳረስ ጠንክሮ የመስራት ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህን ለመፈጸም የጤና አገልግሎት በሁሉም ክልሎችና ወረዳዎች ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት ደግሞ የጤና ተቋማትን በብዛት ከመገንባት ባሻገር በዘርፉ የተማረ የሰው ሃይል በማፍራት ላይ ይገኛል፡፡ ሦስተኛዉና ዋናው የጤና አገልግሎቱ የሚመራበት ፋይናንስ ነው፡፡
የኢትዮጵያን የጤና ፋይናንስ  ስንመለከት፣ 50 በመቶ የሚደጎመው ለጋሽ ሃገራት በሚሰጡን ድጋፍ ነው፡፡ ( አያድርገውና ይህ እርዳታ ድንገት ቀጥ ቢል ምን ያህል ምስቅልቅል እንደሚፈጠር መገመት አይከብድም)፡፡  የጤናው ዘርፍ የፋይናንስ ምንጭ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ከመንግስት ካዝና የሚገኘው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለጤና ዘርፍ ከሚውለው ጠቅላላ ወጪ 16 በመቶ  የሚሆነውን  ብቻ የሚሸፍን ነው፡፡ ቀሪው ደግሞ የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት በመስጠት ከሚያገኙት ገቢ የሚገኝ ነው።
በእርዳታ ላይ የተደገፈ የጤና ፋይናንስ ይዞ እስከመቼ? … እስከመቼ በልመና ዜጎቻችን ይታከሙ?.... ለጋሾቻችን ፊት ያዞሩብንና እርዳታቸውን ያቆሙ ቀን ምን ይዋጠን?... መልሱ ቀላል ነው፡፡ ተጨማሪ የጤና ፋይናንስ አቅም መፍጠር!! ይህን ለማድረግ ደግሞ አዲስ የጤና ፋይናንስ ስርዓት ለሃገሪቱ ማስተዋወቅ - የጤና መድህን ስርዓትን፡፡
በዓለም ላይ የጤና መድህን ስርዓት ከእድርና ከዕቁብ ቅርጽ ተላቆ  አሁን ያለውን መልክ ለመያዝ ወደ 700 ዓመታት በፈጀ ሂደት ውስጥ እንዳለፈ ታሪክ ያወሳል፡፡ ዘመናዊው የጤና መድህን አባት ግን  ቻንስለር ኦቶቫን ቢስማርክ የተሰኘው የጀርመን ቻንስለር እንደሆነና  እ.ኤ.አ. በ1883 ዓ.ም ያወጣው ህግ መነሻ መሆኑን ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
በቢስማርክ አርቃቂነት የተጀመረው የጤና ኢንሹራንስ፣ የተለያየ ቅርጽ ይዞ አተገባበሩም ከሃገራት፣ሀገራት እየተለያየ ዓለምን አዳረሰ፡፡ ዛሬ በተለያየ መልኩ የጤና ኢንሹራንስን ተግባራዊ ለማድረግ የማይፍጨረጨር ሃገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ የአፍሪካ ሀገሮችን ሁኔታ በምንመለከትበት ጊዜ ብዙዎቹ የምስራቅና የምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ እንደወጡ ይከተሉት የነበረውን የጤና አገልግሎትበማሻሻል የጤና አገልግሎትን በፍትሀዊነት ለዜጎቻቸው ለማዳረስ የተለያዩ የጤና መድህን ዓይነቶችን በመንድፍ ተግባራዊ አድርገዋል። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ሀገሮች መካከል ሩዋንዳ፤ ሴኔጋል፤ማሊ፤ኡጋንዳ፤ታንዛንያና፤ጋና ይገኙበታል። ሩዋንዳ የጤና መድህን ስልትን በመከተል እ.ኤ.አ እስከ 2007 ድረስ ከ9.5 ሚሊዮን ህዝቧ ውስጥ 5.7 ሚሊዮን የሚሆነውን በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በማካተት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች።
ሃገራችን ኢትዮጵያም  የጤና መድህን ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ በሙከራ ደረጃ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን በሙከራ ደረጃ በአራት ክልሎች በ198 ወረዳዎች በመተግበር ላይ ትገኛለች። ይህም በመሆኑ በሀብታሙና በድሀው እንዲሁም ከፍተኛ የጤንነት ችግር ያለበት የጤንነት ችግር ብዙም በሌለበት መካከል መረዳዳትና፣ መደጋገፍ እንዲፈጠርና  ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት  እንዲሰፍን ምክንያት እየሆነ መምጣቱ  ታይቷል ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሙከራ ትግበራው  ዜጎች የጤና አገልግሎት በሚሹበት ወቅት የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ክፍያ በመቀነስ አባላትና ቤተሰቦቻቸው ህመም ባጋጠማቸው ወቅት ህክምና እንዲያገኙ የሚያበረታታና የጤና አገልግሎት አጠቃቀምን እንዲጨምር የሚያደርግ ነው፡፡
ከዚህ ረገድ ካየነው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የሙከራ ትግበራ የተካሄደባቸው ወረዳዎች ካልተካሄደባቸው ጋር ሲነጻጸሩ የማህበረሰቡ የጤና አጠቃቀም ላይ መድህኑ ያመጣውን ለውጥ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ገለልተኛ በሆነ አማካሪ የተሰራውና ባለፈው ግንቦት ወር ለህትመት የበቃው የግምገማ ጥናት እንደሚያስረዳው የጤና መድህኑ በተተገበረባቸው ወረዳዎች የጤና አጠቃቀም ድግግሞሽ0.7 አድጓል፡፡ ይህም በሃገር አቀፍ ካለው አማካይ የጤና አጠቃቀም ( 0.34) አንጻር ሲታይ ትልቅ እድገት ነው፡፡
በአባላት ረገድም ካየነው እስከ ባለፈው ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም በአራቱም ክልሎች 1,344,055 ቤተሰቦች ወይም 6,504,146 ሰዎች አባል ሲሆኑ 2,214,557 ሰዎች ህክምና አግኝተው ወጪያቸው በመድህኑ ተሸፍኗል፡፡
እንግዲህ ይሄን ነው ጸሃፊ ዮሐንስ ሰ. ‹‹ የህልም ዓለም!›› በማለት ሊያጥላሉት የሞከሩት፡፡ አራት ዓመት ሙሉ የሚከሰቱ ድክመቶችን በማረም የጤና መድህኑን የሙከራ ትግበራ ከ 13 ወረዳ ወደ 198 ማድረስ ትግስትና እልህ አስጨራሽ ትግል እንጂ የ‹‹ህልም ዓለም›› የወለደው ቅዠት አለመሆኑን ያገኘነውና ያስመዘገብነው ውጤት ይመሰክራል፡፡
በስተመጨረሻ ዮሐንስ ሰም ሆኑ ሥለ ጤና መድህኑ የተሳሳተ አቋም ያላቸው ሰዎች እንዲገነዘቡልን የምንፈልገው ሃቅ፣ የሚሰጡን አስተያየት እንድንሻሻል ታስቦ ከሆነ ድክመታችንን በማረም የተሻለ የጤና ስርዓት በሃገራችን እንዲሰፍን ሌት ተቀን እንጥራለን፡፡ ህብረተሰቡ በጤና መድህን ሥርዓት ላይ ያለውን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ በጋራ ለመስራት እንዲሁም መረጃ ለመለገስ በራችን ምንጊዜም ክፍት ነው፡፡ ይሄ ሳይሆን ቀርቶ በተሳሳተ መረጃ ህዝብን ለማደናገር መሞከርና ሥራን ማደናቀፍ ግን ወንጀል ነውና ተጠያቂ ሊያደርግም ይችላል፡፡
በተረፈ በመጪዎቹ አምስት አመታት ውስጥ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን በመላ ሃገሪቱ ለመተግበር መንግስት እንደሚሰራ ልናረጋግጥልዎ እንወዳለን፡፡ እርስዎም ‹‹ከህልም ዓለም ›› ትችትዎ ወጥተው እውነቱን ለማየትና ሃቁን ለመጻፍ እንደሚበቁ ሙሉ እምነት አለን፡፡
ከኢትዮጵያ የጤና መድህን
ኮሚኒኬሽንና ሞቢላይዜሽን ዳይሬክቶሬት

Read 4431 times