Saturday, 07 November 2015 09:14

ኦሮሚያን በሃይል ለመገንጠል ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 21 ግለሰቦች ተከሰሱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

      በኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኞች የተፈረጀው ኦነግ አባል በመሆን ራሳቸውን በህዋስ በማደራጀት የኦሮሚያ ክልልን ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 21 ግለሰቦች ተከሰሱ፡፡
ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወ/ችሎት የቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፤ በተለይ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉት ኦላና ከበደ፣ ወልዴ ሞቱማና መገርሣ ፍቃዱ የተባሉት ግለሰቦች በመጋቢት 2007 ዓ.ም በአደአ፣ ቢርጋ ወረዳ ኦሎንኮሚ አካባቢ በሚገኘው በሩዴ ጫካ ውስጥ ተሰብስበው ሊቀመንበር፣ ም/ሊቀመንበርና ገንዘብ ያዥ በመምረጥ ራሳቸውን በሚገባ አደራጅተዋል፤ ይህን ስለማድረጋቸውም በወቅቱ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለሚገኘውና በዚህም መዝገብ ተከሣሽ ለሆነው አብዲሣ ኢፋ ሪፖርት ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡ በውጭ ሀገር ከሚገኘው የድርጅቱ አካልም አንድን ግለሰብ ለማስገደል የሚውል ገንዘብን ጨምሮ፣ ከቦንብ እስከ መትረየስ ግዥ የሚፈፀምበት ገንዘብ መቀበላቸውም በክሱ ተጠቅሷል፡፡ ጫካ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የድርጅቱ አባላትም ድጋፍ ያደርጉ ነበር ተብሏል፡፡
ተከሳሾቹ ወደ ኬንያ በመሄድ የተለያዩ ስልጠናዎችን መውሰዳቸውንና የወታደር ልብስና የተለያዩ ቁሳቁሶች በእጃቸው መገኘቱ ተጠቅሷል፡፡ ክሱ የቀረበበት ፍ/ቤትም  ክሱን በንባብ ለማሰማት፣ ለህዳር 7 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 3372 times