Saturday, 24 October 2015 09:59

የኋላ ቀር አስተሳሰብ ተጎጂዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

“ዎማኖዎች” ምህረት ጠየቁ፤ “ፉጋዎች” ይቅር አሉ

ገነት በሃድያ ተወልዳ ያደገች “ከምርጦቹ” የዎማኖ ዘር የተገኘች ኮረዳ ነች፡፡ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ለቤተሰቦቿ እየተላከች ያደገችው ገነት፤ እድሜዋ 16 ሲሞላ በአካባቢዋ ከሚኖር ሸበላ ጋር በፍቅር ወደቀች፡፡ እንደ አገሩ ወግና ልማድ የወንድ ጓደኛ ስትይዝ መጠንቀቅ ነበረባት፡፡ የዎማኖዎች የበታች አገልጋይና እንደ “ቆሻሻ” ከሚታዩት የ“ፉጋ” ማህበረሰብ አባላት ፍቅረኛ መያዝ እንደሌለባት ታውቃለች፡፡ ሆኖም ትኩረቷ ፍቅር ላይ ስለነበር ትዝ ሳይላት ቀረ፡፡
የወደደችው ወጣትም እንደሷ ቀልቡ ከጅሏት ነበር፡፡ በአንድ የተባረከች ቀን ወደ ወፍጮ ቤት ስትሄድ መንገድ ላይ ያገኛትና ልቡ እንደፈቀዳት ይነግራታል፡፡ ገነት አላቅማማችም፤ አጋጣሚውን በመጠቀም እሷም ሸበላውን እንደከጀለችው በድፍረት ነገረችው፡፡ እንዲህ እንደዘበት የተጀመረው የግርማና የገነት የድብቅ ፍቅር እየጎመራ፣ የማታ ማታ የብዙዎች መነጋገሪያ ሊሆን በቃ፡፡ መነጋገሪያ ለመሆን ያበቃው ጉዳይ ደግሞ የግርማ በዎማኖች እንደቆሻሻ ከሚቆጠሩት የ“ፉጋ” ማህበረሰብ መሆን ነው፡፡ የግርማ የሁልጊዜ ጭንቀትም “ፉጋነቴን ካወቀች ይህቺ ልጅ ትታኝ ትሄዳለች” የሚል ነበር፡፡
ፍቅራቸው መስመር ሲይዝ ግርማ፣ ፉጋነቱን ለገነት ሊነግራት ወሰነ፡፡ ግን በብልሃት መሆን ነበረበት፡፡ እናም የሆድ የሆዳቸውን በሚወያዩበት አንድ አጋጣሚ፤ “አሁን ከፉጋዎች ወገን የሆነ ወዳጅ ቢኖርሽስ?” ሲል ግርማ በሌላ አስመስሎ ጠየቃት፡፡ ገነትም ፈጠን ብላ “አይደረግም! እንዴት ይሆናል?” ስትል አፋጠጠችው፡፡ “እንግዲያውስ እኔ ፋጋ ነኝ” አላት፤ ያበጠው ይፈንዳ በማለት፡፡ ገነት የምትይዘው የምትጨብጠው አጣች፡፡
“እውነትህን ነው?”
“አዎ እውነቴን ነው፣ ምነው ደነገጥሽ? እኔና አንቺን ፉጋነቴ ሊያራርቀን ይችላል ማለት ነው? እኔም እኮ እንዳንቺው ሰው ነኝ፤ እይኝ እስቲ ማፍቀር የምችል እንዳንቺው ሙሉ አካልና የተሟላ ሰብዕና ያለኝ ሰው ነኝ” አላት
“ቢሆንም …” አለች ገነት
ግርማ የዋዛ አልነበረም፣ “በምናመልክበት ቤተክርስቲያን ‹ፉጋዎች ከዎማኖች እኩል ናቸው› የሚል ትምህርት ይሰጣል፤ እሱን ብትከታተይ የምልሽ የበለጠ ገባሳል” ይላታል፡፡
ገነት ብዙ አወጣች አወረደች፡፡ በአንድ ወገን ለወራት የገነባችው ፍቅር እንዳልነበር መሆኑ አሳሰባት፤ በሌላ በኩል የአካባቢው ባህል፣ የቤተሰቦቿ ጉዳይ ጭንቀት ሆነባት፡፡ በድንጋይ ተወግራ ሞት የሚፈረድባት ሁሉ መሰላት፡፡ በልጅነትዋ ስለፉጋዎች ቆሻሻነት እየሰማች አድጋ ዛሬ ፉጋ ወዳጅ ማበጀቷ እብደት መስሎ ታያት፣ ከሰው ሁሉ የበታች የሆነችም መሰላት፡፡
በዚያ ሀሳቧ ግን አልዘለቀችም፡፡ ከቀልቧ ሆና ጉዳዩን በቅጡ አሰበችው፡፡ የማታ ማታም ግርማ እንደነገራት፤ ቤተክርስቲያን ሄዳ የተባለውን ትምህርት ለመከታተል ወሰነች፡፡ በእርግጥም የሀይማኖት መሪዎቹ የሚያስተምሩት፤ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል መሆኑን ነበር፡፡ ሰው በራሱ ጊዜ የጌታና ሎሌ መደብን አበጅቶ አንዱ “ንፁህ ዘር”፣ ሌላው “ቆሻሻ ዘር” እየተባለ መኖር ያዘ እንጂ ሰው ሁሉ እኩል መሆኑን ከቤተክርስቲያኑ  ትምህርት ተገነዘበች፡፡ ይኼን ጊዜ በፍቅሩ የወደቀችለትን ጎረምሳ፣ በፉጋነቱ ብቻ ማጣት እንደሌለባት ወሰነች፡፡ “እኔን ከሱ የሚለይ አንዳች ምድራዊ ኃይል ሊኖር አይችልም” ስትልም ለራሷ ቃል ገባች፡፡
ይሄን ሁሉ ጉድ ቤተሰብ ሳይሰማ ነበር ወጣቶቹ የፍቅር ግንኙነታቸው ወደ ትዳር ለማሳደግ ከውሳኔ ላይ የደረሱት፡፡ በራሳቸው ፈቃድም በአንድ ጎጆ ስር መኖር ጀመሩ፡፡ የቤተሰቦቻቸውን በተለይም የገነትን ቤተሰቦች ይሁንታ ሳይሹ በአንድ ጎጆ ስር ከተጠቃለሉ ወራት አልፎ አመት ደፈኑ፡፡ በመሃል የልጃቸው መጥፋት ያሳሰባቸው የገነት ወላጆች፤ ልጃቸውን ማፈላለግ ጀመሩ፡፡ ፉጋ የማግባቷ ወሬ ከነሱ ጆሮ ደርሶ አበዱ፡፡ አንድ ቀን የቤተሰቧ አባል ገነትን አገኛት፡፡ የዚህ ሰው የመጀመሪያ ጥያቄ “እንዴት የቤተሰቡን ክብር የሚጎዳ ተግባር ትፈፅሚያለሽ?” የሚል ነበር፡፡ በተረጋጋ ስሜት ስለሁሉም ነገር አስረዳችው፡፡ እሱ ሆነ ቀሪዎቹ የቤተሰቦቿ አባላት ግን ሊሰሟት አልፈቀዱም፡፡ ምርጫ ቀረበላት፤ ወይ ከፉጋ ባሏ መለያየት አሊያም ሞት፡፡ ገነት ያለማቅማማት “ከሱ ከምለይ ሞት ይሻለኛል” አለቻቸው፡፡ “የእናንተንና የሱን ዘሮች የሚለያቸው ምንድን ነው? ሁላችንም ሰዎች ነን፤ እጅ፣ አፍ አይናችን ተመሳሳይ ነው፤ ታዲያ የእኛ ዘር ከነሱ የሚለየው በምንድን ነው? መቆሸሽ በውሃ ይጠራል፤ ሙያቸው ደግሞ ከነሱ አልፎ ለእናንተም ማጌጫችሁ ሆኗል፤ እስቲ ንገሩኝ እናንተ እንዴትና በምን ሚዛን ነው ከነሱ የበለጣችሁት? አስረዱኝ! እኔ ከሱ ከምለይ ሞቴን እመርጣለሁ” ገነት ለቤተሰቦቿ እቅጩን ነገረቻቸው፡፡ የልጃቸው የማይናወፅ አቋም ያስቆጣቸው ቤተሰቦቿ፤ ምንም እንኳን ትዳሩን ሙሉ ለሙሉ ባይቀበሉትም ጉዳዩን አለስልሰው መያዝን መረጡ፡፡ በዚህ መሃል ነበር ከፋጋና ከዎማኖ የተወለደው የጥንዶቹ የአብራክ ክፋይ እቺን አለም የተቀላቀለው፡፡ ዛሬ ገነትና ግርማ በሆሳዕና ከተማ የትዳር ህይወታቸውን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ የገነት ቤተሰቦች እምብዛም ባይዋጥላቸውም ከልጃቸው ጋር የግዳቸውን ተቀራርበዋል፡፡ ግርማ ከፉጋዎች በመፈጠሩ ከገነት ቤተሰቦች የደረሰበትን እስር፣ በደልና ግፍ ሁሉ ይቅር ለእግዚአብሔር ማለቱን አጫውቶኛል፡፡ ፉጋነት ግን ዛሬም በከንባታ ምድር “መረገም” ሆኖ ቀጥሏል፡፡
“ኬኤምጂ ኢትዮጵያ” የተባለ ድርጅትም ይሄን አስተሳሰብና አመለካከት ሰብሮ ማህበረሰቡን ለማቀራረብ ብዙ እየደከመ መሆኑን ይገልፃል፡፡
“ዎማኖ” እና “ፉጋ”
በከንባታ ምድር ከአንድ ብሄር የመጡ ሁለት ማህበረሰቦች አሉ፡፡
 የእነ ገነት ዘር የሆኑት ዎማኖዎች እና የግርማ ቤተሰቦች ዘር ፉጋዎች፡፡ ዎማኖዎች ንፁህ ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ የሚበሉት፣ የሚለብሱት፣ የሚሰሩት ፀዳ ፀዳ ያለውን ነው፡፡ ፉጋዎች በአንፃሩ የሸክላ እደ ጥበብና የተለያዩ የእንጨት ውጤቶችን በማምረት ይተዳደራሉ፡፡ የሁለቱ ማህበረሰቦች መገፋፋትና አንዱ የበታች የተጠላና የተገፋ፣ ሌላው የተከበረ ያደረጋቸው ይኸው የስራ መደባቸው መሆኑን የማህበረሰብ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር ኢዛና አምደወርቅ ይናገራሉ፡፡ ፉጋዎች በለቅሶና በሰርግ ከዎማኖች ጋር ቁጭ ብለው የማይበሉ ሲሆን የዎማኖችን ትርፍራፊ ብቻ ነው መመገብ የሚችሉት፡፡ እነሱ ባመረቷቸው የሸክላ ውጤቶች ዎማኖች ያሻቸውን ሲጠጡ፣ ፋጋዎች ግን በሰርግም ሆነ በለቅሶ ወቅት መጠጥ በእቃ አይቀርብላቸውም፤ በእጃቸው አሊያም በቅጠል ነው የሚጠጡት፡፡ የሚቀመጡትም ከቤት ውጪ ከዎማኖች ራቅ ብለው መሬት ላይ ሲሆን ዎማዎች እነሱ በጠረቧቸው ወንበሮች ላይ በነፃነት ኮርተው ይቀመጣሉ፡፡ መንገድ ላይ ከዎማኖች ጋር ሲተላለፉ፣ ፉጋዎቹ ጥሻ ውስጥ ተደብቀው ማሳለፍ አለባቸው፡፡ ዎማኖች ታመው የሞቱ ከብቶቻቸውን መቅበር ወይም ማቃጠል ሲገባቸው፣ ለፉጋዎች እንዲመገቡት ይሰጧቸዋል፡፡
ፉጋዎችም ይሄ ነገር ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው የመጣ በመሆኑ “አሜን” ብለው ከመቀበልና ዎማኖዎችን እንደ ምርጥ ዘር፣ የበላይ አድርገው ከመቀበል ውጪ ምንም አማራጭ የላቸውም፡፡ እንደውም ከዎማኖች እኩል ናችሁ ሲባሉ ለመቀበል ሁሉ ይቸገራሉ ይላሉ፤ የኬኤምጂ ኢትዮጵያ መስራች ዶ/ር ቦጋለች ገበሬ፡፡
ፉጋዎች አምላካቸው ፉና ይባላል፡፡ አምላካቸው ፉና የነገን ሳይሆን የዛሬን ብቻ እንዲኖሩ የሚያበረታታ በመሆኑ፣ ለነገ የሚቀመጥ ምግብም ሆነ ንብረት አይኖራቸውም፡፡ የሰማይ ወፎችን የመገበ አምላክ እኛንም ይመግበናል የሚሉት ፉጋዎች፤ ወፎች ለነገ አይሉም፤ እኛም ለነገ አንልም ይላሉ፡፡ በአጠቃላይ በፉጋዎች ዘንድ ቁጠባም ሆነ ገንዘብ መቋጠር ወይም ንብረት ማበጀት ጠያፍ ነው፡፡ የሚስትና የልጅ ገደብ አያውቁም፡፡ ስነ ተዋልዶ ከሚባለው ጉዳይ ጋር ጨርሶ አይተዋወቁም፡፡ አንድ ለአቅመ አዳም የደረሰ ፉጋ፤ 3 እና ከ3 በላይ ሚስት ማግባት መብቱ ነው፡፡ ሚስት መጨመር ሲያሻው እቤት ያሉት አይቃወሙም፡፡ ሴቶቹም አንድ ላይ ተከባብረውና ተዋደው ይኖራሉ፡፡ መቀናናት በፉጋ ባለትዳር ሴቶች ዘንድ አይታወቅም፡፡
አንድን የፉጋ አባወራ ጠጋ ብለው፤ “ስንት ልጆች አሉህ?” ቢሉት ጣቱን መቁጠር ይጀምራል፡፡ 10 ካለ በኋላ ግን “በመሀል የዘነጋኋቸውም ሳይኖሩ አይቀሩም” ሊል ሁሉ ይችላል፡፡ እኔም በአካባቢው ያነጋገርኳቸው አንድ አባወራ፤ የልጆቻቸውን ብዛት በውል እንደማያውቁ ነግረውኛል፡፡ ልጆችን ማስተማር ደግሞ የማይታሰብ ነው፡፡ እናስተምር ቢሉም የዎማኖ ልጆች እንዴት ከፉጋዎች ጋር ሊቀመጡ? የማይሆን ነገር ነው!!
ፉጋዎች አይታመሙም፡፡ ባለመድሃኒት ናቸው፡፡ ለዎማኖችም የመድሃኒት ምንጮች ናቸው፡፡ የማያውቁት የመድሃኒት አይነት የለም ይላሉ ዶ/ር ቦጋለች፡፡ ድሮ ድሮ ዎማኖች መድሃኒት ፈልገው እነሱ ጋ ሲሄዱ በጄ ብለው አይሰጧቸውም ነበር የሚሉት ዶ/ር ቦጋለች፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ማህበረሰባዊ መቀራረቡ እየተፈጠረ ሲመጣ ፉጋዎች መድሃኒታቸውን ለዎማኖዎች ማጋራት ጀምረዋል ይላሉ፡፡
“ፉጋዎች እኛም ሰው ነን አሉ”
ፉጋዎች “ሰው ሆነን ለምን እንደቆሻሻ እንታያለን” የሚለውን ጥያቄ ማንሳት የጀመሩት ኬኤምጂ ኢትዮጵያ የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት ቀርቦ ካወያያቸው በኋላ ነው፡፡ ለአንዳንድ የማህበረሰቡ አባላት “ከዎማኖች እኩል ነን” የሚለው አስተሳሰብ እብደት መስሎ ቢሰማቸውም ዛሬ ብዙዎቹ እየተለወጡ መጥተዋል ይላሉ፤ ዶ/ር ቦጋለች፡፡
“ዎማኖች የሚያገሉን ገላችንን ስለማንታጠብ፣ ሰካራም ስለሆንን፣ ለነገ የሚባል ህይወት ስለሌለን ነው” የሚል ማህበረሰባዊ ሂስ በራሳቸው ላይ ማድረግ የጀመሩትም ከሦስትና አራት ዓመታት በፊት ነው፡፡ ከማህበረሰቡ ትንሽ ፊደል የቆጠሩትና የሃገር ሽማግሌዎች ሰብሰብ ብለውም ኮሚቴ በማቋቋም ስለ ንፅህና አጠባበቅ፣ ስለ አመጋገብ፣ ስለ መጠጥ አጠቃቀምና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ሊመራበት ይገባል የሚሉትን ህገ ደንብ አወጡ፡፡ ዛሬ በዚህ ህገ ደንብ ታግዘው ማህበረሰባቸውን የማንቃትና ከበታችነት ስሜት የማላቀቅ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ ኬኤምጂ ኢትዮጵያ የተባለው ግብረሰናይ ድርጅት ደግሞ ድጋፍና ክትትል ያደርግላቸዋል፡፡
ቀደም ሲል ፉጋዎች ከዎማኖች ጋር መገበያየት አይችሉም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሳንቲም ከእጃቸው የሚቀበል አልነበረምና፡፡ ዛሬ ግን ነገሮች እየተሻሻሉ ነው ይላሉ፤ ዶ/ር ቦጋለች፡፡ ሱቅ ሄደው እንደ ማንኛውም ሰው እቃ መግዛት እየቻሉ ነው፡፡ ለትምህርት የደረሱ ህፃናት ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት እየላኩ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በልጆቻቸው ላይ መገለል አይደርስም ማለት አይደለም፡፡ በአካባቢው በነበረን ቆይታ ሁለት የዎማኖ እና የፉጋ ታዳጊ ልጆችን አነጋግረን ነበር፡፡ የዎማኖው ታዳጊ፤ “እንዴት ሆኖ ፉጋ ጓደኛዬ ሊሆን ይችላል … እነሱ እኮ እንደ ሰው አይደሉም” ሲል፣ የፉጋው ተወላጅ በበኩሉ፤ “እነሱ አያቀርቡንም … እኔ ከመሰሎቼ ጋር ነው ጓደኛ መሆን የምፈልገው” ብሎኛል፡፡ ዶ/ር ቦጋለች ግን ፉጋዎች እየተለወጡ ለመሆናቸው ሌላው ማሳያ ለነገ ማሰብ መጀመራቸው ነው ይላሉ ቁጠባን እየተለማመዱ መሆናቸውን በመግለፅ፡፡ መኖሪያ ቤታቸውን አሳምረው በቆርቆሮ መስራት ጀምረዋል፣ እድር፣ እቁብ የመሳሰሉ የማህበራዊ መስተጋብሮች አካል እየሆኑ ነው፣ የመምረጥና የመመረጥ እድላቸውን እየተጠቀሙ ነው፤ ወደ አምልኮ ቦታዎች እየሄዱም ከዎማኖዎች ጋር ቁጭ ብለው ፈጣሪያቸውን እያመለኩ ነው፡፡
እንዲህ ያለው ማህበረሰባዊ ለውጥ ከዘመናዊነት፣ ከትምህርት መስፋፋትና ከከተሜነት ጋር ተያይዞ መምጣቱ አይቀርም የሚሉት የስነ ማህበረሰብ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር ኢዛና፤ ፉጋዎችም ሆኑ በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ያሉ መገለል የሚፈፀምባቸው ማህበረሰቦች በጊዜ ሂደት ወደ እኩልነት መምጣታቸው እንደማይቀር ያምናሉ፡፡
የተገለሉ ማህበረሰቦች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አለም ሰለጠንን በሚሉት ሀገራት ሳይቀር እንዳሉም ረዳት ፕሮፌሰሩ ምሳሌ ጠቅሰው ያስረዳሉ፡፡ በህንድ፣ በላቲን አሜሪካና በአውሮፓ በእጅ ሙያ ጥበባቸው፣ በአመጋገባቸውና በአኗኗራቸው የተነሳ በሌላው ማህበረሰብ ዘንድ የሚጠሉ ማህበረሰቦች በርካታ ናቸው ይላሉ - ረዳት ፕሮፌሰሩ፡፡
ዎማኖች ምህረት ጠየቁ
በከንባታ ዞን ዋና ከተማ ዱራሜ ጥቅምት 6 ቀን 2008 ዓ.ም አንድም የመንግስት ተወካይ ባለስልጣናት ባይገኙም የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያን ጨምሮ የእስራኤል አምባሳደርና የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች በተገኙበት በተከበረው “የእጅ ወርቆች ቀን” (ፉጋዎች እጀ ወርቆች ተብለው እንዲጠሩ ተደርጓል፣ ፉጋ ማለት ከእንግዲህ ነውር ነው) ዎማኖች “እስከዛሬ ላደረስንባችሁ በደል ምህረት አድርጉልን” ሲሉ እጀ ወርቆችን በአንድነት ቆመው ጠይቀዋል፡፡ እጀ ወርቆችም በተራቸው ተነስተው፤ “ይቅር ብለናል፤ ከእንግዲህ አንድ ነን የሚለየን የለም” ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡ በከንባታ ምድር ከእንግዲህ ዎማኖ እና እጀ ወርቅ እኩል ይሁን ተብሏል፡፡ በከንባታ ዞን ብቻ ከ35-40 ሺህ የሚገመቱ እጀ ወርቆች መኖራቸውን መረጃዎች ሲጠቁሙ በተመሳሳይ በሀድያ፣ ወላይታ፣ ጉራጌና ሌሎች ብሄሮች ውስጥ በሸክላ ስራ፣ በእንጨት ስራ፣ በቆዳ ፋቂነትና በመሳሰሉ የእደ ጥበብ ሙያ የሚተዳደሩ “እጀ ወርቆች” ዛሬም ድረስ በሌላው ዘንድ እየተገለሉ እንደሚኖሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡   ዶ/ር ቦጋለች እና ድርጅታቸው ኬኤምጂ ኢትዮጵያም … እጀ ወርቆችን ከበታችነት ስሜት አላቆ ከሌላው ማህበረሰብ እኩል እንዲታዩ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት በከንባታ ምድር ብቻ ሳይሆን በአካባቢው በሚገኙ ሌሎች ማህበረሰቦች ዘንድም የማስፋፋት እቅድ አላቸው፡፡

Read 3449 times