Saturday, 24 October 2015 08:46

የቦክስ ስፖርቱን ለማነቃቃት በአዳዲስ አቅጣጫዎች እየተሰራ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

   የኢትዮጵያ ቦክስ ስፖርት ፌደሬሽን በ2008 ዓ.ም የገቢ አቅም በሚያጠናክሩ፤ ዓለም አቀፍ ተሳትፎን በሚያመቻቹ እና የክለቦችን ንቁ ተሳትፎ በሚያሳድጉ ውድድሮች ለመስራት ማቀዱን አስታወቀ፡፡  ባለፈው ሳምንት የቦክስ ስፖርት ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚዎች፤ የክለብ አመራሮችና የኢቢኤስ ቴሌቭዥን አመራሮች በሆቴል ዲኦሎፖል ባደረጉት ስብሰባ የ2007 ዓ.ም የውድድር ዘመን የገመገሙ ሲሆን የ2008 ዓ.ም የውድድር ዘመንን አካሄድንም አስታውቀዋል፡፡ የቦክስ ፌደሬሽኑ ባለፈው ዓመት በበላይነት ባካሄዳቸው ውድድሮች ላይ የታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጐኖች  የዳሰሰበትን ሪፖርትን ባቀረበበት ወቅት በተለይ የውድድር ቁጥሮችን ለማብዛት ትኩረት ማድረጉን አመልክቶ፤   ከኢ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን ጋር እና ሌሎች ስፖንሰሮችንም በመፈለግ በየሳምንቱ ወይም በየ15 ቀኑ ውድድሮችን ማድረግ እና የውድድር ልምድን መጨመር ያላቸውን አዳዲስ አቅጣጫዎች  አቅርቧል፡፡በስብሰባው በዋናነት የቦክስ ፌዴሬሽን ስፖርቱን ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት ብቸኛው የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ ከሆነው ከኢ.ቢ .ኤስ ቴሌቪዥን ጋር የሚሰራባቸው አቅጣጫዎች አበረታች መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን እና በኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ትብብር በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተካሂዶ የነበረው የአራተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ስኬታማነት ለቀጣይ ስራዎች ከፍተኛ መነሳሳት እንደፈጠረም ታውቋል፡፡ የኢቢኤስ ቴሌቪዥን  ባደረገው ሙሉ ድጋፍ   ባለፈው ዓመት ደማቅና
ልዩ ውድድር ለማድረግ የተቻለ ሲሆን የውድድር መድረኩ ስፖርቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ተችሏል፡፡በ2007 ዓ.ም አጠቃላይ የቦክስ ስፖርት እንቅስቃሴዎችን በገመገመው ሪፖርት ውድድሮች በታቀደላቸው ፕሮግራም መሰረት መከናወናቸው፤ ዳኞችና አሰልጣኞች  በመግባባት መስራታቸው፤ በውድድሮች ላይ የውጤት አገላለጽ መቀየሩንና በአዲስ  ሪንግ የመጨረሻውን ዙር ውድድር ማከናወኑን እንደጠንካራ ጎን አንስቶታል፡፡ በርግጥም የቦክስፌደሬሽኑ ባለፈው ዓመት ካከናወናቸው ተግባራት ከ50 ዓመታት በላይ ሲጠቀምበት የኖረውን ሪንግ በአዲስ፣ ዘመናዊ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቦክስ መወዳደሪያ መቀየሩ ትልቁ ውጤት ነበር፡፡ አዲሱን ሪንግ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ባገኘው የገንዘብ ርዳታ ለማሰራት ችሏል፡፡ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው የቦክስ ፌዴሬሽን ለመላ አፍሪካ ጨዋታዎችና ለ2016ቱ ኦሎምፒክ ተሳትፎ እንዲኖረው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡የቦክስ ስፖርት ፌዴሬሽኑ በመረጃ አያያዝ ድክመት እንዳለበት፤ የዳኝነት ስኮሪንግ ማሽን አለመኖር፤ በውጤት አሰጣጥ እና በዳኝነት የተወሰኑ ችግሮች መኖራቸው፤ የዳኞች፣ የስፖርተኞች እና የአሰልጣኞች ማህበራት አለመኖራቸው ፤ የደረጃ እድገት ሆነ ሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎችን በየጊዜው ለባለሙያዎች አለመሰጠታቸው፤ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ማነስ፤  ተወዳዳሪዎች በቂ ገንዘብ ለማግኘታቸው፤ ፕሮፌሽናል ውድድሮች በስፋት አለመካሄዳቸው እንዲሁም በቦክስ ስፖርት  የሴቶች ተሳትፎ ማነሱን ሪፖርቱ የገመገመ ሲሆን፤ በባለድርሻ አካላቱ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡በ2008 ዓ.ም የቦክስ ስፖርት ፌደሬሽን የውድድሮችን ቁጥር በማሳደግ፣ ስልጠናዎችን በመስጠት፣
አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማሟላት ከኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጋር በመሆን ለመስራት ተስማምቷል፡፡ የቦክስ ስፖርትን ከማሳደግ አልፎ የተወዳዳሪ ስፖርተኞች ህይወት በመለወጥ በስፖርት ኢንቨስትሜንት ስፖርት የራሳቸውንና የአገራችንን ኢኮኖሚ እንዲያሳድጉ ለማድረግ እንቀሳቀሳለን ያለው ፌደሬሽኑ፤ ክለቦች፣ የክልልና ከተማ የስፖርት ቢሮዎችና ፌዴሬሽኖች የጋራ ጥረት እንዲኖራቸውም ጥሪ አቅርቧል፡፡   በኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት ከተዋወቀ ከ85 ዓመታት በላይ መቆጠራቸውን አንዳንድ መረጃዎች ሲያመለክቱ ፤ የቦክስ ስፖርት ፌዴሬሽን የተመሰረተው ከ45 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡

Read 3116 times