Saturday, 17 October 2015 10:55

ሀገር! ሀገር! ማለት ምንድነው ትርጉሙ?

Written by  በሰለሞን አበበ ቸኮል (saache43@yahoo.com)
Rate this item
(9 votes)

መጽሐፍ፡- “ሀገርህን ጥላት ልጄ…”
ዘውግ፡- አጭር ልብወለድ
ደራሲ፡- በቴዎድሮስ አበራ
ገጽ፡- 274.00
ዘመን፡- ነሐሴ 2007 ዓ.ም”
ዋጋ፡- 50 ብር
ባለንበት የኢትዮጵያ ዘመን ውስጥ ተፈጥረውና ነፍስ አውቀው፣ ወደ ድርሰቱ ዓለም ከገቡ ጀማሪ ጸሐፊያን መካከል የዚች ሀገር ፖለቲካዊ ዕጣ - ፈንታ ክትት ብሎላቸው ያንኑ ደፈር ብለው በሥራዎቻቸው የሚያቀርቡ ሲገኙ ማስገረሙ የማይቀር ነው፡፡ በእርግጥም ‹የገባው፣ ነቄው…› እየተባለ በአራድኛው መጠራቱንም ያጸድቁለታል፡፡ “ሀገርህን ጥላት ልጄ” እና ሌሎች ልቦለዳዊ ትረካዎችን ይዞ ብቅ ያለው የቴዎድሮስ አበራ፤ አራት ቤሳ ልብወለዶች መድበል እንደነዚህ ያሉ የገባቸው ልጆች እንደሚወለዱ ማሳያ ምልክት ነው! ደግሞም፣ ደወልም ጭምር!
በእርግጥም “ሀገር ማለት” እና “ሰው ማለት…” የመለያያም ኾነ የመገናኛ ድንበራቸው የት ድረስ እንደሆነ ከነፍሱ የሚጠይቅ፣ ዘመን ወካይ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑንም ምልክት እየታየ ይሆን!? ያስብላል፣” ሲል አርታኢው ገዛኸኝ ፀጋው፣ ከቴዎድሮስ አበራ አራት ታሪኮች በፊት እንደመቅድመ ነገር ባሰፈረው ማስታወሻ ላይ የገለጸው ሐቅ ሐቅነቱ አይታበልም፡፡
በዚህ በአዲሱ ዘመን ጥቢ ወቅት አዲስ የቀረበው የወጣቱ ቴዎድሮስ መጽሐፍ የቤሳ ልብወለዶች መድበል ነው፡፡ ዐራት አጫጭር ትረካዎችን በአንድ አዳብሎ የያዘ፡፡ ምናልባት በሽፋኑ ያለመጮኽ የተነሳ ልናልፈው ካልቻልን፡፡ አዎን፤ የመጽሐፉ ሽፋን ዐይንን ለቀም አድርጎ የሚይዝ አይደለም፤የእርሱ ፊደላት ሳይቀሩ ያን ያህል ጎላ ጎላ ያሉ አይደሉም፡፡ ወደ መጥቆሩ መሄድ በጀመረ ሰማያዊ መደብ ላይ በፈዘዘ የቻይናው ቀይ ቀለም መጻፋቸውም እንዳይታዩ የበኩላቸውን አዋጥተዋል፡፡ ከሥር ያሉትን የደራሲው ስም እና ዓመተ ምህረቱንማ የግድ ፈልገው የሚያነቧቸው ናቸው፡፡
የሽፋን ሥዕሉ ከይዘቱ አንጻር ምን ሊባል እንደተፈለገበት ማሰብ ቢቻልም፣ ግራ የሚያጋቡ ነገሮችም አሉት፡፡ በቅድሚያ በውኃ ተለያይተው የሚታዩት ኹለቱ የብሶች፣ አንዱ ያንዱ የመስተዋት ምስል (ቅጂ) መስሎ መታየቱ ነው፡፡ የተፈለገው የተገነጠለች መሬትና የተገነጠለባትን ምድር ማሳየት ይመስላል፡፡ ሌላው ደግሞ የላይኛው የብስ ላይ ያለችው ሴትዮ፤ ቆማለች ወይስ በልቧ ተንበልብላለች? የሚል ጥያቄ የምትፈጥር ሆና መቅረቧ ነው፡፡
“ኧዲ ማለት ናታብ ህያብ…” የሚለው ነገረ ዓለሙ መለዋወጡን የሚያውቁት መናኚት እማይሆ ሃና ማርያም፤ በኤርትራ ዱር በረሃ ከሚገኘው ገዳማቸው ኹለቱን ዘማች ልጆቻቸውን ለመፈለግ ወደ አጋሜ ያመራሉ፡፡
ከኤርትራም ከትግራይም መንደሮች ከብቶቻቸውን አሰማርተው እየጨፈሩ የሚጠብቁ ልጆች ያዩበት በነበረ ሀገር፣ አንድም ዝር የሚል ሰው ባያዩም ከድሮ ጀምሮ በሚያውቁዋቸው ቀዬዎች እያለፉ፣ ወደ አዲሱ ድንበር ሲጠጉ ጀምሮ፣ በወያኔው “ድንበር” ጠባቂ መነጽር ውስጥ ገብተው ክትትል እየተደረገባቸው ነበር፡፡ ወደ አዲስ አበባ ደውሎ አንዲት አሮጊት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እየገባች መኾኗን ይገልጻል፡፡
 ወታደሮች ልኮ እንዲይዟት ካልሆነ፣ በጥይት ብለው እንዲደፏት ይታዘዛሉ፡፡ አዲሱን ድንበር ዐልፈው ሲገቡ በዋርድያዎች ተከበቡ፣ እማሆይ፡፡ ተያዙና በግርፋት ምርመራ ቁም ስቅላቸውን ያዩ ገቡ፡፡ ባለጌው የወያኔ ወታደር፤ “የሰው ሀገር አቋርጠሽ ስትመጪ ተይዘሽ፣ የሻዕቢያ ሰላይ አይደለሁም ልትይ?” እያለ ቢጠይቃቸውም፣ “የሰው ሀገር” ብሎ ነገር ሳይገባቸው፣ በስቃዩ እስከ ሞት ይደርሳሉ፡፡ ያን ቀጭን ትእዛዝ ከአዲስ አበባ ያስተላልፍ የነበረው ሹም፤ ለእማሆይ ምናቸው እንደነበሩ ሲታወቅ ነው የሚያሳዝነው፡፡
እንግዲህ፣ የሟችቱ የመጨረሻይቱ ጅምር ቃላቸው፣ “ኧዲ ማለት ናተይ ህታብ” ነበረች “ልጄ አገር ማለት ….” እንዳሉ በጥፊ በመመታቸው የተቋረጠ ቃል፣” ስትል በትረካው የገባችው ቃል መዝጋቢ መዝግባለች፡፡ ይሄኔ፣ ‹በለው!› ተብሎ፣ ሌላዋ ታሪክ አስመራ ላይ የኾነች ናት፡፡ በሻዕቢያነት የተጠረጠረ ወጣት፣ የደርግ ወታደሮች ከቤቱ አውጥተው እያዳፉ ሲወስዱት በማይገባ ውርደትና ጭካኔ ነበር፡፡ ለምን በአግባቡ ሳይረጋግጡት ይዘውት እንደማይሄድ የግደይ ባል ይናገራል፡፡ ጥይት እንካ ቅመስ ይሉታል፡፡
ፍግም ብሎ ይቀራል፡፡ ከዚያ ሬሳውንም ለመውሰድ የጥይት ካልተከፈለ ይባልና ግደይ የባሏን ሬሳም አታገኝም፡፡ ይህን ኹሉ ያልቻለውና የሚያውቀው ታደሰ የተባለው የደርግ ወታደር፤ ለዚች ሴት የምትከፍለውን ከፍላ የሚተርፋት ብር ደብቆ ይሰጣታል፡፡
“የኢትዮጵያ አምላክ ፍረደኝ” ስትል ግደይ ከልቧ አልቅሳለች፡፡ በታደሰ ልብም ይህ ተከትቦ ተቀምጧል፡፡ ስለ ጦርነቱም ሲጠይቅ ኖሯል፡፡ ታደሰ አገር እንዳትገነጠል ሊዋጋ የተሰለፈ ቢኾንም፣ የሚደረገው ነገር ኹሉ አልዋጥ ብሎት ሊከዳ ወሰነ፡፡ ግና ተያዘ፡፡
በመርማሪ ፖሊስ ምክርና እርዳታ ከመረሸን ተርፎ፣ ከእስር ቅጣት በኋላ ወደ ውጊያ ገባ፡፡ በመጨረሻ በደርግ ጊዜ ይዋጋ የነበረው ኢትዮጵያ ጦር ተመታ፡፡ ወታደሩ በየአቅጣጫው ተበተነ፡፡ ታደሰ የኤርትራ ገጠር ሰዎች እግሩን በጥይት መተውት፣ እየጎተተ በደረሰበት መንደር ማመን የማይቻል ዕድል አጋጠመው፡፡ ግደይ አገኘችው! በተራዋ ባለውለታዋን መንከባከብ ጀመረች፤ተዋደዱም፤ ተጋቡም፤ ተዋለዱም፡፡
በኋላ ከሀገር ውጡ የሚባልበት ጊዜ መጥቶ ያቺ ዕድለቢስ ሴት ይኼኛውን ባሏንም በሀገር ምክንያት አጣችው፡፡ ልጇ አድጎ፣ “ሀገር ማለት ምን ማለት ነው?” ብሎ በኮልታፋ አፉ የጠየቃት ጊዜ ምን ብላ ትንገረው? ስታስበው ትርጉሙን ከምትነግረው ይልቅ ይቺ ሀገር የምትባል ባሎቿንና የልጆቿን አባቶች የበላች ነገርን፣ እንዲጠላት አበክራ መከረችው፡፡
አገር አቋራጩ ወሎ ነፋስ ወደ ኤርትራ እና ትግራይ ይነፍሳል፡፡ ከአውሮፓዎቹ ሀገራት ከኢጣሊያና ከእንግሊዝ እየተነሳ ወደ ኢትዮጵያ ሌሎች አካባቢዎችም በመድረስ ያገኘውን ግሳንግስ እያግበሰበሰ፣ አሸዋውን እያቦነነ፣ በሚረብሸው ነፋስ ይቺ ምድር መመታት ከጀመረች ቆይታለች፡፡
“ነፋሱ ከየት ነው የሚነሳው?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አንዳንዶች፤ ከነዚህ ሁለት የአውሮፓ ሀገሮች ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ከራሱ ከቀይ ባህር ነው ይላሉ፡፡ ስለ መነሻው ከዚህ ወዲያ መጠቆምም አያስፈልገውም፡፡ በአካባቢው የሚነፍስ ኹሉ ከየት አቅጣጫ እንደሚመጣ በሚቃረን ጥቆማ ሰሜናዊ መነሻን የመስጠት ጉዳዩ ግን ሰምሯል፡፡
ተፈጥሮአዊነት ያለው መነሻ ይመስላል፡፡ የሞንሱን ንፋስ ከህንድ ውቅያኖስ ከደቡብ እየተጠቀለለ ወደ ላይ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሲዘልቅ፣ ቀይ ባህርንም ይዞ በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎች ዝናቡን አዝሎ ይገባል፡፡
ዋናው ነጥብ ግን ከየትመጣ አይደለም፡፡ መነሻው የትም ይሁን የት፣ “የኤርትራን ድንበር አቋርጦ የትግራይን ክልል ሳይቀር በአሸዋ ማዕበል መናጡ የተለመደው ግብ ሆኗል … “ ይላል፡፡
ንፋሱ በብዙ የአገሪቷ ግዛቶች በተለይ ተማረ በሚባለው ዘንድ መከሰት ከጀመረም ሰንበትበት ብሏል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና አካባቢው በር ላይ ያነሳው አቧራም መሬቱን ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባን ሰማይም ያጠቆረው ይመስላል (አጥቁሮታል ቢል ይመች ነበር)፡፡ እንደዚህ ያሉ ተምሳሌታዊ ውክልናዎች ያሉባቸው ስራዎችም ናቸው የቀረቡት፡፡ ዐራተኛው እና የመጨረሻው ትረካ በብዙ መሰረታዊ ጉዳዮች የሚለይ ከመኾኑም በላይ፣ ከዐራቱም ይልቅ ትንሽ በሰል ያለ ነው፡፡ በቅርጹ ከቤሳ ልብወለድነትም ይልቅ ወደ አጭር ታሪክነት ያደለ ይመስላል፡፡
ሌሎቹ እንዲያውም የረጅም ልብወለድ ቢጋሮች ዓይነት ናቸው፡፡ በቤሳ ልብወለድነት የተፈረጁና የሚፈረጁ ቢሆኑም፣ እንደገና ቢጻፉ ራሳቸውን የቻሉ ልብወለዶች መሆናቸው አይቀርም፣ እንደዚህ አንባቢ እይታ፡፡ የዚህ ያራተኛው ትረካ ርዕሱ “ሀገር የእጅ ሥራ” የሚል ነው፡፡ በአንድ ዕውቅና ድንቅ ደራሲ ሽማግሌ ላይ የተቀረጸችና የሰረጸች ሀገርን ያቀርብበታል፡፡
የ70 ዓመት ዕድሜ ያለው ሀገር ወዳዱ “ዕሩግ” ደራሲ፤ በአንድ ዓለም አቀፉ ጉባኤ ላይ ስለሀገር አንድ ጽሑፍ እንዲያቀርብ በአክብሮት ተጠይቋል፡፡ የ40 ዓመት ዕድሜ ያላት ሚስቱ ደግሞ ስለሀገሯ ያላት ግንዛቤም ይሁን ምስል ከርሱ የተለየ ብቻ ሳይሆን አሉታዊ የኾነም ነው፡፡ ያም ኾኖ በሥጋዊ ፍላጎትና ፍትወታቸው ተቻችለው ይኖራሉ፡፡
እንዲያም ሆነው  ከመቻቻሉ ሜዳ ወጥተው ሲናቆሩ እና ሲሸዋወዱም ይገኛሉ፡፡ ታዋቂው ደራሲ አስቀድሞ የሚያውቃትን ጥቁር ጠይም፣ “የበሰለ ወይን” መልክ ያላትን ሴተኛ አዳሪትንም እየፈለገ በፍትወት ይቃጠልባታል፡፡ እሷም ብልጭ እያለች፣ ከመኖርያ ቤቱ፣ ከመኝታ ቤቱ ድረስ በአካል ብቅ እያለች ትረብሸዋለች፡፡ ይከታተላታል፡፡ ሊያገኛት ይማስናል፡፡ በአደባባይ ስትሰስን፣ ከሌሎች ወንዶች ጋር ስትቃበጥ ኹሉ ትገኛለች፡፡ ወንዶቹም በአደባባይ እንደ ውሻ ሲናቆሩባት፣ እንደ አውራ ዶሮ ሲናተፉባት ኹሉ ያያል፡፡ እንደዚያም ኾኖ በፍቅሯ አብዶ ይዟታል፡፡ ከሚስቱና ቀድሞ ከሚያውቃት ከዚች ሴት ጋር ያለው ታሪክ እያደገ ባለበት ጉዞ ላይ ኹሉ ስለ ሀገሩ የሚያቀርበው ወረቀትም አብሮ ይጓዛል፡፡ እንዲሁ ሲያነሳው ሲጥለው በመጨረሻ ምንም ሳይዘጋጅ ከዕድሜው፣ ከንባቡ፣ ከዕውቀቱ፣ ሲያብሰለስለው ከኖረውም በቃሉ አንዲት ንግግር ማድረግ እንደማያቅተው ወስኖ በስብሳባው ይገኛል፡፡ ገና አትሮንሱን ይዞ እንደቆመ ግን፣ እንዲችው ስትበጠብጠው የኖረችው ያች የተቆላ ቡና መልክ ያላት ወዳጁ፤አዳራሹ ውስጥ ሰተት ብላ ስትገባ ያያታል፡፡ ያን ጊዜ ከፊቱ የተደቀነውን የድምጽ መቀበያ መከፈቱን እንኳ ዘንግቶት፣ “መጣች … መጣች ይች ሴተኛ አዳሪ! ዛሬ ደግሞ እንዴት ነው የለበሰችው” እያለ ይቀበጣጥራል፤ በድምፅ ማጉያው እየተሰማ፡፡ …..
ጥያቄ
በነዚህ ዐራት ትረካዎች ኹሉ ጥያቄዋ ሀገር ናት፡፡ የሀገር ምንነት፣ የዚህች ሀገር የምትባል ነገር ትርጉሟ የሚጠየቅባቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያው፤ “ቢያንጀቹ ማልጀቹን…?” ይላል፡፡ (ሀገር ማለት?----ቀጥሎ በእማሆይ አፍ በትግርኛ ይጠየቃል፡፡ ከዚያም በግደይ በኩል ትጠየቃለች፡፡ በመጨረሻ በታዋቂው ደራሲ እናም ከነዚህ በተቃራኒ በሚገኙት ገጸ ባሕርያት፡፡ ቴዎድሮስ አበራ ያለውን ምናባዊ ጥያቄም በተለያዩ ቦታዎች፣ በተለያዩ ሰዎች፣ በተለያዩ ታሪኮች እንዲጠየቁ እያደረገ፣ ስር ድረስ የሚመተልገውን የምናቡን እንቆቅልሽ እያበከረ ያቀርባል፡፡ በደቡብ በኩል ባሌ ውስጥ በአንድ የወያኔ ጎረምሳ፤ “ሀገርህ ግባ ….” የተባለው ጄኔራል ዋቆ (የቀድሞ ጀግና መኮንን) ሀገሩን አጥቶ፣ ሌት ተቀን አንድ ተራራ ሥር ባለ ዋሻ ውስጥ እንደ ንክ እየለፈለፈ፣ “ዕብድ ነው፤ ሰይጣን ለክፎት ነው” እየተባለ፣ “ሀገር አሳጥተው ሀገርህ ግባ ይላሉ፣” እያለ የሚኖር የትም የተጣለ ሆኗል፡፡ ይህም ሳያንስ፣ “ሀገርክን ፈልግ” ያለው ኃይል (ግለሰብ) በቅርብ በምትገኝ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪነት ተሹሞ (መምሬ ፈጠነ)፤ የርሱን ፍጻሜ ሊያቀርብ ህዝቡን ይዞ ሲያሴር ይገኛል፡፡ በእውነቱ ፍርሃትን አስወግዳ የተነጠበች ብዕር ናት - ቴዎድሮስ አበራ የያዛት፡፡ እንደርሱ ያለውን ጸሐፊ ሳያነብቡ እንዴት ይቀሯል?

Read 6614 times