Saturday, 10 October 2015 16:11

የመጽሐፍ ምዘና

Written by  ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም
Rate this item
(0 votes)

   ርዕስ ………….................ሌባሻይ
              ደራሲ …………...............ድርቡ አደራ
              የህትመት ዘመን ……….2007 ዓ.ም
              ዋጋ………………................ብር 80

        ደራሲው ይህንን ልብወለድ ለምን “ሌባሻይ” እንዳለው በግልጽ አይታይም፡፡ በመሠረተ ትርጉሙ “ሌባሻይ” ማለት ሌባን የሚፈልግ ማለት ነው፡፡ የሌባ መሻት ተግባር ይፈፀም የነበረው በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት እንደነበርና ሥርዓቱ የተሠረዘውም በልጅ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት እንደነበረ ይነገራል፡፡
በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ሆነ ከዚያ ወዲህ እስከዛሬው ድረስ በተግባር ውሎ አያውቅም፡፡ የተሠረዘውም (መድኃኒት በማጠጣት) እውነተኛ ሌባን ፈልጐ ለማግኘት አያስችልም፤ ንፁሐንን ሊኮንን ይችላል በሚል እምነት እንደነበረ ይገመታል፡፡
የድርቡ ልብወለድ የታሪኩ ጊዜ በሺ ዘጠኝ መቶ ሰባዎቹ ወይም ሰማንያዎቹ አካባቢ መሆኑ ከትረካው ሂደት ለመረዳት የሚቻል ሲሆን ለምን ይህን ዓይነት ርዕስ እንደተሰጠው ግልጽ አይደለም፡፡ ከቀድሞው የሌባሻይ ሥርዓትም ጋር ምን ዓይነት ተዛምዶ እንዳለው ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ በእርግጥ የታሪኩ ይዘት በአንድ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ላይ የተመሠረተ ቢሆንም የወንጀሎቹ አፈላለግ ዘዴ ከቀድሞው ሌባሻይ ወይም አውጫጭኝ (አፈርሳታ) በፍፁም የተለየና በዛሬው ዘመን የወንጀል ክትትል ዘዴ የተፈፀመ ነው፡፡
ምንም እንኳ የፖሊሱ ክትትል ገና ከመጀመሪያው መሆን ይገባው የነበረ ቢሆንም ከትረካ እንደምንረዳው ግን የፖሊስ ክትትሉ የሚመጣው ታሪኩ ለፍጻሜ ለመድረስ በተቃረበበት ወቅት ብቻ ነው፡፡
አሁን ወደ ይዘቱ እንዝለቅ፡፡ ሁለት ታዳጊ ወጣቶች፤ አንደኛው ከአዲስ አበባ ገዳም ሠፈር (ከጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በስተጀርባ)፣ ሁለተኛው ደሞ ከቢሾፍቱ ከተማ ተጠልፈው ወደ ከፋ ክፍለሀገር፤ እልም ካለ ገጠር ተወስደው ከባርነት በማይሻል ሁኔታ እንዲያገለግሉ ይደረጋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው የልጆቹን መጥፋት እንጂ የት እንደደረሱና በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖሩ፤ ጠላፊዎቻቸውም እነማን እንደሆኑ ፈፅሞ አያውቁም፡፡ ልጆቹ በሰቀቀን እንደሚኖሩ ሁሉ ቤተሰቦቻቸውም እንዲሁ የጭንቀት ሕይወት ነው የሚገፉት፡፡ የቢሾፍቱው ወጣት ለ8 ዓመታት፤ የአዲስ አበባው ደሞ ለ4 ዓመታት የባርነት ኑሮ ከኖሩ በኋላ በተለያየ መንገድ በመጨረሻ አርነታቸውን ይጐናጸፋሉ፡፡
የደራሲው መልእክት ምን እንደሆነ እያንዳንዱ አንባቢ እንደፈለገው ሊተረጉመው ቢችልም ዋና ዓላማው ግን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሕዝቡ እንዴት እንደሚኖር ለማሳየት ጥረት ያደረገ ይመስላል፡፡ ዋና ዓላማው ይህ ከሆነም ተዋጥቶለታል ለማለት ይቻላል፡፡ ስለእርሻው ከብት ርቢው፣ አደኑ፣ አምልኮው፣ የዕለት ተዕለት ኑሮው በዝርዝርና በግልጽ ተመልክቷል፡፡ አንባቢው ራሱ ከእነዚህ ገጠሬዎች ጋር አብሮ እየኖረ ሕይወታቸውን የሚጋራ ይመስለዋል፡፡ የገጠሩ ሕዝብ እንዴት ይገበያያል? እርስበእርሱ እንዴት ይጠያየቃል? የቀንዳም ቀንዳም ግለሰቦችና የሽማግሌዎች ሚና ምን ይመስላል? በሕብረተሰቡ መሐል ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች ምን ዓይነት አሰቃቂ ወንጀል ይፈጽማሉ? ጠንቋዩ፣ ባለአውሊያው የሕዝቡን መንፈስ የሚገዙት እንዴት ነው? ለእነዚህና ሌሎችም መሰል ጥያቄዎች መልስ የምናገኘው መፅሐፉን በማንበብ ነው፡፡ አንድ እጅግም ግልጽ ያልሆነ ነጥብ ግን እዚህ ላይ መጠቀስ አለበት፡፡ የአብዛኛው ትረካ ቦታ ከፋ ክፍለሀገር እልም ካለ ገጠር ውስጥ ነው፡፡ ሆኖም የሰው አኗኗር ከቤተ ጉራጌ ሕዝብ አኗኗር ጋር እጅግ በጣም የተቀራረበ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ ስለ እንስት ተከላው፣ ስለ ቆጮው ምግብነት፣ ስለ ክትፎው፣ እና ስለ ሌላ ሌላውም የሕዝቡ ባህልና አኗኗር በምናነብበት ጊዜ በሰባት ቤት ጉራጌ ወይም በሶዶ ጉራጌ እንጂ ከዚያ ውጭ ያለን አይመስለንም፡፡ ይህ ሊሆን እንዴት ቻለ?
በሌላ በኩል ግን በተለይም በወንጀል ድርጊት በኩል ያለው ሥርዓት ከዚህኛው በፍጹም የተለየ ነው፡፡ ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ በቤተ ጉራጌ ከሆነ ጉዳዩ የሚታየው በባህላዊ ሕግ (በጉራጌ ቅይጫ) እና በሽማግሌዎች አማካኝነት ሲሆን በከፋ ክፍለ ሀገር የምናየው ግን ከዚህ በፍጹም፣ በተለየ ሁኔታ ነው፡፡ በመጽሐፉ እንደተንደባረቀው ከሆነ፤ እንዲያውም ሕግና ሥርዓት ጨርሶ ያለም አይመስልም፡፡ ሁለት ግለሰቦች በግፍ ተገድለዋል፤ በትረካው ውስጥ፡፡ ነገር ግን ሕብረተሰቡ ምንም ዓይነት ርምጃ ሲወስድ አናይም፡፡ እንዴት ነው አንድ ሕዝብ ያለሕግና ሥርዓት የሚኖረው? በእርግጥ የነፍስ ግድያውም ሆነ የልጆቹ መጠለፍ በመጨረሻ እልባት የሚያገኘው በዘመናዊው የሕግ ሥርዓት (በፖሊስ ክትትል) ነው፡፡ ነገር ግን ሕብረተሰቡ ራሱ አንድ ዓይነት ባህላዊ ሕግና ሥርዓት ሳይኖረው እንዴት ቀረ ያሰኛል፡፡
የመጽሐፉ (የልብ ወለዱ) ጥንካሬ ግን በሁለት መልኩ ሊቀርብ ይችላል፡፡ 1ኛ/ ደራሲው ተዝቆ የማያልቅ የቃላት ክምችት እንዳለው ከዚህ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎ ከወጣው ከ”ሽምብሩት” መጽሐፉ ጭምር ለመረዳት ይቻላል፡፡ በመጽሐፉ የሚታዩት በጣም በርካታ እንግዳ ቃላት ለአንባቢው አስቸጋሪ ከመሆናቸውም በላይ አንዳንዶቹ በመዝገበ ቃላት እንኳ ሊገኙ የማይችሉ ናቸው፡፡ ከደራሲው አንጻር ስናየው፤ የቃላት ክምችቱ ከጥንካሬው አንዱ ቢሆንም ከአንባቢው አንጻር ግን “ምነው የቃላቱን ፍች በመጽሐፉ መጨረሻ ገጾች ላይ ቢያቀርብልን ኖሮ!” ያሰኛል፡፡
2ኛ/ እያንዳንዱን ድርጊት፣ እያንዳንዱን ሁነት፣ ገጸ ባህሪያቱ የሚጓዙበትን መንገድ፣ የአገሩን መልክአ ምድር፣ የአየሩን ሁኔታ፡- ዝናቡን፣ ጭቃውን፣ እሾህና አሜከላውን፣ የወንዛወንዙን ሙላት፤ የገጸ ባህሪያቱን ውጫዊና ውስጣዊ ምንነት፣ ወዘተርፈ በዝርዝር (ያለአንዳች ክፍተት) ፍንትው አድርጐ ስለሚያሳይ ፊልም የምናይ እንጂ መጽሐፍ የምናነብ አይመስለንም፡፡ የመጽሐፉ ገጸ ባህርያት እጅግ የበዙ በመሆናቸው ስለእያንዳንዳቸው መናገር ያስቸግራል፤ አስፈላጊም አይመስለኝም፡፡ በጉልህ ወጥተው የሚታዩት ግን ሁለት ናቸው፤ ዮሴፍና ዘነበች፡፡
ዮሴፍ ልበ ገር፣ ምንም ክፋት የሌለበት፣ ታዳጊ ወጣት፣ ሆኖ ሳለ ሊገመት የማይችል ግፍ ሲሠራበት እንታዘባለን፤ እናዝንለታለንም፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ለእሱ ስቃይና መከራ ምክንያት የሆነችው ዘነበች ወይም በሌላ ስምዋ ተዋበች ከጭካኔዋ የተነሳ “ሰው እስከዚህ ለመጨከን እንዴት ይቻለዋል?” የምታስብል እኩይ ገጽ ባህርይ ሆና ተስላለች፡፡ ከእሷ እጅግም በማይተናነስ ደረጃ እኩይ ገጸ ባህርያት ሆነው የቀረቡት ዘማዊትዋ ብሬና የአውሬ ባህርይ ያለው ዶዮ ነው፡፡
ከዚህ በላይ ስለገጸ ባህሪያቱም ሆነ ስለመጽሐፉ ይዘት ማተት ታሪኩን ማጨናገፍ ስለሚሆን የተቀረውን አንባቢው ራሱ አንብቦ ቢረዳው የሚሻል ይመስለኛል፡፡
በአጠቃላይ ግን ደራሲው ድርቡ አደራ ከአዲስ አበባ ጫጫታ፣ ከትርምሱ፣ ከመንገድ አደጋው፣ ከጢሱና ከመሳሰለው ሁሉ አውጥቶ ለተወሰነ ጊዜ የገጠሩን ንፁህ አየር እንድንተነፍስ፣ የገጠሩንም ሕይወት እንድንቀምስ ስላደረገን መመስገን ይገባዋል፡፡
ከአዘጋጁ
ከላይ የቀረበውን የመፅሃፍ ዳሰሳ ያቀረቡልን አንጋፋው ደራሲ ሳህለስላሴ ብርሃነማርያም ሲሆኑ ደራሲው በሦስት ቋንቋዎች፡- በጉራጊኛ፣ በእንግሊዝኛና አማርኛ በርካታ ሥነፅሁፋዊ ሥራዎችን ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ከሥራዎቻቸው መካከልም Shinega’s Village, The Afersata, Warrior King እና Firebrands የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እኚህ አንጋፋ ደራሲ ይህን የመፅሃፍ ዳሰሳ ለዝግጅት ክፍላችን ስለላኩልን በአንባቢያን ስም ከልብ እናመሰግናለን፡፡

Read 1851 times