Saturday, 10 October 2015 15:49

የኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ግንኙነት 40ኛ አመት እየተከበረ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 40ኛ አመት እየተከበረ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የህብረቱ አምባሳደር የሆኑት ቻንል ሄበሬች የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በብዙ ዘርፎቹ እየተጠናከረና እየጐለበተ እንደመጣ ጠቅሰው፣ ህብረቱ እርዳታ ከሚያደርግላቸው የአፍሪካ ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተቀምጣለች ብለዋል፡፡
ባለፉት 5 አመታት በየአመቱ በአማካይ ከ200 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ኢትዮጵያ የህብረቱ እርዳታ ተቋዳሽ ነበረች ብለዋል፡፡ በቀጣይ 5 አመታትም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕሮግራሞች ህብረቱ 745 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን አምባሳደሯ ጠቁመዋል፡፡ ህብረቱ ባለፉት 40 አመታት የኢትዮጵያን እድገት ለማገዝ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ መውጣቱን ያወሱት አምባሳደሯ፤ ከ15 አመታት ወዲህ ደግሞ በተለይ በድህነት ቅነሳ ከውጭ ምርቶች የሚገኝ ገቢን በማሳደግ፣ መሠረተ ልማትን በመገንባት፣ ዲሞክራሲያዊ ሂደትንና የሴቶች መብትን በማስጠበቅ እንዲሁም አካባቢያዊ ለውጦችን ለመግታት የሚደረጉ ስራዎችን በማገዝ ሰፊ ስራ መሠራቱ ተጠቅሷል፡፡ የአውሮፓ ህብረት በአሁን ወቅት የመንገድና ኢነርጂ ልማት፣ ጤና፣ ዘላቂ የግብርና ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃና የምግብ ዋስትና እንዲሁም በዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ይበልጥ አተኩሮ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየሠራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ግንኙነት በይፋ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1975 ሲሆን የ40 አመቱን ግንኙነት ለመዘከር በትናንትናው እለት በብሔራዊ ቲያትር የፖርቹጋል የሙዚቃ ዝግጅቶች እንዲሁም የሀገር ቤት ዳንሰኞች የተሳተፉበት የዳንስና የሠርከስ ዝግጅት ተካሂዷል፡፡ ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 4 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስም በተለያዩ የኪነጥበብና ስፖርት ማዕከላት የህብረቱ አባል ሀገራት ፊልሞች በነፃ ለተመልካች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡

Read 645 times