Saturday, 03 October 2015 10:31

የምሁራንን ክርክር ያጧጧፈው “እመጓ” መፅሀፍ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(15 votes)

      የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ነው “እመጓ” የተሰኘውን መፅሃፍ ምርቃት እንዲታደሙ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ትልቁ አዳራሽ መሰብሰብ የጀመሩት፡፡ አዳራሹ በምሁራን፣ በእምነት አባቶች፣ በመፅሃፍ አፍቃሪያንና በጋዜጠኞች ጢም ብሎ ሞልቷል፡፡ ከአዳራሹም ውጭ በሩና ኮሪደሩ በታዳሚዎች ተሞልቷል፡፡ በእለቱ በመፅሃፉ ላይ ሂስ ያቀረቡት ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራና ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ሲሆኑ በቅድሚያ ሂስ የሰጡት ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ነበሩ፡፡ በተፈቀደላቸው 25 ደቂቃ ውስጥ በመፅሃፉ መንፈሳዊ ይዘት ላይ ትንታኔያቸውን አቀረቡ፡፡ አወያዩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነፅሁፍ መምህሩ አቶ ወንደሰን አዳነ፤ በቀጣይ እድሉን ለዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ሰጡ፡፡
ዶ/ር በድሉም መፅሃፉ ልቦለድ ነው አይደለም፣ ትውፊታዊ ታሪክ ነው አይደለም፤ ታሪካዊ ልቦለድ ነው አይደለም የሚል አሻሚ ሃሳብ የተነሳበት በመሆኑ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ነው የጀመሩት፡፡ “የመፅሃፉ ደራሲ ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ እሸቴ፤ የሥነ-ምህዳርና የሥነ-ህይወት ተመራማሪ እንደመሆናቸው መፅሃፉ የምርምር ይዘት ያለው፣ ታሪካዊ ልቦለድ ቢሆንም፣ በመፅሃፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቦታዎች በእውን ያሉ ቢሆኑም፣ ገፀ ባህሪያቱ ኖረው ያለፉና የሚታወቁ ባለመሆናቸው ምርምርም ታሪካዊ ልቦለድም ሳይሆን ልቦለድ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የመጀመሪያውን መወያያ ያቀረቡት ዲያቆን ብርሃኑም፤ ሰፋ ያለውን ትንታኔያቸውን ከመንፈሳዊ ፋይዳው አንፃር ቢያቀርቡም፣ መፅሃፉ የጉዞ ማስታወሻም፣ የምርምር ውጤትም፣ ትውፊታዊ ፅሁፍም ይመስላል፤ ሆኖም በሚት (myth) የተሞላ የጉዞ ልብወለድ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር በድሉ በበኩላቸው፤ ምንም እንኳን መፅሃፉ የልብ ወለድ አፃፃፍ መሰረታዊያንን ባያሟላም ያነሳው ጭብጥ የተለየ መሆኑ ለአባቶች እውቀት ሚሰጠው ክብር መፅሃፉን እንዲያደንቁት እንዳደረጋቸው ገልፀው፤ በመፅሃፉ ላይ ያሉትን የአፃፃፍ ግድፈቶች እንደ ሥነ-ፅሁፍ ባለሙያነታቸው አንድ በአንድ ነቅሰው ሂሳቸውን በሚገባ አቅርበዋል፡፡
በእለቱ በእንግድነት የተገኙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የነበሩት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ “መፅሃፉ ልቦለድ ተባለ፣ ምርምር ተባለ ምን ፋይዳ አለው፡፡ የመፅሃፉ ፎርም ላይ ከምንሟገት ለምን የተነሳው ጭብጥ ላይ አናተኩርም” ሲሉ ዶ/ር በድሉን ከሞገቱ በኋላ፤ “ይህ መፅሃፍ አንደኛ “ፍሬሽ” ነው፤ ይህ ማለት አዲስና በድግግሞሽ ያልተሰለቸ ድንቅ ሃሳብ ነው፤ ሁለተኛ “ስትሬንጅ” ነው፤ ይህ ማለት የተለየ ሃሳብ ነው፤ በሌላ በኩል የሁለት አለም ወጐች የሚፋጩበት ነው፤ የኢትዮጵያ ጥናታዊ አስተምህሮና የምዕራቡ አለም ጉዳይ አለ፤ ይሄ ሁሉ ፋይዳ ሊያከራክረን ሲገባ እንዴት ልቦለድ ነው አይደለም በሚለው ላይ ጊዜ እናባክናለን ጐበዝ” ብለዋል፡፡
ዶ/ር በድሉ ጥያቄዎቹን ተቀብለው እንደጨረሱ፤ “ዶ/ር ዳኛቸው ፈላስፋ ስለሆነ ሃሳቡ ላይ ብቻ ነው ያተኮረው፤ እኔ ግን የስነ-ፅሁፍ ባለሙያ በመሆኔ የአፃፃፉ ሁኔታ፣ የገፀ ባህሪያት አወቃቀር፣ መቼቱ፤ በአጠቃላይ የመፅሃፉ ፎርም ስለሚያሳስበኝ በፎርሙም ላይ ያለውን ጉድለት ለመግለፅ እገደዳለሁ፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው ቢኖርና ምላሼን ቢሰማ ጥሩ ነበር” (ያኔ ዶ/ር ዳኛቸው ከአዳራሹ ወጥተው ነበር) በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አንድ ወጣት በሰጠው አስተያየት፤ “መፅሃፉ ልቦለድ ነው ብትሉም ልብወለድ አይደለም” አለ፡፡ ምክንያቱንም እንዲህ በማለት አስረዳ፤ “የ5 እና የ6 ዓመት ህፃን እያለሁ፣ መንዝ ውስጥ ደራሲውን ዶ/ር አለማየሁን አውቀዋለሁ፡፡ እንደውም በመፅሃፉ ላይ የተጠቀሰው ሲሳይ የተሰኘው ገፀ ባህሪ ራሱ ዶ/ር አለማየሁ ነው፡፡ የተጠቀሱትም አድባራትና ገዳማት አሁንም ያሉና በብዙ ቱሪስቶች የሚጐበኙ ስለሆኑ ልቦለድ ሊባል አይችልም” በማለት ንግግሩን ሲጨርስ፤ ዶ/ር በድሉ የወጣቱ አስተያየት “የዋህ አስተያየት ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ ሁሉ ክርክር አጠር ያለ ምላሽ እንዲሰጡ የተጋበዙት ደራሲው፤ ልክ ማይክ እንደጨበጡ “መፅሃፉን ከመፃፌ በፊት ባገኛችሁ ኖሮ ጭራሽ አልፅፈውም ነበር” በማለት ታዳሚውን በሳቅ አፍርሰውታል፡፡ “አሁን ግን ሁለተኛ መፅሃፌን እንዴት እንደምፅፍ አስተምራችሁኛል” ሲሉም አክለዋል፡፡ በእርግጥ መፅሃፍ ሙሉ በሙሉ ልብወለድ መሆኑን ከመግለፅ ወደኋላ አላሉም፡፡ መፅሃፉ በቤተሰብ ወጪ የታተመ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር አለማየሁ፤ ከታተመበት ሰኔ ወር 2007 ዓ.ም ጀምሮ 15 ሺህ ኮፒ መሸጡን ገልፀው፣ ከወጪ ቀሪ 200 ሺህ ብር እንዳስገኘና ይሄም ብር  መፅሃፉ ላይ የተገለፁት ገዳማት በፕሮጀክት መልክ እንዲጠናከሩበት በቼክ የሰጡ ሲሆን ከዚህም በኋላ መፅሃፉ ገበያው በፈለገው መጠን እየተተመነ በሚያስገኘው ገቢ እነዚሁ የገዳማቱ ፕሮጀክቶች እንዲታገዙበት መፅሃፉን ለማህበረ ቅዱሳን አስረክበዋል፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮም የመፅሃፉ ባለቤቶች ማህበረቅዱሳን ሆነዋል፡፡
በመጨረሻም የተሰማቸውን እንዲገልፁ እድል የተሰጣቸው አቡነ አብርሃም፤ “መፅሃፉን ጀምሬ ማቋረጥ ባለመቻሌ በአንድ ሌሊት ፈፅሜዋለሁ” ብለዋል፡፡ “ይህ መፅሃፍ በዘመናችን የሰው ልጅ የደረሰበትን የባህል ግጭት፣ የእምነትና የሳይንስን ፍጭት አጉልቶ የሚያሳይና ለእኛ ዘመን ትውልድ የተሰጠ የአዕምሮ ማረጋጊያ (Mental therapy) ነው” በማለት አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡
አቡነ አብርሃም አክለውም፤ አሁን አሁን እየተፃፉ ያሉ መፅሃፎች ምን ያህል አስደንጋጭና ፍጥጥ ያለ ነውር እንደሚያጋጥሟቸው ገልፀው፤ “እኔ ለምን ተፃፈ አልልም፤ ቢያንስ ግን ለምን ጠየም አያደርጓቸውም?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “እርግጥ እነዚህ አይነት መፅሀፎችን በነውር የተሞሉ ብዬ አልተዋቸውም፤ እያንገሸገሹኝም ቢሆን አነባቸዋለሁ፡፡ ይህ ደግሞ የማስተምረውን ትውልድ ስነ-ልቦናና ሃሳብ ለማወቅ ይረዳኛል” ብለዋል፡፡
በዶ/ር በድሉና በዲያቆን ብርሃኑ መሃል ተቀምጠው ሲያወያዩ የነበሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው አቶ ወንድወሰን አዳነ በበኩላቸው፤ “ለምን አትቆጣም” የሚል መፅሃፍን የተወሰነ ምዕራፍ በማንበብ፣ የቀድሞው ትውልድ የአሁኑን ትውልድ የሚወቅስበትን ሃሳብ የሚቃወምና የድሮውን ትውልድ የሚቆጣ ወጣትን ሃሳብ የሚገልፅ መሆኑን ተረድቻለሁ “እመጓ” መፅሃፍ ግን ለነዚህ ሁለት ትውልዶች መወቃቀስ ምላሽ የሚሰጥ ሚዛናዊ መፅሃፍ ሆኖ ይሰማኛል፤” በማለት የማጠቃለያ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ በዚሁ የመፅሃፉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓትና የውይይት ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡

Read 13205 times