Saturday, 26 September 2015 09:13

“...ካንሰርን በተስተካከለ የአመጋገብ ስርአት መከላከል...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ዮዲት ባይሳ/ ከኢሶግ
Rate this item
(5 votes)

 ካንሰር ማለት ጤነኛ የነበረ የሰው ልጅ ሴል ጤነኛ ወዳልሆነ ሁኔታ ሲለወጥ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ ሴል ስራውን በትክክል የማይሰራ፣ በትክክል የማያድግ ወደመሆን ሲለወጥ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጤነኛ የነበረው ሴል የሚኖረው ስራ ሲቋረጥ ወይንም  ከቁጥጥር ውጪ ሲራባ አለዚያም ሲያድግ እና ከጎረቤቱ ያለውን ሴል ስራና ጤንነት ሲበጠብጥ የሚፈጠረው በሽታ ነው ካንሰር ማለት፡፡ ካንሰር አንድ ቦታ ሲፈጠር እዛው በነበረበት ቦታ አይቆይም፡፡ ወደ ሳንባ ወደጉበት እና ወደሌሎችም የሰውነት ክፍሎች ይሄዳል፡፡ ወደተለያዩ የሰውነት አካሎች ከሄደ በሁዋላም እድገቱን በመቀጠል የሰውነት ክፍሎችን ይበጠብጣል፡፡ ባጠቃላይም ካንሰር እንደእብድ ሰው የሚቆጠር ሕመም ነው፡፡ አንድ ሰው እብድ ነው ሲባል የተፈጥሮ ሕግ በትክክለኛው መንገድ እንዲመራ ስለማያዙትና ሁሉንም ነገር እንደፈቀደው ከተፈጥሮ ስርአት ውጪ የሚከውን ሲሆን ሴልም ወደ ካንሰርነት ሲለወጥ በዚህ መልክ ሊገለጽ ይችላል፡፡ የካንሰር ሴሎች ቁጥራቸው መጠናቸው በተፈጥሮ ሕግ መሰረት ሳይሆን እንደተመቸው ይጨምራል፡፡ መስራት የሌለባቸውን ስራ ይሰራሉ፡፡ ከራሳቸው አልፈው ከጎረቤት ያለውን ሴል ይበጠብጣሉ፡፡ ይህ በእንግሊዝኛው Carcinogenesis በመባል ይታወቃል፡    
ዶ/ር አበበ ፈለቀ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል
የቀዶ ሕክምና    ባለሙያና አሲስታንት ፕሮፌሰር
ካንሰር የተባለው በሽታ ባህርይ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህንን ሕመም በአመጋገብ መከላከል ይቻላል የሚለውን መረጃ ከተለያዩ ጽሁፎች ማመሳከር የሚቻል ሲሆን ለዚህ እትም ግን ምንጭ ያደረግነው ዌብ ሜድ (WEB MED) የተሰኘውን ድረ ገጽ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ጽሁፍ ለካንሰር መከላከል ምቹ ናቸው የተባሉ ምግቦችን በሙሉ የሚጠቅስ ሳይሆን በመጠኑ እና በእለት ተእለት አኑዋኑዋራችን የምንጠቀምባቸውን የሚመለከት ነው፡፡
አንድ አይነት ምግቦችን አዘውትሮ በመመገብ ካንሰርን መከላከል አይቻልም፡፡ ይልቁንም የተለያዩ ምግቦችን በይዘትም ሆነ በአይነት አመጣጥኖ በመመገብ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ የገበታዎ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው ቅጠላቅጠል ቢሆን ይመረጣል፡፡ ከእንስሳት ተዋፅኦ የሚገኘው ፕሮቲንም ከገበታዎ አንድ ሶስተኛ በላይ መሆን የለበትም፡፡
እንደ አሜሪካ የካንሰር መከላከያ ተቋም ከሆነ የተመጣጠነ ምግብ ካንሰርን ለመከላከል አይነተኛ መሳሪያ ነው፡፡
አትክልትና ፍራፍሬን አዘውትሮ መመገብ፡-
አትክልት እና ፍራፍሬዎች  ካንሰርን ለመከላከል በሚያስችሉ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ሲሆኑ ቀለመ ደማቅ የሆኑ አትክልት እና ፍራፍሬዎች ለዚህ አይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምግቦች ሌላም ተጨማሪ ጥቅም አላቸው፡፡ አዘውትሮ አትክልት እና ፍራፍሬን መመገብ ጤናማ የሰውነት ክብደት እንዲኖረን ያደርጋል በዚህም ከልክ በላይ በሆነ የሰውነት ክብደት ሳቢያ የሚከሰቱ የካንሰር በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል፡፡
በፎሌት የበለፀጉ ምግቦች፡-  
እንቁላል፣ ሱፍ፣ ባቄላ፣ አባባ ጎመን እና ሌሎች አረንጓዴ ቀለም ያላቸው አትክልቶች በውስጣቸው ከፍተኛ የሆነ የብረት ንጥረ ነገር አላቸው፡፡ በምግብ ሰአት የብርቱካን ጭማቂ ሎሚ እና እንጆሪ የመሳሰሉትን መጠቀም በትልቁ አንጀት እና በአንጀቱ የታችኛው አካባቢ እንዲሁም በጡት ላይ የሚከሰተውን ካንሰር ሕመም ሊከላከል ይችላል፡፡ በመድሀኒት መልክ
ውሀ እንዲሁም ሌሎች ፈሳሾችን መውሰድ፡-
አብዝተን ውሀ በመጠጣት ጥማችንን ብቻ ሳይሆን የምናረካው እራሳችንን በሽንት ፊኛ ላይ ሊከሰት ከሚችል ካንሰርም መከላከል እንችላለን፡፡ ሌሎች ፈሳሾችንም አብዝተን በወሰድን ቁጥር ብዙ ቆሻሻ በሽንት መልክ ከሰውነታችን ስለሚወገድ ለሽንት ፊኛ ካንሰር የሚኖረን ተጋላጭነት በእጅጉ ይቀንሳል፡፡
ስኳርን መቀነስ፡-
ስኳር በቀጥታ የካንሰር በሽታን አያመጣም፡፡ ነገርግን በሰውነታችን ያለው የስኳር መጠን ሲጨምር ካንሰር ተከላካይ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን መጠን ይቀንሳል፡፡ በተመሳሳይ በሰውነታችን ያለው የካሎሪ መጠን እንዲጨምር እና ከልክ በላይ የሆነ የሰውነት ክብደት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ይህም ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች ያለንን ተጋላጭነት ይጨምራል፡፡ ስለዚህም ከስኳር ይልቅ በተፈጥሮ ጣፋጭ የሆኑ ፍራፍሬዎችን መመገብ ተመራጭ ነው፡፡
ጥቁር አረንጉዋዴ መልክ ያላቸው ቅጠላቅጠሎች፡-
እንደ ጎመን እስፒናች የመሳሰሉት ቅጠላቅጠሎች የአፍ፣ የሳንባ፣ የጣፊያ፣ የቆዳ እና የሆድ ካንሰር ሕመሞችን ሊከላከሉ እንደሚችሉ ጠበብት መስክረዋል፡፡
አልኮሆሎን መቀነስ፡-
በጉሮሮ፣ በአፍ፣ በድምጽ መተላለፊያ መስመር፣ በጉበት፣ በጡት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉትን የካንሰር ሕመሞች ለመከላከል የአልኮሆል መጠጥን መጠን መቀነስ ይገባል፡፡ አልኮሆል በአንጀት አንባቢም ለሚከሰተው ሕመም መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡
ባጠቃላይም የተጠቀሱትንና ሌሎችን ተመሳሳይ ምግቦችን በመመገብ ሕመሙን በመከላከል ረገድ ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡  
ካንሰር የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን የሚያጠቃ ሲሆን በተለይም ከሴቶች ጋር በተያያዘ ጡትና ማህጸን አካባቢ ይበልጡኑ ጎጂ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ የጡት እና ማህጸን ካንሰርን በተመለከተ አንዳንድ ነጥቦችን ለትውስታ ታነቡ ዘንድ ለህትመት አብቅተነዋል፡፡  
የጡት ካንሰር  
የጡት ካንሰርን ስንመለከት በእርግጥ ይበልጡኑ ተጎጂዎቹ ሴቶች ቢሆኑም ወንዶችም እንደሚታመሙ መረጃዎች ያመለክታ፡፡ ከ/100/ የጡት ካንሰር ታማሚዎች ውስጥ /90/ ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ ወንዶች /10/ ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ የጡት ካንሰር በብዛት የሚታየው ሴቶች ላይ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱም የጡት መጠኑ ሴቶች ላይ ትልቅ ሲሆን የወንዶች ጡት ግን ትንሽ እና በአይን የማይታይና በእጅ የማይዳሰስ በመሆኑ በካንሰር የመያዝ እድሉም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በጥቅሉ ትልቅ ጡት ያላቸው በካንሰር ሲያዙ ትንሽ ጡት ያላቸው ግን አይያዙም ለማለት አይደለም፡፡ ሴቶች በተፈጥሮአቸው ጡታቸው ላይ ብዙ ሴሎች የሚገኙ ሲሆን ወንዶች ግን እንደጡታቸው ማነስ ሴሎቹም ትንሽ ናቸው፡፡ የጡት ካንሰር ሲጀምር በጡት እና አካባቢው ቀድሞ ያልነበረ እብጠት ይታያል፡፡
የጡት ካንሰር ደረጃ አለው፡፡ ደረጃውም ከአንድ እስከ አራት ይከፈላል፡፡
1ኛ/ መጠኑ እጅግ ያነሰና በጡት ላይ ብቻ ያበጠ እጢ ነው፡፡ 2ኛ/ጡት ላይ ያለው እጢም አደግ ይላል፡፡ እንደገናም ብብት ስር እብጠቶቹ ሊዳሰሱ ይችላሉ፡፡ 3ኛ/ ጡት ላይ ያለው እጢም ትልቅ ሲሆን ብብት ስር እና ዙሪያውን ያሉት እጢዎችም በጣም ጠንካራ እና ያደጉ ሆነው ይዳሰሳሉ፡፡ 4ኛ/ ደረጃ የሚባለው የጡት ካንሰር ከጡትም ከብብት ስርም አልፎ ወደሌሎች የሰውነት ክፍሎች የተሰራጩ ሲሆን ነው፡፡  
ዶ/ር አበበ ፈለቀ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና                     ባለሙያና አሲስታንት ፕሮፌሰር
የማህጸን ካንሰር
የማህጸን ካንሰር አይነቱ እንደመብዛቱ መንስኤውም አንዳንዴ የሚታወቅና አንዳዴ  የማይታወቅ ነው፡፡ በአገራችን ሴቶችን በብዛት የሚያጠቃውና ገዳይ የሆነው የማህጸን በር ካንሰር መንስኤው ቫይረስ መሆኑ በሳይንስ የተረጋገጠ ነው፡፡ መንስኤያቸው በውል ካልታወቀው የማህጸን ካንሰር አይነቶች መካከል ከዘር ፍሬ (ኦቫሪ) ማፍለቂያ ከማህጸን ግድግዳና በአርግዝና የሚነሱ የካንሰር አይነቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጋር በተያያዘም እንደመንስኤ የሚጠቀሱት እንደ ውፍረት ደም ግፊት እና ስኩዋር ሕመም ያላቸው ሴቶች የማህጸን ግድግዳ ካንሰር  ያጠቃቸዋል፡፡ ብዙ ያልወለዱ እና በዘር አማካኝነት ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ደግሞ በዘር ፍሬ ማፍለቂያ ካንሰር ይጠቃሉ፡፡
በአጠቃላይ በከፍተኛ ሁኔታ ሴቶችን ይጎዳሉ ተብለው የሚታወቁት የካንሰር አይነቶች፡-
የማህጸን በር ካንሰር (Cervical Cancer) 80% ያህል በታዳጊ አገሮች ይከሰታል፡፡
የሴት ዘር ፍሬ ማፍለቂያ ካንሰር (Ovarian Cancer) ባደጉና ባላደጉ አገሮች ብዙ ልዩነት ሰያሳይ በተመሳሳይ ሁኔታ     ይከሰታል፡፡
ከማህጸን ግድግዳ የሚነሳ ካንሰር (Endometrial Cancer) በእድሜያቸው ገፋ ያሉትን ሴቶችን ያጠቃል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስፔሺያሊስት

Read 7991 times