Saturday, 26 September 2015 08:58

የመስቀል ደመራ ወዴት ወደቀ? እኛስ?

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(1 Vote)

    ነገ ደመራ ነው፤ ተነገ በስቲያ ደግሞ የመስቀል በዓል፡፡ “እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሰን” መባባል የወግ ነው፡፡ ጉዳዩ የመሚለከተን ሆኖ ሲገኝ የችቦ መዋጮአችንን ይዘን ነገ የሚተረኮሰው ደመራ ላይ ብርሃን ወካይ እሣታችንን እናዋጣለን፡፡ ቢመለከተንም ካላመቸን ደግሞ በየደጃፋችን ላይ ደጃፍ ወካይ ደመራ መተኮስ የሚያስችል አማራጭ አለን፡፡
እንግዲህ ነገ…
…ከሰአት በኋላ ደብርና አድባራት የሚወክሉ፡፡ ዲያቆናት ዝማሬአቸውን ይዘው ብቅ ይላሉ፡፡ ቀሳውስቱም ከሽብሸባ ጋራ ደምቀው ጐዳናውን ያደምቃሉ፡፡ ይሄ እለት የመስቀልን በዓል ባህሉ አድርጐ ለኖረ ማህበረሰብ ልዩ ትርጉም አለው፡፡ ለባዕዶችም እንዲሁ፡፡ ከአዲስ ባህል ጋር መተዋወቂያቸው ነው፡፡ አንዳንድ ባዕዳን ግን ይሄን ደማቅ የመስቀል በዓል ሥነ - ሥርዓት የሚወዱት አይመስልም፡፡ ለምሳሌ ሮማን ፕሮቻዝካ የተሰኘ ጀርመናዊ ጋዜጠኛ ጽፎት ደበበ እሸቱ የተረጐመው “ኢትዮጵያ የባሩዱ በርሜል” የተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ የሚል ነገር አንብቤአለሁ፡-
“ኦብዘርቫቶር ሮማኖ የተባለ የህትመት ውጤት እንኳን በእውነት በጣም ቀና በሆነ አመለካከትና ትዕግስት በሰፈነበት ሁኔታ ስለ ኃይማኖታዊው ሥርዓትና ኋላቀር ስለሆነው የአገልጋዮች ሁኔታ መፅሐፍ አውጥቷል፡፡ ያንን ንፅህና የጐደለውንና ማይማን የሆኑት የጉባኤ አባላት ክምችት የሚያቀርቡትን ከዚያ ኋላቀር ከሆነው ዳንሳቸው ጋር አረመኔያዊነትና የመናፍስት አምልኮ ቅልቅል የሆነውን ባህል እንዴት “የሃይማኖታዊ ሕብረተሰብ ባህላዊ ሀብት” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል”
የፕሮቻዝካ አስተያየት የንፁህ አእምሮ ፍርድ እንዳልሆነ የምናውቅ እናውቀዋለን፡፡ ይሄ ሰው በጋዜጠኝነት አገራችን ገብቶ በሰላይነት ሲያገለግል በመገኘቱ ተይዞ የተባረረ ነው፡፡ በእምነት ሥርዓታችን ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ላይ ያለው ድምዳሜ የጥላቻና የበቀል ፍላጐትን ያንፀባረቀ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ እሱን ትተን ወደ ደማቁ በዓላችን እናዝግም፡-
እንግዲህ ነገ የምናከብረው የደመራ በዓል ማስታወሻነቱ ለንጉስ ቆስጠንጢኖስ እና ለእናቱ ለንግሥት እሌኒ ኃይማኖታዊ ተግባር ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቸነከረበት ሥፍራ መስቀል ከተቀበረበት ሥፍራ በቁፋሮ እንዲገኝ ሁኔታውን ያመቻቸች ንግሥቷ ነበረች፡፡ ከሦስት መቶ አመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ሥፍራው ቆሻሻ መጣያ ሆኖ በመቆየቱ ደብዛ አልነበረውምና ንግሥቲቱ ግራ ቢገባት ደመራ አስደምራ አንድ ዳውላ እጣን ጨመረችበት፡፡ የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ አርጐ ቁልቁል በመውረድ መስቀሉ የሚገኝበትን ትክክለኛ ሥፍራ ጠቆመ፡፡ በዚህ ጥቆማ መሰረት ግማደ መስቀሉ በቁፋሮ ተገኘ፡፡ ነገ ይሄን እለት ደመራ በመደመር እንዘክራለን፡፡ “ኢዮሃ አበባዬ!” እንላለን፡፡
ደመራው የቀሳውስት ድግ ታጥቆ፤ በሽርጉዳችን የኰራ መምሰሉ የግድ ነው፡፡ እስኪለኮስ ድረስ በጊዜያዊ ማጊያጊያጫ ባንዲራ ይታጠቃል፡፡ አደይ አበባ ይጐናፀፋል፡፡ ዝማሜውን በአርምሞ ይቃኛል፡፡ አመሻሹ ላይ መኰፈሱና አበባ መጐናፀፉ አብቅቶ እሳት ይተኮሣል፡፡ ሆታ እና እልልታ ከደመራው ቀድሞ ይጋያል፡፡ ኦሆሆሆሆይ! እናንተን ቱሪስት ማድረጌ ነው ይሄን ሁሉ የምዘበዝበው? አንዳንዴ እንዲህ ነው፡፡ የኖቤል ተሸላሚ ሕንዳዊውን ባለቅኔ ራቢንድራናት ታጐርን የሆንኩ መሰለኝ፡፡ ታጐር አንድ ቅኔ አለችው፡፡ “ጊታንጃሊ” ሲል ሰይሟታል፡፡ የዚች ቅኔ ግብ ተፈጥሮን መተንተን ነው (ተፈጥሮ ለኛ ባዕድ የሆነች ይመስል) እናም ዛፉን፣ ፀሐዩን፣ ቢራቢሮውን፣ አበባውን፣ አየሩን…እያማለለ! ያቀርብልንና ቅኔውን ሲቋጭ “እ-ህ? ምን እኔን ፈዘህ ታደምጣለህ? ውጣና እራስህ ተመልከተው እንጂ” ይላል፡፡ እንዲያ ነው፡፡ የእኔም ድርጊት የደመራን ሥነ - ሥርዓት እየዘገቡ እዚያው ላለው ሰው ማቅረብ መሰለ፡፡ ይሁን!
ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ወደሆነኝ ርዕሰ ጉዳይ ላምራ…
…ደመራ መተኰሱ ከጨለማ ዘመን ወደ ብርሃን መሸጋገራችንን የሚዘክር ብቻ አይደለም፡፡ መጪው ዘመን እንዴት ያለ ባህርይ እንዳለው መተንበያ ጭምር ነው፡፡ መጀመሪያ ደመራው ነዶ ካለቀ በኋላ ዝናብ የሚያጠፋው ከሆነ እንደመልካም ገጠመኝ ይቆጠራል፡፡ “እሰይ፣ እሰይ” ይባላል፡፡ መጪው ጊዜ ላይ ተስፋ ይጣላል፡፡
ደመራው ነዶ ከማለቁ በፊት ደግሞ አወዳደቁም ሌላው ትንበያ ነው፡፡ የደመራው አወዳደቅ አቅል መጪውን ጊዜ የሚተነብይ ተደርጐ ይወሰዳል፡፡ ከደመራው በስተደቡብ ቆመን ወደ ሰሜን ስንመለከተው፣ በስተቀኛችን (ወደ ምሥራቅ) ከወደቀ፣ መጪው ጊዜ ጥጋብና ሰላም ነው ይባላል፡፡ እንዲያ ሳይሆን ቀርቶ ደመራው በስተግራችን (ወደ ምዕራብ) ከወደቀ የጨፍጋጋ ዘመን መጠቆሚያ ነው፡፡ ረሃብና ጦርነት በጨካኝ እጆቻቸው ያስተናግዱናል፡፡
ታገል ሰይፉ “ቀፎውን አትንኩት” ሲል እንደገጠመው ያለ ነው፡፡ የሰው ልጅ በመጪው ጊዜ ላይ ያለው ተሳትፎ ተቀጥቦ የተሰጠውን መቀበል ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሰላምን በማምጣት፣ ጦርነትን በማስቀረት፣ ጥጋብን በማስፈን፣ ረሃብን በማስወገድ በኩል የሰው ልጅ ድርሻ አልተቸረውም፡፡ እንደ አራስ ልጅ ተንጋሎ ከመሣቅና ከማልቀስ ውጭ ነገሮችን እንደሚመቸው አድርጐ የመለወጥ ብቃትም ሆነ ሐላፊነት የለውም፡፡ ተቀጥቦ የተሰጠውን ይቀበላል እንጂ ቢወጣ ቢወርድም ጦርነቱ አይቀርም፤ በጠላትነት ተነስቶ ቦምብ ቢያከማችም፣ ቢጠመድም፣ ቢያፈነዳም ሰላሙ አይስተጓጐልም፡፡ ሺህ ምንተሺህ ትራክተር ጠምዶ ቢያርስም፣ እርዳታ ተቀብሎ ቢያከማችም የተባለው ረሃብ አይቀርም፡፡ ደግሞም የተመረተውን ሁሉ እሳት ውስጥ ቢማግድም አንዴ ደመራው ወደ ቀኝ ወድቋልና ጥጋቡ ግድ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ደመራ ነክ ትንበያ፣ ለማህበረሰብ ትልቅ ጫና ሳይኖረው አይቀርም፡፡ የሰው ልጅ መጪውን አይቶ ካላመለጠ፣ አዘናነቡን ተመልክቶ ካልተጣለለ፣ እጥረት ሰግቶ በቁጠባ ካልዳነ… ምኑን የሰው ልጅ ሆነው? የመጣው እንደመጣ እያወቀ ዝም ብሎ ከጠበቀ ምኑን ከእንስሳ ተለየው? የደመራ አወዳደቅ እንደ አዝማሪ ግጥም አቀባይ “ተቀበል” ያለንን ካዘመርን አደጋ አለው፡፡
ከመስቀል ደመራ ባሻገር የመስቀል ዶሮ እርድንም እንደዚያው መጪውን ጊዜ ተንባይ አድርጐ የሚወስድ የህብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ አራጁ ፊቱን ወደ ሰሜን መልሶ ሲባርክ፣ የዶሮው አወዳደቅ እንደ ደመራው ሁሉ ፊቱን ወደ ምሥራቅ አዙሮ በግራው፣ ክንፉ በኩል ከሆነ፣ ጥጋብና ሰላም ይሰፍናል፡፡ በተቃራኒው ከሆነ ደግሞ እንዲሁ ዕጣ - ፈንታችን እንደተጣመመ ይቆጠራል፡፡
ምልኪ የዘመናዊ ህዝብ መተዳደሪያ ሊሆን እንደማይገባው እሙን ነው፡፡ “እንዲህ ስለሆነ እንዲህ ይሆናል” የሚል ምልኪ ከተፈጥሮ ጋር በቅጡ የማይተዋወቅ ጭፍን ሕዝብ አሚነ - ስብከት ነው፡፡ የእንዲህ ያሉ ምልኪዎች ጅማሬ ከክርስቶስ ልደት በፊት አምስት መቶ ዘመን አስቀድሞ ወደኖረው ግሪካዊ ፈላስፋ ፓይታጐረስ ይወስደናል፡፡ ፓይታጐረስ ከተጠይቃዊ አስተሳሰብ ባሻገር መላቅጣቸው የጠፋ የምልኪ ትዕዛዛትን ለደቀመዛሙርቱ አስተላልፎ ነበር፡፡ እርሱ እንደሚለው፤ መጪው ጊዜ እንዲሰምር መደረግ የሌለባቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አተርን ጠርጥሮ መብላት፣ ነጭ አውራ ዶሮን ማረድ፣ መስቀለኛ ብረት መርገጥ፣ አበባን መቀንጠስ፣ በባዶ አውራ ጐዳና መዘዋወር፣ ከመኝታ ሲነሱ የገላን ሰንበር ከአልጋ ምንጣፍ ላይ እንዳለ መተው፣ ከቤት ሲወጡ ግራ እግርን ማስቀደም… ፈጽሞ የተከለከሉ ነበሩ፡፡ ነገሮች ወደ መጥፎ አዝማሚያ የሚሄዱት በእነዚህ ነገሮች መከናወን እንጂ በሌላ እንዳልሆነ አስረግጦ ያስተምር ነበር፡፡ እህስ? የእኛ ደመራና የዶሮ ዕርድ ከዚህ ምልኪ አይመደብ ይሆን? …፡፡ እስኪ ለማንኛውም እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሰን ብለን እንለያይ፡፡
  

Read 1182 times