Saturday, 19 September 2015 09:41

ውይ ህዝብ!

Written by  ደራሲ - አንቶን ቼኾቭ ትርጉም - ቅዱስ ገዛኸኝ
Rate this item
(5 votes)

  “ይሄው፤ ከመጠጥ ጋር ተቆራረጥኩ! ምንም…ም…ን…ም ነገር ከእዚህ በኋላ ወደ እሱ አይመራኝም፡፡ እራሴን ለመቆጣጠር ጊዜው አሁን ነው፤ በርትቼ መስራት አለብኝ…ደሞዝ ሲከፈልህ ደስተኛ ነህ፤ ስለዚህ እንቅልፍ ምቾት ሳትል በሀቀኝነት፣ ከልብህና በጥንቃቄ መስራት ይገባሀል፡፡ መለገም አቁም! ሳይሰሩ ደሞዝ መውሰድ ለምደሀል፤ ይህ ደሞ ወዳጄ…ትክክል አይደለም…በጭራሽ ትክክል አይደለም…”
ይህን የመሳሰሉ ትምህርቶችን ለራሱ ከሰጠ በኋላ፣ ዋና ትኬት ተቆጣጣሪው ፖድቲያጊን፣ ሊቋቋመው የማይችለው የስራ መነሳሳት ተሰማው፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ያለፈ ቢሆንም ትኬት ተቆጣጣሪዎቹን ቀስቅሶ፣ በባቡር ፉርጐዎቹ ውስጥ ከእነሱ ጋር ወዲያ ወዲህ እያለ ትኬቶችን መፈተሽ ጀመረ፡፡
“ት..ት…ት..ትኬት….እ..እ…እ…እባካችሁ!” የትኬት መቁረጫዎቹን እያማታ መጮኸ ያዘ፡፡ የፀሐይን መጥለቅ ተከትሎ በቀረው ጭላንጭል ብርሃን ውስጥ የተደበቁ፣ እንቅልፍ የጣላቸው የፊት ገፆች ሁሉ አናታቸውን እየነቀነቁ ትኬታቸውን ማቀበል ጀመሩ፡፡
“ት…ት…ት…ትኬት…ይቅርታ!” እያለ ፖድትያጊን በፀጉራም ኮትና በአልጋ ልብስ እንዲሁም በትራስ የታጠረውን፣ ኩስምን ያለ የሁለተኛ ማዕረግ ተሳፋሪ ያናግር ጀመር፡፡ “ይቅርታ፤ ትኬት!”
ጣረ ሞት የመሰለው ሰውዬ መልስ አልሰጠም፡፡ እንቅልፍ ውስጥ ሞቷል፡፡ ዋና የትኬት ተቆጣጣሪው የተሳፋሪውን ትከሻ በቀስታ መታ መታ አደረገና ትዕግስት በማጣት ተናገረ፡፡
“ት..ት..ት…ትኬት….እ…እ…እ…እባካችሁ!”
ተሳፋሪው ፖድትያጊን ላይ አይኑን አፈጠጠበት፡፡ “ምን?...ማነው?...ኸ?”
“ግልፅ በሆነ ቋንቋ ነው የተጠየቁት፤ ት..ት…ት…ትኬት……እ…እ…እ…እባክዎን!
ጣረ ሞት የመሰለው ሰውዬ፣ የስቃይ ፊት አሳይቶ “የፈጣሪ ያለ!” ሲል አቃሰተ፡፡ “የአምላክ ያለ! በቁርጥማት እየተሰቃየሁ…ሶስት ሌሊቶችን አልተኛሁም! ለመተኛት ስል አሁን ገና ነው ማደንዘዣ የዋጥኩት፤ አንተ ደግሞ እዚህ… ትኬት! ምህረት የለሽነት ነው፤ ሰብዓዊነት ማጣት ነው! መተኛት ለእኔ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ብታውቅ ኖሮ፣ በዚህ በማይረባ ነገር አትረብሸኝም ነበር…ጭካኔ ነው፤ ከንቱ ነገር ነው! ምንድነው ከትኬቴ የምትፈልገው! የማይረባ ነገር ነው!”
ፖድትያጊን መልስ መስጠት እንዳለበትና እንደሌለበት ያስብ ጀመር፤ ከዚያም መልስ መስጠት እንዳለበት ወሰነ፡፡ “ይሄ መጠጥ ቤት አይደለም፤ አትጩህ!”
“በጭራሽ፤ መጠጥ ቤት ውስጥ ሰዎች የተሻለ ሰብዓዊ ናቸው…” ተሳፋሪው አሳለ፡፡ “ምናልባት ሌላ ቀን እንድተኛ ትፈቅድልኝ ይሆናል! ተዓምር ነው! ብዙ ውጭ ሀገራት ተጉዣለሁ፤ ማንም ትኬት ብሎኝ አያውቅም፤ አንተ ግን ሰይጣን የላከህ ይመስል ደግመህ ደጋግመህ…”
“ውጪ ከተመቸህ እዛ መሄድ ነዋ!”
“ጅልነት ነው ጌታዬ! አዎ! ተሳፋሪውን በጭስ፣ በታፈገ አየርና በብርድ መግደላችሁ ሳያንስ በህግና ደንብ ልታንቁት ነው፤ እንጦሮጦስ ግቡ! ትኬት እንደሆነ አለው፤ የአምላክ ያለህ! ምንድነው እንዲህ ማስጨነቅ! ለድርጅቱ የሚጠቅመው ቢሆን ጥሩ…ይሄኔ ግማሹ ተሳፋሪ ያለ ትኬት ነው የሚጓዘው!”
“ይስሙ ጌታዬ” ፖድትያጊን በብስጭት ጮኸ፡፡ “መጮህና ህዝቡን መረበሽ ካላቆሙ፣ በሚቀጥለው ጣቢያ ላስወርዶት እንዲሁም ስለሁኔታው ሪፖርት ለማድረግ እገደዳለሁ!”
“የሚያሳፍር ነገር ነው!” ሲል ‹ህዝቡ› በንዴት ተናገረ፡፡
“የታመመን ሰው ማሰቃየት ምን ይጠቅምሃል … ኧረ ትንሽ ተመልከትና እስቲ ርህራሄ አድርግ”
“ሰውዬው እራሱ ተሳዳቢ ነው’ኮ” ፖድትያጊን ትንሽ ፍርሃት ገብቶት ተናገረ፡፡
“ጥሩ…ትኬቱን አልወስድም…ደስ እንዳላችሁ…እርግጥ ነው፣ በደንብ እንደምታውቁት ይህንን ማድረግ ግዴታዬ ነበር…ግዴታዬ ባይሆን ኖሮ ጥሩ…የባቡር ጣቢያውን ተቆጣጣሪ ጠይቁ…የምትፈልጉትን ሰው ጠይቁ…”
ፖድትያጊን ትከሻውን በምንግዴነት ሰብቆ ከበሽተኛው ራቀ፡፡ መጀመሪያ ላይ ትንሽ ቅሬታና መጐዳት ተሰምቶት ነበር፡፡ ሁለት ወይም ሶስት ፉርጐዎችን ካለፈ በኋላ ግን የትኬት ተቆጣጣሪው ሆዱ የማያውቀው የሆነ አይነት አለመረጋጋት ተሰማው፡፡
“በሽተኛውን መቀስቀስ አስፈላጊ አልነበረም” ሲል አሰበ፡፡ “ምንም እንኳ የኔ ችግር ባይሆንም…ያለ ምክንያት፣ በግድየለሽነት ያደረግሁት መስሏቸዋል፡፡ ግዴታ አለብኝ…ካላመኑኝ፣ የባቡር ተቆጣጣሪውን አመጣላቸዋለሁ፡፡”
ባቡር ጣቢያ ደረሱ፡፡ ባቡሩ ለአምስት ደቂቃ ቆመ፡፡ ሶስተኛው ደውል ከመደወሉ በፊት፣ ፖድትያጊን መጀመሪያ ወደገባበት ሁለተኛ ማዕረግ ፉርጐ ገባ፡፡ ከኋላው ቀይ ኮፍያ ያደረገ የባቡር ጣቢያ ተቆጣጣሪ ተከትሎታል፡፡
“ይህ እዚህ ጋ ያለ ሰው” ፖድትያጊን ጀመረ፤ “ትኬቱን መጠየቅ እንደማልችል ተናግሯል…ስለጠየኩትም ተበሳጭቷል፡፡ እባክዎን እርሶ ተቆጣጣሪ ስለሆኑ እንዲያብራሩለት እለምናለሁ…ጌታዬ፤ ትኬት የጠየቅኩት በደንቡ መሰረት ነው ወይስ እራሴን ለማስደሰት?” ፖድትያጊን ጣረሞት የመሰለውን ሰውዬ ያናግረው ጀመር፤ “ጌታዬ፤ ካላመኑኝ የጣቢያ ተቆጣጣሪውን ይጠይቁት”
ታማሚው የተወጋ ያህል አይኑን አፍጥጦ በድንገት ተነሳ፤ ወዲያው የስቃይ ፊት አሳይቶ ወንበሩ ላይ ሰመጠ፡፡ “የአምላክ ያለ! ሌላ ኪኒን ውጬ ትንሽ ሸለብ ሲያደርገኝ፣ አንተ ደግሞ እንደገና እዚህ…እንደገና! ልለምንህ፤ ትንሽ እራራልኝ!”
የባቡር ጣቢያ ተቆጣጣሪውን መጠየቅ ይችላሉ…ትኬትዎን መጠየቅ እንደምችል ወይም እንደማልችል”
“ይህ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ነው! ውሰድ ትኬትህን …ውሰድ! በሰላም እንድሞት ከፈቀድክልኝ አምስት እጥፍ እከፍላለሁ! ታመህ አታውቅም? ጨካኞች!” “ይህ ግፍ ነው!” የወታደር የደንብ ልብስ የለበሰ ግለሰብ መበሳጨት ያዘ፡፡ “ለዚህ ንዝንዝ ምንም ማብራሪያ ላገኝለት አልችልም፡፡”
የባቡር ጣቢያ ተቆጣጣሪው በብስጭትና የፓድትያጊንን እጀታ እየጎተተ፤ “በቃ ተው …” አለ፡፡ ፓድትያጊን በምናገባኝነት ትከሻውን ሰብቆ፣ የባቡር ተቆጣጣሪውን ተከትሎ ቀስ ብሎ ማዝገም ጀመረ፡፡
“እነሱን ማስደሰት አይቻልም” ሲል፣ በግራ መጋባት አሰበ፡፡ “ለራሱ ስል ነው የባቡር ተቆጣጣሪውን ያመጣሁት፤ እንዲያስረዳው ብዬ እንዲሁም እንዲረጋጋ፤ ነገር ግን እሱ … ተሳደበ!”
ሌላ ጣቢያ ደረሱ፡፡ ባቡሩ ለአስር ደቂቃ ቆመ፡፡ ሁለተኛው ደውል ከመደወሉ በፊት፣ ፓድትያጊን በመዝናኛ ባር ውስጥ ቆሞ የጠርሙስ ውሃ እየጠጣ ሳለ፣ ሁለት ግለሰቦች ወደ እሱ መጡ፤ አንደኛው የኢንጅነር የደንብ ልብስ የለበሰ እና ሌላኛው የወታደር ካፖርት፡፡
“እየውልህ፤ የትኬት ተቆጣጣሪ!” ኢንጅነሩ ፖድትያጊንን ያናግረው ጀመር፡፡ “ለበሽተኛው ተሳፋሪ ያሳየኸው ባህሪ፣ ተመልካች የነበረውን ሰው ሁሉ አሳፍሮታል፤ ስሜ ፑዝትስኪ ይባላል፤ ተሳፋሪውን ይቅርታ ካልጠየክ፣ የትራፊክ ማናጀሩ ጓደኛችን ስለሆነ ቅሬታችንን ለእሱ እናቀርባለን፡፡”
“ጌቶች! ለምን ግን እኔ … ለምን ግን እናንተ …” ፖድትያጊን ደነገጠ፡፡ “ማብራሪያ አንፈልግም፡፡ ነገር ግን እያስጠነቀቅንህ ነው፤ ይቅርታ የማትጠይቅ ከሆነ፣ ጉዳዩን ወደ ህግ ፍርድ እንዲያገኝ እናደርጋለን፡፡” “በእርግጠኝነት እኔ … ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ በእርግጠኝነት …. ለማረጋገጥ …”
ከግማሽ ሰዓት በኋላ፣ ፖድትያጊን የራሱን ክብር ሳያዋርድ ተሳፋሪውን ይቅርታ የሚጠይቅበትን ቃላቶች መርጦ ወደ ፉርጎው ተጓዘ፡፡ “ጌታዬ” በሽተኛውን ጠራው፤ “አድምጠን ጌታዬ ….”
በሽተኛው ነቃና ተስፈንጥሮ ተነሳ፡- “ምንድነው?”
“እኔ … ምን ነበር? …. መበሳጨት አይገባህም …”
“ኡኽ! ውሃ …” በሽተኛው ልቡን ይዞ ቃተተ፡፡ “ሶስተኛ ማደንዘዣ ውጬ እንቅልፍ ሲወስደኝ … እንደገና! የአምላክ ያለ! መቼ ነው ይሄ ስቃይ የሚያቆመው!”
“እኔ የመጣሁት … ይቅርታ ….”
“ኦኽ! … በሚቀጥለው ጣቢያ አውርደኝ ከእዚህ በላይ አልችልም … እኔ መሞቴ ነው …”
“ይህ ጭካኔ ነው፤ አሳፋሪ!” በብስጭት ‹ህዝቡ› አላዘነ፡፡ “ዞር በል! ለእዚህ ግፍህ ትከፍላለህ፡፡ ዞር በል!” ፖድትያጊን እጁን በሀዘን እያመናጨቀ፣ በረጅሙ ተንፍሶ ከፉርጎው ወጣ፡፡ የተቆጣጣሪዎች ክፍል ገብቶ ጠረጴዛ ላይ ተቀመጠና፣ ድክም ብሎት ይነጫነጭ ጀመር፤ “ውይ ህዝብ! በምንም ነገር ሊደሰት አይችልም! አንድ ሰው የመጨረሻ አቅሙን ተጠቅሞ መልፋትና መስራቱ ትርጉም የለውም፡፡ ሰውን ወደ መጠጥ እና ስድብ ይገፋፋሉ … ምንም ካላደረግህ ይበሳጫሉ፤ ግዴታህን መወጣት ስትጀምር ይበሳጫሉ፡፡ ከመጠጣት ሌላ መፍትሄ የለውም፡፡”  ፖድትያጊን በአንድ ትንፋሽ ጠርሙሱን ከጨለጠ በኋላ፣ ስለ ስራ፣ ግዴታና ታማኝነት መጨነቅ አቆመ፡፡

Read 1495 times