Saturday, 19 September 2015 09:04

ተሳፋሪዎች ቀበቶ እንዲያስሩ ሊገደዱ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

• ባለፈው ዓመት በትራፊክ አደጋ የ448 ሰዎች ህይወት አልፏል
• 22 ተሳፋሪዎች፣ 19 አሽከርካሪዎች፣ የተቀሩት እግረኞች ናቸው

  ለአሽከርካሪዎች የወጣው ደንብ፤ ማንኛውም ሹፌርም ሆነ ከጐን የተቀመጠ ተሳፋሪ፤ የአደጋ መከላከያ ቀበቶ (Seat belt) ሳያስር በጉዞ ላይ ከተገኘ 120 ብር እንደሚቀጣ የሚጠቁም ሲሆን ለሁለቱም ወገን ተጠያቂው አሽከርካሪው ነው ይላል፡፡ እስካሁን ግን ህጉ ከአሽከርካሪዎች በቀር ተሳፋሪ ላይ ሳይተገበር ቆይቷል፡፡ ተሳፋሪዎች እንኳንስ ቀበቶ ሊያስሩ ቀርቶ አብዛኞቹ መኪኖች የአደጋ መከላከያ ቀበቶ ከእነአካቴው የላቸውም፡፡ ተሳፋሪው ቀበቶ የማሰር ልማድ ቢያዳብር ኖሮ፣ በተለያዩ ጊዜያት በሚደርሱ በርካታ አሰቃቂ አደጋዎች ላይ የሟቾችን ቁጥር መቀነስ ይቻል ነበር ይላል - ፖሊስ፡፡
ተወዳጇ አርቲስት ሰብለ ተፈራም በዘመን መለወጫ ዕለት፣ መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም በደረሰባት ድንገተኛ የመኪና አደጋ ወቅት ቀበቶ አስራ ቢሆን ኖሮ የተሻለ የመትረፍ ዕድል ሊኖራት ይችል ነበር ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደገለፀው፤ ትራፊኮች የአሽከርካሪን ብቻ ሳይሆን ከጐን የሚቀመጡ ተሳፋሪዎችንም ቀበቶ እንዲያስሩ ቁጥጥር አለማድረጋቸው  ስህተት ነው፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “በወቅቱ ቀበቶ የማሰርን ጉዳይ በአሽከርካሪው ላይ ብቻ ያጠበቅነው አብዛኞቹ መኪኖች ከእርጅና ጋር በተያያዘ ቀበቶ ስላልነበራቸው ነው” ብለዋል፡፡
ዘንድሮ ግን ህጉ በጥብቅ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር የጠቁሙት ኢንስፔክተሩ፤ አሽከርካሪዎች በህጉ መሰረት የተሳፋሪውንም ቀበቶ አሁኑኑ እንዲያስተካክሉ አሳስበዋል፡፡
“ህይወትን ከአደጋ መከላከል ለራስ ነውና በተለይ በግል ተሽከርካሪ የሚጠቀሙ ግለሰቦች ቀበቶ ማሰርን ካሁኑ መላመድ ይኖርባቸዋል” በማለት ኢንስፔክተሩ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ባለፈው ዓመት (2007 ዓ.ም) በአዲስ አበባ በትራፊክ አደጋ ምክንያት 448 ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 22ቱ ተሳፋሪዎች፣ 19ቱ አሽከርካሪዎች፣ የቀሩት እግረኞች እንደነበሩ የትራፊክ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል፡፡


Read 1752 times