Friday, 11 September 2015 08:55

ጨጨሆ የባህል አዳራሽ ታዋቂ ሰዎችን ሸለመ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ጨጨሆ የባህል አዳራሽ የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአገሪቱ ላይ በባህል፣ በቱሪዝምና በበጐ ሥራ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሰዎች ሽልማት ሰጥቷል፡፡
“የጨጨሆ ባህል ሽልማት” በሚል ርእስ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ አንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ ውብሽት ወርቃለማው የአስር ሺህ ብር እና የዋንጫ ሽልማት ሲያገኙ፣ በውዝዋዜ የምትታወቀውና በቅርቡ ከአሜሪካ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰችው እንዬ ታከለ የአስር ሺህ ብርና የዋንጫ ሽልማት አግኝታለች፡፡ እንዲሁም ከአራት ሺህ በላይ የባህል ግጥምና ዜማ የሰራው ሙሉጌታ አባተ፤ተመሳሳይ ሽልማት ሲያገኝ፣ተወዛዋዥዋ ዳርምየለሽ ተስፋዬም ተሸላሚ ሆናለች፡፡
በሽልማት ፕሮግራሙ ላይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ በቆዳ የተሰራ ምስላቸው የተበረከተላቸው ሲሆን የቱሪዝም አባት የሚባሉት አቶ ሃብተስላሴ ታፈሰም ተሸልመዋል፡፡
የሽልማት ፕሮግራሙ ልዩ ተሸላሚ የሆነው የመቄዶኒያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን ማዕከል መስራች ወጣት ቢኒያም በለጠ ደግሞ 20 ሺህ ብር ተበርክቶለታል፡፡ አርቲስት መሰረት መብራቴ፤የጨጨሆ የባህል አዳራሽ አምባሳደር ሆና ለአንድ ዓመት ለመስራት ተፈራርማለች፡፡

Read 3318 times