Saturday, 05 September 2015 10:04

ሦስቱ ጥያቄዎች

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

   አንዳንድ ነገሮችን ለመፃፍ በጣም እቸገራለሁ፡፡ ይመስለኛል አንድም ስለምፅፈው ነገር በደንብ ስለማላውቅ ነው፤ አልያም የማውቀው ነገር ለመፃፍ አይመችም፡፡፡ ስለዚህ መፍትሄው ምንድነው አቅልሎ መጀመር ብቻ ነው፡፡ ከጥያቄ በላይ ቀላል ነገር የለም፡፡
ጥያቄ፡- ምንድነው ጥበብ?
ጥያቄውን አውቀዋለሁ፡፡ ከጥያቄው ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኙ መልስ መሳይ ነገሮች አሉ፡፡ በተለያየ ሰው አንደበት የተነገሩ፣ በተለያየ ተጓዥ የተቀመጡ መዳረሻዎች …
ግን የትኞቹም እንቅጩን አይጨብጡም፡፡ ዙሪያ ገባውን ይዞሩ ይሆናል እንጂ፡፡ ከፍልስፍና ዘርፎች ውስጥ በቁንፅል ብቻ የተጠና ባይተዋር እንደሆነ ድፍን ሆኖ የተቀመጠ ነገር ቢኖር “ጥበብ ምንድነው?” የሚለው ጥያቄና ፍቺው መሆኑን እኔ እና ቤቴ እናምናለን፡፡
የተመረመረበት አጋጣሚ በጣም ውሱን በመሆኑም ምክኒያት እንደ “መለኮታዊ” ሚስጢር ተደርጎ መወሰዱም አልቀረም፡፡  
ምንድነው ጥበብ? ከሚለው የሚቀድሙ ሦስት ጥያቄዎች እንዳሉ ፈላስፎች ይስማማሉ፡፡ አንደኛው ጥያቄ - ጥበብ የሆነውን ፈጠራ ካልሆነው የሚለየው መለኪያ ምንድነው? የሚለው ነው፡፡
ቀጥሎ የጥበብ አላማው ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ቢሆንም ሁለተኛው ጥያቄ ራሱ በራሱ ውስጥ ሌላ መጠይቆች ይፈጠራል እንጂ የመጀመሪያውን የ “ጥበብ ምንድነው?” ጥያቄን ቀዳዳ አይደፍንም፡፡
የጥበብ አላማው … ማስተማር ነው፣ ፕሮፓጋንዳ ነው ወይንስ ውበትን መጨበጥ? አላማው የትኛው እንደሆነ የመረጠ ሁሉ ደግሞ ለምን እንደመረጠ በተያያዘ ፅንሰ ሀሳብ ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ማያያዝ የሚችለው “የጥበብን ምንነት” ማወቅ ከቻለ ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛው ጥያቄ ራሱ እንደ ቁንጫ ብዙ የጥያቄ እጮች ፈልፍሎ … ነክሶን ሳይገደል እንዳያመልጥ ተጠንቅቀን (በአውራ እና ሌባ ጣታችን ድብን አድርገን ይዘነው) ወደ ሦስተኛው ጥያቄ እናልፋለን፡፡ በሁለት አለኝ!
ሦስተኛው ጥያቄ … ራሱ ጥበበኛው ወይንም የጥበብ ፈጠራ ወኪሉ ማነው ወይንም ምን አይነት ሰው ነው የሚለው ነውን?
እናም እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ስል እስክሪፕቶዬን ባነሳሁበት ጊዜ ሁሉ ፅሁፍ እንቢ ይለኛል፡፡ መያዣ መጨበጫ የሌለውን ነገር ለመግለፅ እንደመሞከር ስለሚሆንብኝ ነው፡፡
አሁንም ከቀላሉ መጀመር ይሻላል፡፡ በቀላሉ ለመግለፅ ከሞከሩት አሳቢዎች መሀል በአንደኛው በእሱ ትከሻ ላይ በመንጠላጠል ኒውተን እንደመሰከረው “ሩቅ ለማየት” ሳይበጀኝ አይቀርም፡፡
ኮሊንግውድ የተባለ የእንግሊዝ ፈላስፋና ታሪክ ተመራማሪ ጥበብን “ገለፃ ነው” ሲል ይገልፀዋል፡፡ ግን “ገለፃ ሲባል መጠንቀቅ ይገባናል” ይላል ኮሊንግውድ “ገለፃ ማለት ምናባዊ አመለካከት እስከታከለበት ድረስ ብቻ የጥበብ አዝማሚያ ይኖረዋል” ይለናል፡፡
“The Principles of Art” በተሰኘው መፅሐፉ እንደሚያስረዳው፤ “ጥበብ … ተፈጥሮን በቀጥታ ከመቅዳት (Representation)፣ ለኑሮ አገልግሎት ሲባሉ ከሚከወኑ እደ ጥበባት (craft)፣ ማህበረሰብን ለማስደሰት ወይንም ለማጫወት ከሚከወኑት (Amusement) ወይንም የአስማት (ምትሀት) (Magic) ትርዒቶች … ውጭ (በላይ) ነው” ይለናል፡፡
የሀሳብን ተፈጥሮ ከላይ ከተጠቀሱት (ጥበብ አይደሉም) ከተባሉት ጋር ያለውን መመሳሰልና ልዩነት ከተነተነ በኋላ … ምናብ የታከለበት “ገለፃ” ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡
ቋንቋ በሌጣው ስንገለገልበትና ቋንቋን ደግሞ ስሜትንና ሀሳብን ስናስተነትንበት የተለያዩ ምንነት አለው … ስሜት፣ ምናብ፣ ሀሳብና ቋንቋ ሲቀላቀሉ በተናጠል እያንዳንዳቸው ከሆኑትም በላይ የሆነ አውታር ተቀይጦ እንደሚፈጠር ያሳያል፡፡ ይህም የቋንቋ አውታር ራሱን የቻለና … የራሱ የመግባቢያ ህጎች ያሉት ከመሆኑም በላይ በራሱ ህግ እንጂ በንጥረ ነገሮቹ ማንነት ብቻ የሚዳኝ አይደለም ይለናል፡፡
The  origin of art he says, can in man’s physical nature (that is, sensation or its emotions) nor in the intellect (concepts)
እናም የጥበብ ፈጣሪ የጥበብ መገለጥን አገኘ (Has an artistic experience) የሚባለው መስተሀልዩ አንዳች አጋጣሚ የጫረበትን ግርድፍ መነካት (Impression) ወደ ሀሳብ ሲቀይረው … ቀጥሎም በዚህ ሀሳቡ ላይ ምናብን ሲያክልበት (ሊያክልበት ሲችል) ነው፡፡
ምናልባትም ይህ የኮሊንውድ እይታ በተለምዶ “ሮማንቲሲስት” ተብለው ከሚጠሩት የጥበብ ንቅናቄ አራማጆች ጋር የሚያስማማው እንደሆነ ይገመታል፡፡ ከሮማንቲክ ዘመን ገጣሚያን አንዱ የሆነው ወርድስወርዝ … የግጥምን መፈጠር መንስኤው የስሜት መገንፈል፣ ወይንም ፈንቅሎ መውጣት መሆኑን ይገልፃል፡፡
“The spontaneous overflow of powerful feelings originating from emotions recollected in traquility”
ለወርድስወርዝ ጥበብ ማለት የስሜት መገለፅ ማለት ነው፤ ግን ስሜትን ቅርፅና ይዘት ሰጥቶ እስትንፋስ የሚዘራበት “ምናብ” (Imagination) ነው፡፡ የኮሊንግውድን ሀሊዮት ተመርኩዤ የት እንደደረስኩ …. ወይንም በዚህ እይታ ላይ ቆሜ ምን እንደሚታየኝ ለማወቅ  አልችልም፡፡ ምናልባት ምንም ስለማይታየኝ፡፡ እንዲያውም ከቆምኩበት እንግሊዛዊው ፈላስፋ ትከሻ ላይ የሚያሟልጨኝ አንድ ጥያቄ ሲረገዝ ይሰማኛል፡፡ ምናብ እና ምኞትን … ወይንም ምናብ እና ቅዠትን እንዴት ነው እምለያቸው? … በአንደኛው መታወቂያ ወረቀት ሌላኛው ሾልኮ በአርቲስቱ ሀሳብ ውስጥ ዘው ቢል እንዴት ይለያቸዋል?
ግን ኮሊንግውድ ለዚህም መልስ አለው፡- ምኞት (Fancy) በጊዜ እና ቦታ የታጠረ፣ ባይከሰትም ሊከሰት የሚችል … ያልወጣ የሎተሪ እጣ አይነት ነው … ይላል፡፡ ምናብ ግን ከጊዜና ቦታ የተፋታ ግን በጊዜ እና ቦታ መቼም የማያደበዝዛቸውን መሰረታዊ (Vital) የማይለወጡ የህይወት ንጥረ ነገሮችን (Archives) ይዞ ህልሙን የሚያደራ ነው፡፡ ከዚህ ቋሚ መነሻዎች ውጭ በጊዜና ቦታ የተገደቡትን … ወደ ቋሚ ከጊዜና ቦታ ወረተኝነት የማይናወጥ ዘላለማዊነት ለመድረስ ይንጠራራል፡፡
“It dessolves, diffuses, dissipates, in order to recreate; or where this is impossible, yet still, at all events it struggles, to idealize, to unity.”ይህ ሁሉ ጣጣ እንግዲህ የሚከናወነው በአንድ ግለሰብ የማስተዋልና የመፍጠር አቅም ውስጥ ነው፡፡ በአንድ የህይወት ጊዜ ቆይታ ውስንነት ገደብ፡፡
ምን ቢያደርግ ነው አንድ ሰው ራሱን ወደ አርቲስት ቀይሮ … አርቲስቱ ደግሞ በአንድ ገለፃ፣ በአንድ መግለጫ አውታር አማካኝነት ይኼንን ከጊዜም ከቦታም በላይ የሆነ ሁሉንም ነገር በኢምንት ፈጠራ ውስጥ ዘላለማዊ አድርጐ ማስቀመጥ የሚችለው? ስንል … ከቆምንበት የኮሊንግውድ ትከሻ አዳልጦን መውደቅ ይዳዳናል፡፡ ምናልባት እንዳንወድቅ ሊደግፈን ይችል እንደሆን በእርግጥ ባላውቅም አንድ ሠዓሊ በፅሁፍ አስቀምጦልን የሄደው አባባል (ለእኔ) ከመውደቅ ድጋፍ ሲሆነኝ ይሰማኛል፡፡ ይህ ሰዓሊ ቪንሰንት ቫንጎ ይባላል፡፡ ይሄንን ጥበብን በምናብ የማስገኘት አስቸጋሪ እንደሆነ እያወቀ አስቸጋሪነቱን ተሻግሮ መፍጠር የሚቻለው “በፍቅር” ብቻ ነው ይለናል፡፡ አንድን አጋጣሚ፣ ክስተት ወደ ጥበባዊ መነካት (Artistic experience) የሚለውጠው ተመልካቹ … የተመለከተውን ነገር ማፍቀር ሲችል ብቻ ነው ባይ ነው፡፡ ማፍቀር ሲችል ብቻ ነው የነገርየው እውነተኛ ማንነትም ሊገለፅለት የሚችለው ይለናል፡፡ “It is by loving a thing, that one can perceive it better and more accurately”
“መነካት” ማለት የአንድን ነገር ውበት ማየት ማለት ነው፡፡ ለመነካት ግን ማፍቀር ይቀድማል፤ እንደማለት፡፡ እንደ ሰዓሊው ቫንጐ እይታ፡፡
ኦስካር ዋይልድም ያለው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ እሱ ግን መነሻውን “ውበት” ነው ያደረገው፡፡ “ማንኛውንም ነገር የምናየው መጀመሪያ ውበቱ ሲገለፅልን ነው” ይላል፡፡ ቫንጎ ከፍቅር፣ ዋይልድ ከውበት ይነሳል፡፡
በኮሊንግውድ የጥበብ ፍልስፍና ላይ ቆሜ ቫንጎን እና ኦስካር ዋይልድን ተመርኩዤ … ሌሎቹን መጀመሪያ ላይ የጠየቅሁዋቸውን ጥያቄዎች እያሰላሰልኩ … ለመልስ እየጓጓሁ … ምናልባት እስከሚቀጥለው የፅሁፍ ድፍረት ጊዜዬ ለመቆየት እችላለሁ፡፡

Read 3072 times