Saturday, 05 September 2015 10:03

ገጣሚ ወንድዬ አሊ ስለ ግጥም…

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“የአገራችን ግጥም በተስፋና በፅልመት መካከል ያለ ግራጫ ሆኖ ይታየኛል!”
             እንባና ሳቅን አሥማምቶ፣ ያለ ሸንጎና ፍርድ በሀረጋትና ስንኞቹ ትከሻ ለትከሻ ትቅቅፍ ህይወትን አዲስ የሚያደርግ ሰው - ገጣሚ ነው፡፡ ሰማይና ምድርን አሳስሞ ባንድ መኝታ ላይ የሚያጋድም ተዓምረኛም እንደዚሁ … ገጣሚው ነው፡፡ የመላዕክት ክንፎችን ላንብብ፣ የእግዜርን ጓዳ ልፈትሽ ብሎ መጋረጃ ገለጣ የሚደፍር ገጣሚ ነው፡፡
የጠፋን ነገር አሥሶ፤ የራቀን ነገር አቅርቦ የሚያሳይ ንሥር ዓይን ያለው ገጣሚ ከአደባባይ ሲጠፋ፣ … “የት ገባ?” ማለት ያገር ነው፡፡ “የወፌ ቆመች” እና የ “ውበት እና ህይወት” የግጥም መጽሐፍት አባት የሆነው ወንድዬ ዓሊ-የት ጠፋ? የአዲስ አድማስ ፀሐፊና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ፣ ከገጣሚ ወንድዬ ዓሊ ጋር በሕይወቱና በግጥም ጥበብ ዙሪያ ተከታዩን ውይይት አድርገዋል፡፡

    ወንድዬ፡- ከአሥር ዓመታት በላይ በግሌ እየሰራሁ ነው፤ ቤቴ ቢሮዬም ሆኗል፡፡ ሥራ ለመቀበል፣ ለማስረከብም ካልሆነ ወይንም የጥናት ወረቀት ከሌለ በስተቀር ከቤቴ አልወጣም፡፡ በየቀኑ ከ12 - 16 ሰዓታት ድረስ እሰራለሁ፤ ይኼ አሰረኝ፡፡ በተለይ ደግሞ ሥነ ጽሑፍ የሕይወትህ ጥሪ - እንጀራህም ሲሆን የበለጠውን እርጋታና ፀጥታ ፍለጋ ከአደባባይ ትጠፋለህ፡፡
በጠፋህባቸው ዓመታት ምን ምን ሰራህ ታዲያ?
በትምህርት (ሙያዬ ልበል ይሆን) ደረጃ ኮሚዩኒኬሽን አጠናሁ - በማስተርስ ደረጃ፡፡ በዚህ ረገድ ከበራሪ ወረቀቶች አንስቶ እስከ ትልልቅ ጥናቶችና መጻሕፍት ዝግጅት ድረስ (እንደ ደንበኞቼ ፍላጎት) ስሰራ ከረምኩ፡፡ አጫጭር ዘገባዊ ፊልሞችም አሉ፣ ሦስት አራት የሚሆኑ፡፡ ይዘታቸውን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ (ኤችአይቪ፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ የልጆች አስተዳደግ፤ የህይወት ክህሎት) እስከ ግለታሪክ ዝግጅቶችና ህትመቶችን ይጠቀልላሉ፡፡ ለነገሩ ኮሚዩኒኬሽን ስትማር ብፌ እንደተመገብክ ቁጠረው፣ ሳይኮሎጂው፣ ስነ ሰብዕ (Anthropology)፣ ስነ - ጽሁፍ እንዲሁም ወደፍልስፍናና አንዳንድ ደረቅ ሳይንሶችም ትጠጋለህ፡፡ ልባም ከሆንክ በንባብና ጥናት አሳድገህ ባለብዙ ፈርጅ ባለሞያ ትሆናህ፡፡ ይህ ደግሞ ኮሚዩኒኬሽን በመማር የሚገኝ ትሩፋት ብቻ ሳይሆን የምንማርበት ተቋም ሥርዐተ ትምህርት፣ የመምህራኑ አቅምና መሰጠት እንዲሁም ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው እውቀትን ለመበዝበዝ ባላቸው ዝንባሌና ጥረት የሚወሰን ይሆናል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ጠነን ያለ፣ ምናባዊ ሸጋ ቋንቋ የሚጠቀም ገጣሚ ነው - ይሉሃል፡፡  ምን ዓይነት ግጥሞች ነው የምትወድደው?
ከስነ ግጥም ዓይነቶች ይልቅ የሚገደኝ ምንጫቸውና አፈጣጠራቸው ነው፡፡ ሰይፉ መታፈሪያ፤ “ግጥም ምንጩ ግለሰባዊ፣. ባፈጣጠሩ ዐይነ - ልቡናዊ፣ ባቀነባበሩ ጭምቅ፣ በቋንቋው ስልታዊ ነው” የሚለው አባባላቸው ይጥመኛል፡፡
ጋሼ ጸጋዬ ደግሞ ማቲው አርኖልድን ጠቅሶ፤ “ሥነ ግጥም ያው የገዛ ሕይወቱ ሂስ ነው” ይላል፡፡ ይህም ግሩም ነው፡፡ ሥነ ግጥም የገዛ ህይወት ሂስ ከመሆኑ ጋር የምደምረው ቁም ነገር አለኝ፤ ይኸውም ከደበበ ሰይፉ የተማርኩት ነው፡፡ “ባድማ ልቡን አድምጦ የሚጽፍ ጸሐፊ ከማህበረሰቡ የተጣላ ነው፡፡” የሚለውን አነጋገሩን እወድለታለሁ፡፡
ከጸጥታና እርጋታ ባሻገር በራስህ ዓለሙን ረስተህ፣ ዓለሙም አንተን ሸጉሮብህ (ቀርቅሮብህ) የምትጽፈው ግጥም የምድረበዳ ምኞት ዓይነት ነው፡፡ በጠየቅኸኝ መሰረት፤ ባብዛኛው የምወደው የግጥም ዓይነት ምሰላን ትርጉም ያላቸውን ይመስለኛል፡፡ የአንድ ቀን ክስተት ተንተርሰው የሚገጠሙ የአዝማሪ ዓይነት ግጥሞችን ብዙም አልወድም፡፡ የአንድ ቀን ገጠመኝ ግን ወደ ህይወት ምሰላ ተለውጦ፣ ሁለንታዊነትን ተላብሶ፣ ሳነብበው ደስ ይለኛል፡፡ ውበት እና ሕይወት ውስጥ “በጥላዬ” የሚለውን ግጥም የጻፍኩት ኃይሌ ገብረስላሴ በኦሎምፒክ መድረክ አንደኛነቱን ለቀነኒሳ ባስረከበበት ቀን ውድድሩን በቴሌቪዥን ካየሁ በኋላ ነበር፡፡ ግና በግጥሙ ውስጥ ኃይሌም ቀነኒሳም የሉም፣ ህይወት ግን ነበረች፡፡ እኔም ነበርኩ፡፡
“ጥላዬ”
የቀደመው ቀረ
   ጀማሪው ፊተኛ
   ፊተኛው ከኋላ
   የኋላው አንደኛ፡፡
    ያልዘቀጠው ወጣ
    የወጣው ዘቀጠ፡፡…
ፊት የወጣች ፀሐይ
    በ-ምዕራብ ሰማይ
    መጥለቂያው በር ላይ፡፡
አዲሷ ከምሥራቅ
    በንጋት አልፋ ላይ
በማለዳ ‘ርከን ላይ፡፡
    እርከኑ እስቲሰበር
    በጭለማ በትር፡፡
የቀደመው ሲቀር፣
የወጣው ሲዘቅጥ፣
ምዕራብ ሲጠልቅበት፣
ጐህ ሲቀድ ለምሥራቅ፣
እነሱን ሲታዘብ … በወጣ … ዘቀጠ
ከገቡበት መቅረት
ከወጡበት መግባት
እንዴት ባመለጠ!?
“ውበትና ሕይወት”ን ካሳተምክ ዘጠኝ ዓመታት አለፉ፤ አሁንስ ግጥም፣ ትጽፋለህ?
ባልጽፍማ ሞቼአለሁ ማለት ነው፡፡ “ውበት እና ሕይወት” በ1998 ዓ.ም ታተመች፡፡ “ወፌ ቆመች” ረቂቁ ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የተሰጠው በ1982 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ነበር፡፡ የታተመችው በ1984 ዓ.ም ይመስለኛል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮተቤ የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ እንደተጨማሪ ማስተማሪያ ሆነች፡፡
“ወፌ ቆመች ቅጽ 2 (ውበት እና ህይወት)” ስትታተም ድፍን አገሩ በነፃ ፕሬሶች የተጥለቀለቀበት ጊዜ ነበር፡፡ ስለዚህ ድምፅዋ ሳይሰማ ከገበያ ጠፋች፤ ተሸጠች፡፡ አዳዲሶቹን ግጥሞች “ወፌ ቆመች ቅጽ 3” ለማሳተም የዘመኑን ነገር እያደባሁ ነው፡፡
በዚህ ዘመን በግጥም ሥራዎች ረገድ ምን ገረመህ?
ያልተዘመረላቸው ጀግኖች እንዳሉ ሁሉ ያልተዘመረላቸውም መጻህፍት መኖራቸው! … የኔ መጽሐፍ “ውበት እና ሕይወት” እንኳ በጎምቱ አንባቢዎች እጅ ብቻ ገብታ ለአዲሱ ዘመን ገጣሚያን የስልትና የፍልስፍና ግብዐት ሣትሆን ልሂቃን ልብ ውስጥ መቅረቷ ገርሞኛል፡፡ ጥቂት የተጠቀመበትና ወደ ቀጣዩ ትውልድ ልብ ያሻገራት ሟቹ ብርሃኑ ገበየሁ ብቻ ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ የሥነ - ግጥምን ጥበብ የሚመለከት “ወፌ ቆመችን እንደ ዘሪሁን አስፋው (የሥነ ፅሁፍ መሰረታዊያን በሚለው መጽሐፍ) “ውበት እና ህይወት”ንና “ወፌ ቆመች” ን አዳብሎ በመተንተን እንደ ብርሃኑ ገበየሁ ያሉ ምሁራን አላገጠሙኝም፡፡
“ፎክር ፎክር አለኝ”
ፎክር!
ፎክር!
    አለኝ፣
ነዘረኝ
ነሸጠኝ
ፎክር - ፎክር አለኝ፣
    ሽለላ - ሽለላ፣
አለ ይሆን ዛሬ
    ግብር የሚበላ!? …
ፎክር
ፎክር
አለኝ፡፡
እንዴ …. !
በነ አባጃሎ አገር
በጀግኖቹ ጎራ፣
ገዳይ በጎራዴ
ገዳይ በጠገራ፡፡
በሾተለ አንደበት
    ገዳይ በአፈር ሳታ፣
በነገር ነጎድጓድ
            ገዳይ በቱማታ፤ …
በነዘራፍ ስንቁ
    ባለ ብር ሎቲ፣
በተሞላች አገር ፡-
ጅረት ባበጀባት
ዘንቦ የደም ዕምባ፤
ተራህ ነው ይለኛል፣
ተሠራ ሹርባ፡፡
በአማርኛ ሥነ ግጥም ምን ይታይሃል?
በተስፋና በፅልመት መካከል ያለ ግራጫ ነገር ሆኖ ይታየኛል፡፡
(ይቀጥላል)

Read 6531 times