Saturday, 05 September 2015 09:52

የገንዘቤና አልማዝ ትንቅንቅ እስከ ኦሎምፒክ ይቀጥላል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

በ3ሺ እና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና የያዙት ትንቅንቅ እስከ ኦሎምፒክ እንደሚቀጥል በስፋት እየተዘገበ ነው፡፡ በ15ኛው የዓለም አትሌተክስ ሻምፒዮና ወደ አስደናቂ የፉክክር ደረጃ ያደገው የሁለቱ አትሌቶች ተቀናቃኝነት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የተስፋ ብልጭታዎችን ፈጥሯል፡፡  
ከ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና ከ2015 ዳይመንድ ሊግ በኋላ በኦል አትሌቲክስ  ድረገፅ በወጣ የውጤት ደረጃ በሴቶች  ሁሉም ዓይነት የውድድር መደቦች በ1461 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ገንዝቤ ዲባባ ስትሆን አልማዝ አያና በ1418 ነጥብ በ2ኛ ደረጃ ትከተላታለች፡፡ በሌላ በኩል በ5ሺ ሜትር አልማዝ አያና በ1418 ነጥብ 1ኛ ደረጃን ስትቆናጠጥ ገንዘቤ ዲባባ ደግሞ በ2ኛ ደረጃ የምትከተለው በ1404 ነጥብ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በኢትዮጵያ የተሳትፎ ታሪክ በ1500 ሜትር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበችው አትሌት ገንዘቤ ዲባባ፤ ከትናንት በስቲያ ደግሞ የ2015 ዳይመንድ ሊግን በ5ሺ ሜትር ማሸነፏን አረጋግጣለች፡፡ በዚህ ውጤቷም የዳይመንድ ሊግ ዋንጫና 40ሺ ዶላር የገንዘብ ሽልማት አሸንፋለች፡፡
በሌላ በኩል በዓለም ሻምፒዮናው በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ በአስደናቂ አሯሯጥና ታክቲክ ለመጐናፀፍ የበቃችው አልማዝ አያና የዓለም አትሌቲክስን ትኩረት ስባለች፡፡ በውድድር ዘመኑ የገንዘቤን ኃያልነት በከፍተኛ ደረጃ በመቀናቀንና ከ2 ጊዜ በላይ አሸንፋት በተፎካካሪነት መጠቀስ የጀመረችው አልማዝ ለኦሎምፒክ ስኬት ከተገመቱ የኢትዮጵያ አትሌቶች ግንባር ቀደም ግምቱን እየወሰደች ነው፡፡  ሁለቱ የዓለም ሻምፒዮኖች በ3ሺ ሜትርና በ5ሺ እያሳዩ ያሉት ተመጣጣኝ ብቃት ከስራቸው ከምትከተላቸው ሰንበሬ ተፈሪ ጋር  እስከ 2016 የሪዮ ዲጄኔሮ ኦሎምፒክ በተለይ በ5ሺ ሜትር የኢትዮጵያን የበላይነት አስተማማኝ እንደሚያደርገው እየተወሳ ነው፡፡

Read 3107 times