Saturday, 05 September 2015 08:35

ከአመቱ ስኬትና ቅሌት፤ በጐና መጥፎ…

Written by 
Rate this item
(9 votes)

1. [የባራክ ኦባማ ጉብኝት፤ የትሪሊዮን ዶላሮች ጉባኤ፤ የ100% ምርጫ፤ ዘግናኞቹ ግድያዎች]
2. [የኤክስፖርት ድንዛዜ፣ “እድሜ ለዳያስፖራ”፣ የነዳጅ ዋጋ እና የሚኒስቴሩ አስገራሚ መግለጫ]

    በፖለቲካው መስክ፣ የባራክ ኦባማ ጉብኝትና የዩኤን የፋይናንስ ጉባኤ በበጎነት የሚጠቀሱ ክስተቶች ናቸው። በእርግጥ፣ የኦባማ የፖለቲካ ቅኝት፣ የአሜሪካ የነፃነትና የብልፅግና አርአያነትን ይወክላል ብዬ አላስብም።
እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገራት፣ ወደ ተሻለ አቅጣጫ እንዲጓዙ፣ የመገፋፋት ብቃት አላቸው ብዬም አላምንም።
ቢሆንም ግን፣ የኦባማ ጉብኝት፣ ለኢትዮጵያ መልካም ክስተት ነው። ከአሜሪካ የተሻለ የስልጣኔ አርአያ ስለሌለ፣ ከአሜሪካ ጋር መወዳጀት ጥሩ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ በተወሰነ ደረጃ እንዲሻሻል፣ ያም ባይሆን፣ ይብስ እንዳይበላሽ ይረዳ ይሆናል - የአሜሪካ ወዳጅነት። በዚያ ላይ፣ የስራ እድል የሚከፍቱ፣ የቢዝነስ አሰራርን ለማሻሻል የሚያግዙ የውጭ ኢንቨስተሮች፣ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡም ያደፋፍር ይሆናል።
የዩኤን ጉባኤስ? ለድሃ አገራት የገንዘብ ምንጭ ለማፈላለግ፣ በአዲስ አበባ የተካሄደው የዩኤን የፋይናንስ ጉባኤ፣ እንደ ድሮው ከቢሊዮን ዶላሮች አልፎ፣ ስለ ትሪሊዮን ዶላሮች የተወራበት ጉባኤ ነው። ግን፣ ጉባኤው ለኢትዮጵያ እንደ በጎ አጋጣሚ የሚቆጠረው፣ ዩኤን እንደሚያወራው፣ ዶላር ይጎርፍልናል በሚል አይደለም።
እንደ ካሁን ቀደሙ፣ አብዛኛው የእርዳታ ወሬ፣ በዚያው ወሬ ሆኖ ነው የሚቀረው።  የተወሰነ እርዳታ አይመጣም ማለት አይደለም። ይመጣል። ነገር ግን፣ እርዳታ... ካሁን በፊት እንደታየው፣ ለተወሰነ ጊዜ በሕይወት ለመቆየትና ከአደጋ ለማምለጥ ያግዛል እንጂ፣ ብልፅግናን አያስገኝም።
ቢሆንም፣ ስብሰባው በአዲስ አበባ መካሄዱ መልካም ነው። በሺ የሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች የተገኙበት ትልቅ ጉባኤ መሆኑ፣ አንድ ነገር ነው። ግን፣ ከዚህም ይበልጣል። እንደ ሌላው ጊዜ፣ በአንድ አዳራሽ የተካሄደ ወይም በጥቂት ስብሰባዎች የተጠናቀቀ ጉባኤ አይደለም። ጎን ለጎን፣ ከ200 በላይ ስብሰባዎች ናቸው የተካሄዱት። ትልልቆቹ ሆቴሎች፣ በአንድ ቀን ውስጥ፣ ከአምስት እስከ ሰባት አዳራሾችን፣ ማከራየት ሲችሉ አስቡት። አንዱን አዳራሽ ሁለቴና ሦስቴ ሲያከራዩስ? ጉባኤው፣ ለበርካታ ሆቴሎች፣ የአመቱ ትልቅ ባለውለታ ነው።
የ100% ምርጫ
ሌላኛው የአመቱ ክስተት፣ ፉክክር የራቀውና 100% ኢህአዴግ ያሸነፈበት የፓርላማ ምርጫ ነው። የአገራችን ፖለቲካ፣ ገና ኋላቀር መሆኑን የሚመሰክር ምርጫ ቢሆንም፣ አወንታዊ ነገር እናውጣለት ብለን መሞከር እንችላለን።
አንደኛ ነገር፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን፣ የፓርቲዎችን ክርክር በቴሌቪዥን አይተናል። ሁለተኛ ነገር፣ ምርጫው ላይ፣ አንዳችም የፉክክር ምልክት አልነበረም ማለት አይደለም። ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፓርላማ ወንበር ባያሸንፉም፣ በበርካታ ከተሞች፣ እስከ 30 በመቶ ድረስ ድምፅ ያገኙበት ምርጫ እንደነበረ ማስታወስ ያስፈልጋል። ሦስተኛ ነገር፣ አላስፈላጊ ቀውስ አልተፈጠረም።
ከዚህ ውጭ፣ ያው፣ ወደፊት እንዲሻሻልና፣ ከፉክክር ጋር በሰላም የሚካሄድ ምርጫ እውን እንዲሆን መመኘትና መጣር ነው።

ሃዘንና ቁጭት - በአክራሪነትና በዘረኝነት
2007 ዓ.ም፣ በጣም አሳዛኝ ክስተቶችን ያስተናገድንበት  አመት ነው። አለምን እያናወጠ የሚገኘው የሃይማኖት አክራሪነትና አሸባሪነት፣ ኢትዮጵያዊያንን የሚምር አልሆነም። በእርግጥም፣ ከየትኛውም እምነት ቢሆን፣ ከእስልምናም ሆነ ከክርስትና፣ ከሂንዱም ከሆነ ከቡድሃ እምነት፣ ብዙም ልዩነት የለውም። የሃይማኖት አክራሪነት፣ ማንንም አይምርም። ይሄ እውነት ነው። እንዲያም ሆኖ፣ አሸባሪዎች፤ ሊቢያ ውስጥ፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የፈፀሙት አረመኔያዊ ግድያ፣... አእምሮ ከሌለው ክፉ አውሬ እንኳ የማይጠበቅ ነው።
ያልታጠቁ ሲቪሎችን፣ ለዚያውም ስደተኞችን በጅምላ መጨፍጨፍ ምን ይባላል?... የሃይማኖት አክራሪነት የእብደት መጠን፣ “እዚህ ወይም እዚያ ድረስ ነው” ተብሎ የሚገለፅ አልሆነም።
በዚህ መሃል፣ ገዢው ፓርቲ፣ ያንንም ያንንም “አሸባሪ” ብሎ እየወነጀለ፣ እጅግ አሳሳቢ የሆነውን ጉዳይ፣ ተራ የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ ሲያደርገው ማየት ያሳዝናል። እጅግ አላዋቂነት ነው። ይህም ብቻ አይደለም።  
ሁሉም ባይሆኑም፣ በርካታ ተቃዋሚዎችም፣ ‘ገዢውን ፓርቲ ለማሳጣት ይጠቅመናል’ በሚል ቀሽም ስሌት፣ ጨርሶ የሃይማኖት አክራሪነትና የሽብር ስጋት የሌለ እስከማስመሰል ይደርሳሉ።
እባካችሁ፣ ገዢው ፓርቲ እና ተቃዋሚዎች፣ ... ምናለ፣ አንዳንድ ከባባድ ጉዳዮች፣ በጭራሽ የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ መሆን እንደሌለባቸው ብትገነዘቡልን።
የዘረኝነት እብደትም፣ እዚህ ላይ መጥቀስ ያስፈልጋል። የዘረኝነት እብደት፣ ገደብ እንደሌለው፣ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች ስደተኞች ላይ በተፈፀመው ዘግናኝ ግድያ አይተናል።
ድሮ ድሮ የምናውቀው፣ በዘር የተቧደኑ ጥቂት ነጮች፣ በጥቁሮች ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ፤... ወይም ሮበርት ሙጋቤ እንዳደረጉት፣ በዘር የተቧደኑ ጥቂት ጥቁሮች፣ በነጮች ላይ ሲዘምቱ ነበር። ሮበርት ሙጋቤን የሚያደንቁ ‘አላዋቂዎች’፣ ምንን እያደነቁ እንደሆነ መች አወቁ?
ዘረኝነት፣ “ጥቁርና ነጭ” በሚል መቧደኛ ውስጥ ታጥሮ፣ እዚያው እንደተቀመጠ ሊቀር አይችልም። በአገር፣ በብሄረሰብ፣ በጎሳ፣ በወረዳ... እያለ፣ ከላይ እስከ ታች ሁሉንም ሳያዳርስ፣ የጥፋት ሰደዱ አይቆምም - ሙሉ ለሙሉ ካላስወገዱት በቀር። በተግባር እያየነው አይደል?

በኢኮኖሚው መስክ፡
“የነዳጅ ዋጋና አስገራሚው የንግድ ሚኒስቴር ስጋት”
(“የኤክስፖርት ድንዛዜ” ፣ “እድሜ ለዳያስፖራ”፣ “አስፊሪ የብድር ክምር”)
በ2007፣ ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ያለው አለማቀፍ የኢኮኖሚ ዜና፣ የነዳጅ ዋጋ መቀነሱ ነው። ባለፉት ስድስት ወራት፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ፣ በትንሹ ከፍና ዝቅ ቢልም፣ ከአመት በፊት ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ግን፣ በጣም ወርዷል -  በበርሜል ከ110 ዶላር ወደ 50 ምናምን ዶላር። ይህም ብቻ አይደለም።
የነዳጅ ዋጋ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ እንደገና ሊጨምር ይችላል ተብሎ አይገመትም። አንደኛ ነገር፣ የበርካታ አገራት ኢኮኖሚ፣ ብዙ የመነቃቃት አዝማሚያ አይታይበትም። በርካታዎቹ ደግሞ፣ የለየለት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል። ሁለተኛ ነገር፣ የሳዑዲ አረቢያ መንግስትና ሌሎቹ፣ የነዳጅ ምርት ለመቀነስ ፍላጎት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ገልፀዋል። እንዲያውም፣ የነዳጅ ምርት ጨምሯል - በተለይ አሜሪካ ውስጥ በተስፋፋውና ‘ፍራኪንግ’ የተሰኘ አዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ አማካኝነት።
ሦስተኛ ነገር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ የቻይና ኢኮኖሚ፣ በበርካታ ችግሮች ሳቢያ መደነቃቀፍ አብዝቷል። የኢኮኖሚ እክል ሲያጋጥም፣ የነዳጅ ፍጆታ እንደሚቀንስ ሲያስረዱ የከረሙት አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት፤ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት፣ ከቻይና የኢኮኖሚ እክል ጋር፣ የነዳጅ ዋጋ ይበልጥ እንደወረደ ዘግበዋል። ለሚቀጥሉት በርካታ ወራት፣ ያን ያህልም የዋጋ ጭማሪ አይከሰትም ሲሉም ግምታቸውን ገልፀዋል። ይሄ፣ ለኢትዮጵያ መልካም የኢኮኖሚ ዜና ነው። መንግስት የተጣራ ነዳጅ ለማስመጣት የሚከፍለው ዋጋ በ45% እንደቀነሰ፣ በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው ሪፖርት ገልፆ የለ! ግን ምን ማለት ነው? ልዩነቱን መመልከት ትችላላችሁ።
በ2007 ዓ.ም ከጥር እስከ መጋቢት መጨረሻ፣ የተጣራ ነዳጅ ገዝቶ ወደ ኢትዮጵያ ለማስመጣት የዋለው ገንዘብ፣ 317 ሚሊዮን ዶላር ነው።
በ2006 ዓ.ም የነበረው ዋጋ ባይቀንስ ኖሮ ግን፣ 583 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልግ ነበር። ልዩነቱ ቀላል አይደለም። በሦስት ወራት ብቻ፣ 266 ሚሊዮን ዶላር ማዳን፣ እጅግ ትልቅ ነገር ነው። የነዳጅ ዋጋ፣ በዚህ ከቀጠለ፣ በዓመት ውስጥ፣ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ዳነ ማለት ነው - ወደ 22 ቢሊዮን ብር ገደማ።
“ጥሩ ነው። ጥሩ ነው። ግን፣ ጥሩነቱ አየር ላይ እንደተንሳፈፈ ቀረሳ” የሚል ስሜት ቢፈጠርባችሁ አይገርምም። ትንሽ ወደ መሬት እናውርደው።  
አምና፤ በመጋቢት 2006 ዓ.ም፣ ቤንዚን ገዝቶ ወደ አገር ለማስገባት፣ በሊትር 14.70 ብር ይፈጅ ነበር።
ከወደብ ለመረከብና ወደ ነዳጅ ማደያዎች ለማድረስ፣ የማጓጓዣ ወጪ አለ። የታክስ ክፍያም ይጨመርበታል። የችርቻሮ የአገልግሎት ክፍያና ሌሎችም ወዘተ...። ነገር ግን፣ የችርቻሮ ዋጋው፣ በገበያ ውድድር ሳይሆን፣ መንግስት በሚያወጣው ተመን ነው የሚወሰነው። እናም በሊትር፣ 20.30 ብር ነበር የሚቸረቸረው - አምና በመጋቢት ወር።
[በ14.70 ተገዝቶ ይመጣል። በ20.30 ይቸረቸራል]
ዘንድሮስ?
ዋጋው ስለወረደ፣ ቤንዚን ወደ አገር ለማስገባት፣ ወጪው ከ8.50 ብር በታች ሆኗል - ለአንድ ሊትር ቤንዚን።
መንግስት የተመነለት የችርቻሮ ዋጋስ? ለአንድ ሊትር፣ 17.90 ብር ነው።
[በ8.50 ተገዝቶ ይመጣል። በ17.90 ይቸረቸራል]። ይሄ በፍፁም ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ነው የምትሉ ከሆነ አልተሳሳችሁም።
የአለም ባንክ፣ ባለፈው ሐምሌ ባወጣው ሪፖርት፣ የችርቻሮ ዋጋው፣ ወደ 14.80 ብር መውረድ እንደነበረበት ይጠቁማል። (4TH ETHIOPIA ECONOMIC UPDATE - ገፅ 15)። ግን፣ አልወረደም። በዚህ ምክንያት ብቻ ከቤንዚንና ከነናፍጣ፣ መንግስት የሚያገኘው ትርፍ፣ ከ7.5 ቢሊዮን ብር በላይ ነው። ‘ያልታሰበ ሲሳይ’ ሆኖ ሊታየው ይችላል።
በዚህ መሃል፣ ረቡዕ እለት፣ የንግድ ሚኒስቴር ያወጣውን መግለጫ ሰምታችሁ ይሆናል። በአለም ገበያ፣ የነዳጅ ዋጋ ይበልጥ መውረዱን ይጠቅሳል መግለጫው። የአገር ውስጥ የችርቻሮ ዋጋ ግን አይቀየርም፡፡ እስካሁን የነበረው ተመን፣ በመስከረም ወርም እንዲቀጥል ወስኛለሁ ብሏል ሚኒስቴሩ።
የችርቻሮ ዋጋው፣ ከአለም ገበያ ጋር እንዲቀንስ የማይደረገው ለምንድነው? ሚኒስቴሩ፣ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ አዘጋጅቷል።
የእስካሁኑ የዋጋ ተመን እንዲቀጥል የተወሰነው፣ የአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥሉ በማሰብ እንደሆነ ሚኒስቴሩ ገልጿል።
እንዴት እንዴት?
የአለም ገበያን ተከትሎ፣ የችርቻሮ ዋጋው ከተቀነሰ፣ “የአገሪቱ ኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ይናጋል” ማለት ነው? የንግድ ሚኒስቴር ስጋት፣ ግራ የሚያጋባ ነው። “በአለም ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ አስገራሚ ስጋት” ተብሎ ለድንቃድንቅ መዝገብ ቢመረጥ አይበዛበትም።
“አንተ፣ ዋጋውን አስተካክል እንጂ፣ ቀሪውን ለኛ ተወው። ጨርሶ ስጋት አይግባህ” ብላችሁ ልታሳምኑት ከቻላችሁ ሞክሩ - የሚሰማ ከሆነ።
እንደሚመስለኝ ግን፣ መንግስት ይህንን የገንዘብ ምንጭ በቀላሉ ለመልቀቅ ፈቃደኛ ይሆናል ብዬ አልጠብቅም። መዓት ወጪዎችን ለመሸፈን ገንዘብ ያስፈልገዋል። እየተከመሩ የመጡ እዳዎችን ለመክፈል፣ ገንዘብ ያስፈልገዋል። አስቀድሞ፣ ወጪዎችን ለመቀነስና ብድር ላለማብዛት የማይጠነቀቅ ከሆነ፣ ምን ማድረግ ይቻላል?
ለማንኛውም ግን፣ በአለም ገበያ፣ የነዳጅ ዋጋ መቀነሱ ጥሩ ነው። አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ከየት ይመጣ ነበር?
ከኤክስፖርት?
የኤክስፖርት ነገርማ፣ አሳዛኝ ሆኗል። ላለፉት አራት አመታት፣ ምንም አይነት እድገት ሳይታይበት፣ እዚያው በነበረበት ቦታ እየረገጠ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ፣ ዶ/ር አርከበ እቁባይ የተናገሩትን መጥቀስ ይበቃል - “በጣም በጣም አሳሳቢ ነው” ብለዋል፡፡  
እንደ መንግስት ‘እቅድ’ ቢሆን ኖሮ፣ ወደ ውጭ ምርታቸውን የሚልኩ ድርጅቶች እየበዙና እያደጉ፣ በአመት የሚያገኙት የሽያጭ ገቢ፣ ዘንድሮ ቢያንስ ቢያንስ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ይደርስ ነበር። ግን አልሆነም። ከአራት አመት በፊት የነበረበት ቦታ ላይ ቆሟል - 3 ቢሊዮን ዶላር ላይ።
ሌላኛው፣ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ፣ የውጭ እርዳታና ብድር ነው። እርዳታው ባይቋረጥም፣ እንደታሰበው አልጨመረም። እርዳታ ሰጪዎቹ የአውሮፓና የአሜሪካ መንግስታት፣ ተጨማሪ እርዳታ የመስጠት አቅማቸው ተንጠፍጥፏል። እነሱ ራሳቸው፣ በኢኮኖሚ ድንዛዜና በበጀት እጥረት ተወጥረዋል። ብድርስ? ብድርስ አልጠፋም። ግን፣ ምን ዋጋ አለው? ብድር ሲደራረብ ያስፈራል። እንዴት ተደርጎ ከነወለዱ መመለስ እንደሚቻል እንጃ!
ምንም፣ መልካም ወሬ የለም ማለት ግን አይደለም። “እድሜ ለዳያስፖራ” ብንል ይሻላል። ለቤተሰብ የሚልኩት ገንዘብ፣ ከአመት አመት እየጨመረ መጥቷል። በ2007 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ብቻ፣ ከዳያስፖራ የመጣው ገንዘብ፣ ከ1.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው። በአመት፣ ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል። ከኤክፖርት ገቢ ይበልጣል ማለት ነው።
በጥቅሉ ሲታይ፣ በ2007 ዓ.ም፣ አገሪቱ በውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ጉድ ከመሆን የተረፈችው፣ በሁለት ምክንያቶች ነው ማለት ይቻላል - ‘ዳያስፖራዎች’ ለቤተሰብ የሚልኩት ገንዘብ በመጨመሩና በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ።

Read 5692 times