Monday, 31 August 2015 09:29

በ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ክፍል 3
በ5ሺ ሜ በሁለቱም ፆታዎችና በሴቶች ማራቶን ተጨማሪ ሜዳልያዎች ይኖራሉ፡፡
ገንዘቤ በ5ሺ ለሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያ ተጠብቃለች፤ ሪከርዱን ለመስበር እንደምትችልም ተናግራለች
በታክቲክ መበላሸት፤በቡድን ስራ ማነስና በአጨራረስ ድክመት ውጤት ጎድሎበታል፡፡
ከ1 ዓመት ያነሰ ጊዜ ለቀረው ኦሎምፒክ ከሳምንት በፊት በወንዶች ማራቶን የተጀመረው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  ነገ በሴቶች ማራቶን ፍፃሜውን ያገኛል፡፡ በዓለም  ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ ከ2 ዓመት በፊት በሞስኮ ያገኘችውን የ3 ወርቅ፤ ሁለት ብር እና የነሐስ ሜዳልያ ስኬት ለማሻሻል ይቅርና ለመድገም ፈተና ይሆንባታል፡፡ ሻምፒዮናው ዛሬ እና ነገ ሲቀጥል ኢትዮጵያ በ5ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ለተጨማሪ ሜዳልያዎች ተጠብቀዋል፡፡ ዛሬ በወንዶች 5ሺ ሜትር የ18 ዓመቱ ዮሚፍ ቀጀልቻ እና፤ ኢማና መርጋ ከ32 ዓመቱ ሞ ፋራህ ጋር ከባድ ትንቅንቅ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሞፋራህ በዓለም ሻምፒዮናው በ5ሺ ሜትር ለሶስት ጊዜያት አከታትሎ ለማሸነፍ የበቃ አትሌት መሆን እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡ በሌላ በኩል በነገው እለት በሴቶች ምድብ ማጣርያውን በከፍተኛ ብቃት ለማለፍ የቻሉት ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና በዋናነት እርስ በራሳቸው በሚያደርጉት ፉክክር የዓለም 5ሺ ሜትር ሪከርድ ሊሰበር እንደሚችል ግምት እየተሰጠ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጠችው የ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ገንዘቤ ዲባባ ‹‹ በ1500 ሜትር ማሸነፌ በራስ መተማመኔን ጨምሮታል፡፡ በፍፃሜ ሊገጥም የሚችለውን ማወቅ ባይቻልም፤ በጥሩ ብቃት ከተወዳደርኩ የ5ሺ ሪከርድን ሊሰብር የሚችል ፈጣን ሰዓት የማስመዘግብ ይመስለኛል፡፡›› በማለት ተናግራለች፡፡
ኬንያ እና የሜዳልያ ስብስብ ደረጃ
በቤጂንግ ከተማ በሚገኘው የወፍ ጎጆ ስታድዬም ላለፉት  ሰባት ቀናት ሲካሄድ በቆየው 15ኛው የዓለም አትሌቲስ ሻምፒዮና 207 አገራትን የወከሉ 1933 አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በ47 የውድድር መደቦች  በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ 36 አገራት ቢያንስ አንድ ሜዳልያ በማግኘት የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በሜዳልያ ስብስብ  ኬንያ 6 የወርቅ፤ 3 የብር እንዲሁም 2 የነሐስ ሜዳልያዎች በማስመዝገብ የደረጃ ሰንጠረዡን በአንደኝነት እየመራች ነው፡፡  አሜሪካ 3 የወርቅ፤4 የብር እና 5 የነሐስ ፤ጃማይካ 3 የወርቅ እና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች፤ ታላቋ ብሪታኒያ 3 የወርቅ፤ ፖላንድ 2 የወርቅ፣ 1 የብርና 3 የነሐስ ፤ኩባ 2 የወርቅ ፣ 1 የብር፤ ቻይና 4 የወርቅ ፣ 1 የብርና 4 የነሐስ፤  ጀርመን 1 የወርቅ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ፤ ኢትዮጵያ 1 የወርቅ እና ሁለት የብር ፤ እንዲሁም ካናዳ 1 የወርቅ 1 የብር እና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች በመሰብሰብ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ አከታትለው ይይዛሉ፡፡  ቤጂንግ ላይ ኬንያ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ ከፍተኛውን ስኬት እያስመዘገበች ነው፡፡ ሻምፒዮናው ሲጠናቀቅ የሜዳልያ ሰንጠረዡን በመሪነት የመጨረስ እድልም ይኖራታል፡፡ በሻምፒዮናው ለኬንያ  የወርቅ ሜዳልያዎች ያስመዘገቡት  በ800 ሜትር ዴቪድ ሩዲሻ፤ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በ400 ሜትር መሰናክል ኒኮላስ ቤት፤ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ወንዶች እዝኬል ኬምቦሚ፤ በ10ሺ ሜትር ሴቶች ቪቪያን ቼሮይት፤ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ሴቶች  ኪያን ጄፕኮሚ እንዲሁም በጦር ውርወራ ጁሌዬስ ዮጎ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የኬንያ የወርቅ ሜዳልያ ውጤቶች በ400 ሜትር መሰናክል እና በጦር ውርወራ ያገኘቻቸው በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ በ3ሺ ሜትር መሰናክል የሚያሳዩት የበላይነት መቀጠሉም የሚያስገርም ይሆናል፡፡ ኬንያ በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ በአጭር ርቀት ምርጥ አትሌቶች የነበሯት ሲሆን ማናጀሮች እና አሰልጣኞች ወደ ረጅም ርቀት በማተኮራቸው አት ውጤታማነታቸው ቀንሷል፡፡ በሜዳ ውድድር ግን ኬንያ የሜዳልያ ስኬት ስታገኝ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን ለኢትዮጵያም ትልቅ ትምህርት የሚሆን ነው፡፡ ኬንያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዶፒንግ በተያያዘ 40 አትሌቶች በላይ መከሰሳቸው  በስፖርቱ ያላትን ክብር እያጎደፈው ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ከዓለም ሻምፒዮናው ጋር በተያያዘ 2 አትሌቶች ከዶፒንግ በተያያዘ መከሰሳቸው የኬንያን ሰኬት ያደበዘዘው መስሏል፡፡ 2 አትሌቶች በ400 ሜትር ወንዶች እና በ400 ሜትር መሰናክል የሚሳተፉት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያን የከዳችው ማራቶን ልዕልቷ
በማራቶን በዓለም ሻምፒዮና ታሪክ ወጣቱ የማራቶን አሸናፊ ለመሆን የበቃው የ19 ዓመቱ ግርማይ ገብረስላሴ ነው፡፡ የወርቅ ሜዳልያውን የወሰደው ርቀቱን  በ2 ሰዓት ከ12 ደቂቃዎች ከ27 ሰከንዶች በመሸፈን ነው፡፡  ኢትዮጵያዊው የማነ ፀጋዬ የዓመቱን የግሉን ፈጣን ሰዓት በ2 ሰዓት ከ13 ደቂቃዎች ከ07 ሰከንዶች  በሆነ ጊዜ አስመዝግቦ የብር ሜዳልያውን ወስዷል፡፡ የኡጋንዳው ሙኖዮ ሰለሞን በ2 ሰዓት ከ13 ደቂቃዎች ከ29 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ የነሐስ ሜዳልያውን ለመጎናፀፍ በቅቷል፡፡  በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች ከ1 በላይ የወርቅ ሜዳልያ አግኝታ አለማወቋ ከቤጂንግ በኋላም ቀጥሏል፡፡ በ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመክፈቻ ውድድር በሆነው ማራቶን ላይ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነት ይታይበት ነበር፡፡ የጣሊያን አትሌቶችም ያሳዩት ፉክክር ሊደነቅ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች  ግን ባላቸው ልምድ ተጠቅመው ውጤታማ መሆን ሲገባቸው ውድድሩን በመቆጣጠር ማራቶኑን መቆጣጠር አልቻሉም፡፡  በማራቶን አሰልጣኞች በኩል የሚሰሩ ተግባራት ተገምግመው የሆነ መዋቅር ሊፈጠር ይገባዋል፡፡ ግማሾቹ አትሌቶች በራሳቸው፤ ሌሎቹ በባሎቻቸው እንዳንዶቹ በማናጀሮቻቸው የሚሰለጥኑበት ሁኔታ ውጤት እያበላሸ መቀጠል የለበትም፡፡  በሌላ በኩል የዓለም ማራቶን ሪከርድን አከታትለው የሰበሩት ሁለት ኬንያውያን  አትሌቶች ከሜዳልያ ውጭ መሆናቸውም ያልተጠበቀ ሲሆን፤ በሌላ በኩል የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ስቴፈን ኪፕሮችም ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ ከየማነ ፀጋዬ የብር ሜዳልያ ባሻገር  ኢትዮጵያዊያኑ ሌሊሳ ዴሲሳ 7ኛ እንዲሁም ለሚ ብርሃኑ 15ኛ ደረጃ አግኝተው ውድድሩን የጨረሱት፡፡ የብዙ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማናጀር የሆኑት ሆላንዳዊው ጆስ ሄርማንስ ስለ ኤርትራዊው አትሌት ግርማይ ገብረስላሴ በሰጡት አስተያየት በቺካጎ ማራቶን በአሯሯጭነት መሳተፉን በዱባይ ማራቶን ሲሳተፍ አቋርጦ መውጣቱን ገልፀው ሳይጠበቅ ማሸነፉ አስገርሞኛል ብለዋል፡፡ በሞቃት አካባቢ ልምምምድ ሲሰራ መቆየቱን የገለፀው ኢትዮጵያዊው የብር ሜዳልያ ባለቤት የማነ ፀጋዬ በበኩሉ ልምድ እንዳለኝ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ውድድሩ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ከ35 ኪሎሜትር በኋላ ጨጓራ ህመም ገጠመኝ በዚህ ምክንያት ግርማይ አምልጦኝ በመሄድ ሊያሸንፍ ችሏል ብሎ ተናግሯል፡፡
አጨራረሱ የማያምረው የኢትዮጵያ አትሌቶች  የመሰናክል ሩጫ
በ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድሮች ከኢትዮጵያ አትሌቶች የተሻለ ፉክክር ማሳየት የሆነላቸው ሴቶች ናቸው፡፡  በሁለቱም ፆታዎች በ3ሺ መሰናክል ኬንያውያን ፍፁም የበላይነት ማሳየታቸው አልቀረም፡፡ በወንዶች ምድብ ኬንያዊው ኢዝኬል ኬምቦሚ ለ4ኛ ተከታታይ የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ በመውሰድ ሲሳካለት እስከ አረተኛ ደረጃም ተከታትለው ገብተዋል፡፡ ማጣርያውን አልፈው ለፍፃሜ መድረስ የቻሉት ቶሎሳ ኑርጊ እና ሃይለማርያም አማረ በፍፃሜው ሲሳተፉ የተለየ ቴክኔክ እና የቡድን ስራ ስላልነበራቸው በአጨራረስም ደካማ በመሆናቸው ከሜዳልያ ፉክክር ውጭ የሆኑት በቀላሉ ነው፡፡ በፍፃሜው ውድድር አሁንም ለኢትዮጵያ የሜዳልያ እድል አጠያያቂው  ሁኔታ የወንዶቹ አትሌቶች የአጨራረስ ብቃት ደካማ መሆኑ ነው፡፡በ3ሺ መሰናክልም በሴቶች ለፍፃሜ የበቁት  ሶፍያ አሰፋ እና ህይወት አያሌው ያላቸውን የዳበረ ልምድ በመጠቀም የተሻለ ፉክክር ቢያሳዩም አጨራረስ ላይ የተለየ ዝግጅት ስላልነበራቸው ውጤቱ ሳይሆንላቸው ቀርቷል፡፡
ለኢትዮጵያ ዱባ እዳ እየሆነ የመጣው 10ሺ
በ10ሺ ሜትር ወንዶች የሞ ፋራህ የበላይነት በቤጂንግም ቀጥሏል፡፡ በውድድሩ የታየው ፉክክር የምንግዜም ምርጥ እየተባለም ሲሆን የኢትዮጵያውያኑ ከጨዋታ ውጭ መሆን ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ የኬንያ አትሌቶች በውድድሩ ላይ በተጠቀሙት የቡድን ታክቲክ ኢትዮጵያውያንን ከፉክክር ውጭ ማድረግ ቢችሉም  ከሞፋራህ ጋር ከባድ ትንቅንቅ ገጥሟቸው የወርቅ ሜዳልያውን ሊነጥቁት አልቻሉም፡፡ ሞፋራህ በ10ሺ ሜትር ንግስናውን ለመቀጠል የበቃው ርቀቱን በ27 ደቂቃዎችከ01.13 ሰከንዶች ጊዜ በመሸፈን ሲሆን፤ ሁለቱ ኬንያያን ጄዮፍሪ ኪፕሳንግ እና ፖል ታንዊ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎች አግኝተዋል፡፡ የአሜሪካው ጋለን ሩፕ ደግሞ ከኢትዮጵያውያን የተሻለ ብቃት አስመዝግቦ ሲጨርስ፤ ድሮ ከፍተኛ የበላይነት በማሳየት የሚታወቁት የኢትዮጵያ አትሌቶች ዙር ማክረራቸው ሲጠበቅ ዙሩ ከሮባቸው ከፉክከሩ ተቆርጠው ለመውጣት ተገደዋል፡፡ ይሄው የኢትዮጵያ አትሌቶች ደካማ ብቃት የረጅም ርቀት የምንግዜም ምርጥ አትሌት የሆነው ቀነኒሳ የታል የሚል ጥያቄም በስፖርቱ ቤተሰብ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት የኢትዮጵያ  አትሌቶች በወንዶች 10ሺ ሜትር ከ1 እስከ 10 ባለው ደረጃ ይወጡ የነበረ ቢሆንም ቤጂንግ ላይ የተሳተፉት አትሌቶች ባልተጠበቀ ሁኔታ ከዚህ ብቃት መውረዳቸው  አሳሳቢ ሁኔታ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የተጠበቀው ኢማና መርጋ ውድድሩን አቋርጦ ለመውጣት ሲገደድ ሌሎቹ አትሌቶች ከ10ኛ በኋላ በመጨረስ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ የወረደ ውጤት ለማስመዝገብ ተገድደዋል፡፡
በሴቶች 10ሺ ሜትርም ብዙ የሚያበረታታ ነገር አልታየም፡፡ የወርቅ ሜዳልያውን የወሰደችው ወልዳ ከተነሳች 1 ዓመት እንኳን ያልሞላት ቪቪያን ቼሮይት ናት፡፡ ኬንያዊቷአትሌት ለሁለተኛ ጊዜ በዓለም ሻምፒዮና ጥሩነሽ በሌለችበት የተለመደውን የወርቅ ሜዳልያ ከኢትዮጵያ በመንጠቅ ማሸነፏም ነው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ለ10ኛ ጊዜ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ መውሰዳቸው አንድ የሚያኮራ ሁኔታ ነው፡፡በዚህ ውድድር በርቀቱ ብዙም ልምድ የሌላት ገለቴ ቡርቃ በሩጫ ዘመኗ ከፍተኛ የሚባለውን ውጤት በብር ሜዳልያ ማስመዝገቧም ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይሁንና በመጨረሻዎቹ 100 ሜትሮች ገለቴ ቡርቃ የወርቅ ሜዳልያውን ለመውሰድ ያደረገችው ሙከራ በአጨራረስ ላይ ብዙ ባለመስራቷ የተሳካ አልነበረም፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የወርቅ ሜዳልያ ያሸነፈችውን ጥሩነሽ ዲባባ ተከትላ በመግባት የብር ሜዳልያ የወሰደችው በላይነሽ ኦልጅራ ከሜዳልያ ውጭ ሆና ስትጨርስ ብዙም ልምድ ያልነበራት አለሚቱ ሃሮዬ ተፎካካሪነት አልነበራትም፡፡ አሜሪካዊት አትሌት በዚህ ውድድር የነሐስ ሜዳልያ ለመውሰድ መብቃቷ ተፎካካካሪነታቸው እያደገ መምጣቱን ያሳየ ነበር፡፡
በ1500 ሜትር የገንዘቤ ወርቅ የተሻለው ውጤት
በ1500 ሜትር ሴቶች ገንዘቤ ዲባባ የወርቅ ሜዳልያውን በፍፁም የበላይነት ለመውሰድ በቅታለች፡፡ እስከትናንት ኢትየቶጵያ ያስመዘገበችው ትልቁ ስኬትም ነው፡፡ ገንዘቤ የዓለም ሪከርድን ዘንድሮ እንደማስመዝገቧ ውጤቱን የተለየ ባያደርገውም የወርቅ ሜዳልያው በርቀቱ በኢትዮጵያ የዓለም ሻምፒዮና ታሪክ ለኢትዮጵያ የመጀመርያው፤ ለራሷ ገንዘቤ በዓለም ሻምፒዮናው በትራክ የመጀመርያ የወርቅ ሜዳልያ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በሴቶች 1500ሜ ለሶስቱ ሜዳልያዎች ጠቅላይነት የኢትዮጵያ 3 አትሌቶች ከመጀመርያው ዙር ማጣርያ በኋላ ተጠብቀው ነበር፡፡ ከገንዘቤ ጋር ለፍፃሜ የደረሰችው ዳዊት ስዩም ሜዳልያ ውስጥ ለመግባት ከባድ ፉክክር የገጠማት ከትውልደ ኢትዮጵያዊቷና ለሆላንድ የምትወዳደረው ሰይፋ ሃሰን ነበር፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የሜዳልያ ድል ያስመዘገበችው በ1999 እኤአ ላይ የነሐስ ሜዳልያ የወሰደችው ቁጥሬ ዱለቻ  የነበረ ሲሆን ገንዘቤ ዲባባ የወርቅ ሜዳልያ ካገኘች በኋላ ግን በርቀቱ በሴቶቹ ምድብ በዓለም ሻምፒዮናው የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ለማለት ይቻላል፡፡
የመሃመድ  ክብርን የማስጠበቅ ህልም በቴክኒክ ስህተት መበላሸቱ
በ800 ሜትር ወንዶች የመሃመድ አማን ክብር የማስጠበቅ  ከፍተኛ ትንቅንቅ በግማሽ ፍፃሜ  በተፈጠረው ያልተጠበቀ ሁኔታ ተበላሽቶበታል፡፡  በ3 ምድብ በተካሄደው የግማሽ ፍፃሜ ፉክክር በመጀመርያ ዙር ገብቶ የነበረው የወቅቱ ሻምፒዮን መሃመድ አማን በመጨረሻዎቹ ሁለት መቶ ሜትሮች የገጠመው ነገር በወቅቱ ውድድሩን ሲያስተላልፍ በነበረው ኮሜንታተር አገላለፅ እሱን ከመሰለ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው አትሌት የማይጠበቅ ነበር፡፡  መሃመድ አማን የ800 ሜትር ውድድሩ ሊጠናቀቅ በቀሩት የመጨረሻዎቹ ሁለት መቶ ሜትሮች በተፎካካሪ አትሌቶች ከተከበበበት  ሁኔታ ለመውጣት  በግራ በኩል ለማለፍ ያደረገው ሙከራ በሱ እና በሌላ አትሌት ላይ በፈጠረው መደነቃቀፍ ተበላሽቶበታል፡፡
 ሻምፒዮናነቱን የማስጠበቅ እድሉ አጣብቂኝ የገባውም በዚህ ክስተት ነበር፡፡ በሶስቱ የግማሽ ፍፃሜ ማጣርያዎች አንደኛና ሁለተኛ የወጡት በቀጥታ አልፈው መሃመድ አማን በግማሽ ፍፃሜው ያገኘው ፈጣን ሰዓት ከሶስተኛ ደረጃው ጋር በምርጥ ሶስተኛነት ሊያሳልፈው ቢችልም በተሰጠው እድል መሰረት ለፍፃሜ ቢያደርሰውም  ከውድድሩ ውጭ የሆነው በዚያው መደነቃቀፍ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ በ800 ሜትር ወንዶች ብቸኛውና  የመጀመርያው የወርቅ ሜዳልያ ድል የተመዘገበው ከሁለት ዓመት በፊት በመሃመድ አማን እንደነበር ይታወሳል፡፡

Read 3096 times