Saturday, 15 August 2015 16:01

በጁሊያን አሳንጄ ላይ የተመሰረቱት ሶስት ክሶች ተቋረጡ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  የስዊድን ፍርድ ቤት አቃቤ ህጎች ዊኪሊክስ የተባለው አለማቀፍ ሚስጥር ጎልጓይ ድረገጽ መስራች በሆነው ጁሊያን አሳንጄ ላይ ከቀረቡት የተለያዩ የወንጀል ድርጊት ክሶች መካከል ሶስቱን ውድቅ ማድረጋቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የስዊድን ፍርድ ቤት አቃቤ ህጎች ሃሙስ እለት እንዳስታወቁት፤ በአሳንጄ ላይ ከቀረቡት ውንጀላዎች ሶስቱ ክስ መመስረት ከሚገባው ጊዜ አልፎ የቀረቡ በመሆናቸው ውድቅ የተደረጉ ሲሆን፣ በ2010 የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽሟል በሚል የቀረበበት ክስ ግን መታየቱን ይቀጥላል፡፡ አሳንጄ በስዊድን ከተላለፈበት የእስራት ትዕዛዝ በማምለጥ ከሰኔ ወር 2012 ጀምሮ ለንደን ውስጥ በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ጥገኝነት አግኝቶ እየኖረ እንደሆነ ያስታወሰው ዘገባው፤ውድቅ የተደረጉለት ወንጀሎች ክስ መመስረት ከሚገባቸው የአምስት አመት የጊዜ ገደብ አልፈዋል መባሉን ጠቁሟል፡
የ44 አመቱ አውስትራሊዊ አሳንጄ የቀረቡበትን የወንጀል ክሶች በሙሉ መካዱን  ያስታወሰው ዘገባው፣ በሺህ ዎች የሚቆጠሩ አሜሪካን የሚመለከቱ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ይፋ በማውጣቱ ሳቢያ እየተደረገበት ካለው ምርመራ ጋር በተያያዘ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዳይሰጥ በመስጋት ወደ ስዊድን እንደማይመለስ መናገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2740 times