Saturday, 15 August 2015 15:52

ዛሬም እንደትላንቱ እንዳይሆን...?!

Written by  አለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(9 votes)

ዛሬም … ?
… ድርቅ ተንጠርብቧል፣ ደግሞ ረሃብ ሊዘንብ? እልቂት ከመሬት ሊፈላ? መፈናቀል ሊያንሰራራ? እዬዬ ሊያስተዳድረን? ዋዬ ሊውጠን?...
ያኔ …
… “አዬ ሰባ - ሰባት ባልተወለድኩኝ፣
እናቴ ከእጄ ላይ ጥሬ ስትቀማኝ” ያልነውን፤
ዛሬም …
… “ሁለት ሺህ ሰባት ባልተወለድኩኝ፣
እናቴ ከእጄ ላይ ጥሬ ስትቀማኝ”ን ልንደግም?
ተፈጥሮ እናትን ከቀማች፤ ከእናት ውስጥ ባላንጣ ከፈጠረች ከዚያ ወዲያ ምን አለ? ለሰውልጅ ምን ተረፈው? ለመኖር ምን አጓጓው? … ልንል?
ዛሬም …?
… በችጋር መጠራሞት፣ መቃተት የትውልድ ፅዋ ሆኖ “ማነህ ባለሳምንት” ልንባል? በባዶ እንቅብ መናቸፍ፣ በወና አቅማዳ መንሳፈፍ … ሊደገም? ስጋችን እንደ እፍየ ገላ ሊያመልጥ፣ አይናችን አጥንታችንን ሰርስሮ ሊሰምጥ? … በእንባ አቀባባይነት፣ በሰቀቀን አደራ አስቀማጭነት ሁለት ትውልድ ልናማክል?...
… ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “ረሃብና ተስቦ በኢትዮጵያ” በተሰኘ ጥናታቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፡-
“ከታሪካችን ታላላቅ ምዕራፎች አንዱ የሚመሰክረው የኢትዮጵያን የልጆች ደም ጠጥቶ፣ በልጆቿ ሥጋ ዳብሮ፣ የልጆቿ አጥንት የሚረመረምበት መሆኑን ነው፡፡ ገበሬዎቹ ሰለስቱ አጋእዝት ወይም ሰልስቱ አጋንንት፣ ርኀብ፣ በሽታ ገዢዎቻችን ናቸው፡፡”
 ዛሬም …
… የገባሪ ልጅ ጭሰኛ ሆነን እኛም ደማችን ለጥማቱ፣ ሥጋችን ለመዳበሩ፣ አጥንታችን ለመረማመጃው ሊውል? ምን ይሉት ዕጣ፣ እንዴት ያለው የዘር በሽታ ይሆን?...
… ከሰባ ሰባቱ ረሃብ በኋላ ስንት ረሃቦች ተግተለተሉ? ሰማኒያ ሁለት፣ ሰማኒያ ሶስት፣ ዘጠና ሁለት፣ ዘጠና ሰባት … አራት የረሃብ ቶርፒዶዎች፤ አገር የነቀነቁ… እንደሽፍታ ተደብቆ አካባቢ የሚያሸብረው ትናንሽ ረሀብ ሳይቆጠር ማለት ነው፡፡ ቶም ፍራክሊን የተሰኘ አሜሪካዊ ስለነዚህ ድብቅ የሽፍታ ባህርይ ያላቸው ርሃቦች እንዲህ ሲል አትቶ ነበር፡- “During the 20 - year period, between 1958 and 1977 about 20% of the country was under famine condition each year.” (በ1958 እና 1977 ዓ.ም መካከል ለሃያ ዓመታት ያህል የአገሪቱ ሃያ ከመቶ አካባቢ በየዓመቱ በረሃብ ይጠቃ ነበር፣) ይልና ከእነዚህ ሃያ ረሃቦች መካከል አንዱ ብቻ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ እንደዳሰሰው ይጠቁማል፡፡ እሱም በ1965 ዓ.ም የተከሰተው ረሃብ ነው። ፍራንክሊን አስራ ዘጠኙ ረሃቦች ከስልሳ አምስቱ ረሃብ በእልቂት አይተናነሱም ነበር ይላቸዋል፡፡
ታዲያ፤ አንዱን ብቻ ምን አገኘው? “ፖለቲካ” ይላል - ፍራንክሊን፡፡ ከአፄ ኃይለሥላሴ ሰማኒያኛ የልደት በዓል ጋር ረሃቡ በመግጠሙ የብሶት ማግለብለቢያ ተደረገ፡፡ ለአንድ ንጉስ ኬክ ትልቅ ነገር ሆኖ ሲቆርሱ የተነሱት ፎቶ አላማውን ስቶ ለአልጋ ነጣቂዎች ፍጆታ ዋለ፡፡
“ረሃብ” እንዲያ ነው ለእኛ፡፡ የፖለቲካ ማርሽ መቀየሪያ፡፡ አፄ መንግሥቱ ኃይለማሪያም  ለጠላቶቻቸው የፕሮፓጋንዳ ግልጋሎት እንደተጠቀሙበት ማለት ነው። አስረኛው የአብዮት በዓል ከሰባሰባቱ ረሃብ ጋር ገጥሞ ሁለት መቶ ሚሊዮን ዶላር ለዊስኪና ለአብረቅራቂ መብራት ተመደበ። ለዚህም ሁለት ሚሊዮን ህዝብ በልዋጭ ለሞት ተዳረገ፡፡
ረሀብ ከነኩት፣ ካንጎዳጎዱት ብዙ ነው። ከዚያ ወጥተን ወደ ሌላ አቅጣጫ እንማትር፡፡ በተንጠረበበው ድርቅ፣ በሚዘንበው የረሃብ ዶፍ መካከል “ብልጭ” የምትል የጥበብ ፀሐይ አለች፡፡ አልፎ አልፎ ቢሆንም ቅሉ፡፡ አንዱ ከቁጭት ሌላው ከህይወት እየጨለፈ የገመምተኛ ሣቅ ያስፈግጋታል፡፡ ፀጋዬ ገብረመድህን ረሃብን የቁጭት ቁጨት አድርጎ በግጥም አፍተልትሎታል፡፡ “ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል?” በሚል።
ረሃብ ቀጠሮ ይሰጣል?
ወይስ ቀን ቆጥሮ ይፈጃል?
“የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል”
ይባላል፣ ድሮም ይባላል
ይዘለዝላል ይከትፋል
ብቻ እስከሚጨርስ ድረስ ሆድ ለሆድ ጊዜ ይሰጣል?
ወተት አንጀት ነጥፎ ሲላብ
ሆድ ዕቃ ደርቆ ሆድ ሲራብ
ተሟጦ አንጀት በአንጀት ሲሳብ …
የጣር ቀጠሮው ስንት ነው
ለሰው ልጅ ሰው ለምንለው
ላይችል ሰጥቶ ለሚያስችለው
ስንት ቀን ነው? ስንት ሌት ነው?
ፀጋዬ የግጥም ሱባኤ ገብቶ ረሃብተኛንና ረሃብን የሆነበት ሥራው ነው፡፡ ድቅድቁ ረሃብ እንደ ድንኳን ሸራ  ተሸንትሮ ለእዝን ጥላ ተካስሟል፡፡ ማዘኛ ዳስ ሆኗል፡፡
የማዕዱ ወዝ ሳታጥጥ
አድባሩ አብዳ ሳትፈረጥጥ
ጥንብ ላይተርፋት ሜዳ  - አይጥ
የቤት ድመት ሳታማምጥ
በእመቤቷ አስከሬን ብካይ
እሷም ዋይ አንጀቷም ዋይ - ዋይ
ውሻም በጌታው ሥጋ ላይ
ቸነፈር በጣለው ሲሳይ
አይ! ….
ረሃብ ሰው ሲዘነጥፍ፣ ከእርሱ ጥበብ ማትረፍ አይበልጥም፡፡ ግን ደግሞ ሲያመልጥም ትርፍ የለውም። እንደውም የአንዳንድ ባለቅኔ ልብ ከሰርግ ቤት ይልቅ ሀዘን ቤት ማሰስ ይቀናዋል፡፡
ዛሬም … ?

Read 4792 times