Saturday, 01 August 2015 14:33

የቢዝነስ ስብሰባ ኢንዱስትሪ - ያልተነካው ሃብት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

ቅንጡዎቹ የአፍሪካ ህብረትና ኢሲኤ አዳራሾች አልተዋወቁም
                   ብዙ ዓለማቀፍ ስብሰባዎችን በማስተናገድ አሜሪካ ትመራለች
                                 
         ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ዓለማቀፍና አህጉራዊ ትልልቅ ስብሰባዎችን እያዘጋጀች ነው። በዚህም አዲስ አበባ የቱሪዝም ኮንፈረንስ ከተማ እየሆነች መምጣቷ ይነገራል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት እንኳ 7 ሺህ ያህል እንግዶች የተሳተፉበትን 3ኛውን ፋይናንስ ለልማት ኮንፈረንስ በብቃት መወጣቷን፣ ተሳታፊዎች መደሰታቸውንና በአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት መደነቃቸውን ታዛቢዎች ተናግረዋል፡፡
አገሪቱ በዓለም የቱሪዝም መዳረሻነትና በኮንፈረንስ ቱሪዝም እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ በዘርፉ ባለሙያ የሆኑትን አቶ ቁምነገር ተከተልን አነጋግሬአቸዋለሁ፡፡ ባለሙያው በአዲስ አበባ ሦስት ጊዜ የተሳካ የሆቴል ሾውና ኢትዮጵያ ኤግዚቢሽን ፎረም ያካሄዱ ሲሆን ማይስ (MICE) ኢስት አፍሪካ የተባለ ድርጅት መስርተው፣ በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ 4ኛውን “ሆቴል ሾው አፍሪካ 2016 ፎረም እና ኤክስፖ” ለማካሄድ ዝግጅት እያጠናቀቁ ይገኛሉ፡፡ አቶ ቁምነገር፤የኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር እንዲሁም የሆቴሎች አማካሪም ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ካሏት የቱሪስት ሀብት አኳያ ከዚህ በፊት ይህ ነው የሚባል የሰራቸው ነገር ባለመኖሩ እውቅናው ዘገየ እንጂ በጣም ጥሩ ነው ይላሉ - ባለሙያው፡፡ ቱሪዝም የመዝናናትና የቢዝነስ (ኮንፈረንስ ቱሪዝም) በመባል በሁለት ይከፈላል፡፡ ኮንፈረንስ ቱሪዝም፤ በአሁኑ ወቅት ጊዜ ያለፈበትና ያረጀ አባባል ስለሆነ በማይስ (MICE) አስተሳሰብ ተተክቷል ብለዋል- አቶ ቁምነገር፡፡ እንዴት? ማይስ ደግሞ ምንድነው? በማለት ጠየቅሁ፡፡
ማይስ (MICE) M (meeting) ስብሰባ፣ I ኢንሴንቲቭስ (ማበረታቺያ ማነቃቂያ) C - ኮንፈረንስ/ኮንግረስ እና E ኤግዚቢሽን/ኤቨንት ማለት ነው ሲሉ ማብራሪያቸውን ቀጠሉ፡፡
ስብሰባ ፡- ከ2 ሰዎች ጀምሮ እስከ 1000 ሰዎች የሚያደርጉት የንግድ፣ የቤተሰብ ወይም ማንኛውም የአንድነት ግንኙነቶች ነው፡፡ ኢንሴንቲቭስ ትራቭል (ማበረታቻ፣ ማነቃቂያ፣ ማትጊያ) ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በዱባይ የኖኪያ ወይም የሳምሰንግ፣ …  ኩባንያ በዓመቱ ባደረገው እንቅስቃሴ አገኛለሁ ብሎ ካቀደው በላይ የላቀ ትርፍ በማግኘቱ ለሰራተኞቹ ወጪ ችሎ ኢትዮጵያ ወይም ወደመረጡት አገር ሄደው እንዲዝናኑ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከዚህም ጋር ተያያዥነት ያላቸው የሎያሊቲ ጥቅማጥቅሞችን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡
ኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚባለው ከ1000 እስከ 3000 የሚደርሱ ሰዎች የሚሳተፉበት ስብሰባ ነው። ተሳታፊዎቹ ከ3000 ሰዎች በላይ ከሆኑ ኮንግረስ ይባላል፡፡ ለዚህ ነው አንዳንድ ጊዜ MICE እየተባለ የሚጠራው፡፡ ኤግዚቢሽን/ ኢቨንት፤ ኮንሰርት፣ የሃይማኖት ፕሮግራም፣ አነስ ያለ ስብሰባ፣ ሩጫ፣ ቅስቀሳ (ካምፔይን) … ወይም ኤግዚቢሽን ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ኤግዚቢሽኑን የሚያዘጋጀው ኩባንያ፣ ሌሎች ድርጅቶችና ኩባንያዎች በትርዒቱ እንዲሳተፉ ይጋብዛል፡፡ የተሳታፊዎቹ ወጪ የሚሸፈነው በተሳታፊው ድርጅት ወይም ኩባንያ ነው፡፡
በኤግዚቢሽኑ የሚሳተፉ ሰዎች የአውሮፕላን ቲኬት፣ በሚቆዩበት ቀን ታስቦ የአልጋ፣ የምግብ፣ … ወጪ በላኪው ኩባንያ ይሸፈናል፡፡ በኤግዚቢሽኑ ለሚቀርቡ ዕቃዎች የአውሮፕላን ኪራይ ድርጅቱ ይከፍላል፡፡ ስለዚህ ተሳታፊዎቹ የተሰጣቸውን ገንዘብ ለማጥፋት አይሰስቱም፣ አይቆጥቡም። እንዲያውም በሚሄዱበት አገር፣ የሚገኝ ረከስ ያለ ነገር ወይም መታሰቢያ ለመግዛት የራሳቸውን ገንዘብ ይዘው ሊጓዙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ከአገራቸው ይዘው የተነሱትን ዶላር ኤግዚቢሽኑን ባዘጋጀው አገር ያጠፋሉ እንጂ ይዘውት አይመለሱም፡፡
ኮንፈረንስ ቱሪዝም ከማይስ ውስጥ አንድ ዘርፍ ነው፡፡ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች ስላሉት የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ያስፈልጋል። ለምሳሌ በቅርቡ በአገራችን የተካሄደው 3ኛው ፋይናንስ ለልማት ኮንፈረንስ እንዴት እዚህ እንደተካሄደ እንይ፡፡
ስብሰባዎች የመንግሥት ኮሚትመንትና የቢዝነስ ሞዴል ስብሰባ በመባል በሁለት ይከፈላሉ። በመንግሥት ኮሚትመንት የሚመጣ ስብሰባ አድካሚና አንዳንድ ጊዜም ወጪ ያለው ነው፡፡   መንግስት፤ “3ኛው ፋይናንስ ለልማት፤በኢትዮጵያ መካሄድ አለበት፡፡” ብሎ የማሳመን ስራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም ተጨባጭ ስራዎችን መስራቱ የሚታይ ነው፡፡
መንግሥት ስብሰባውን ለገጽታ (ኢሜጅ) ግንባታ ጠቃሚ መስሎ ከታየው አስፈላጊውን ሥራ ሰርቶ አንዳንድ ወጪዎችን እሸፍናለሁ ሊል ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ የገጽታ ግንባታ ሊያገኝ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር የገጽታ ግንባታ ሲደረግ የንግድ ትስስሩም ሊመጣ ይችላል፡፡ እንዲሁም ተጨማሪ የኢንቨስትመንት አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡
ማይስ (MICE) ማለት የቢዝነስ ስብሰባ ነው። በሌሎች የቱሪዝም ስራዎች የሚገኘው ጥቅም ከማይስ ጋር በፍፁም ሊወዳደሩ ቀርቶ ሊቀራረቡ እንኳ አይችሉም፡፡ ከማይስ የሚገኘው ጥቅም ከሌሎቹ አምስት እጅ ይበልጣል፡፡ ማይስ ትልቅ የገቢ ማግኛ ስለሆነ ኢትዮጵያም ማይስን ጠቃሚዬ ነው፤ ገበያዬ ነው፣ … ብላ አጥብቃ መያዝ አለበት፡፡
ዓለም ማይስ ማይስ ማለት ሲጀምር ብልጦቹ የበለፀጉት አገሮች ትልልቅ የስብሰባ አዳራሾችን፣ (የኮንቬንሽ ቦታዎችን) … ማዘጋጀት ጀመሩ። መሰብሰቢያ ቦታዎችን ስለሰሩ ብቻ ገበያ አይመጣም። ራሳቸውን ማስተዋወቅና መሸጥም አለባቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት (የመሰብሰቢያ ቦታ) ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ ቅንጡዎቹ የአፍሪካ ኅብረትና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ)፣ ሚሊኒየም  አዳራሽ፣ ዓለም የደረሰበት  የቴክኖሎጂ ውጤት (ስቴት ኦፍ አርትስ) የተገጠመለትና 2000 ሰዎች መያዝ የሚችለው የባህርዳር ዘመናዊ አዳራሽ፣ ስታዲየሞች፣ … ሌሎችም አሉ፡፡ የማስተዋወቅ ሥራ ስላልተሰራላቸው እንጂ ቅንጡዎቹ የአፍሪካ ኅብረትና ኢሲኤ አዳራሾች እንደ ትልቅነታቸው በየሳምንቱ ከ1000 እስከ 3000 ስብሰባዎች ማስተናገድ ነበረባቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት አዳራሾች በሌሎች አብዛኛው የአፍሪካ ሀገሮች አይገኙም፡፡ በእነዚህ አዳራሾች በየሳምንቱ 1000 ሰዎች ቢስተናገዱ በትራንስፖርት፣ በአየር መንገዱ፣ በሆቴሉ፣ በሸቀጡ፣ በባህል ዕቃው ግዢ ፣… የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ (የገንዘብ ልውውጥ) የትየለሌ ነው፡፡
ይህን የማይስ ትሩፋት የወሰዱት እነዚያው የበለፀጉት አገሮች ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ብዙ ትልልቅ ስብሰባዎች የሚካሄዱት የት ነው? ቢባል አሜሪካ ነው፡፡ በአሜሪካስ፤ በየትኛዋ ከተማ ነው? ቢባል አብዛኛው ሰው ኒውዮርክ ወይም ዋሽንግተን ሊመስለው ይችላል፡፡ ሁለቱም አይደሉም፡፡ በረሃ ላይ የተቆረቆረችውና የዓለም ሀብታሞች መዝናኛ የሆነችው ላስቬጋስ ናት፡፡ በዚያች ከተማ 2000፣ 3000፣ 5000፣ 10000፣ … ሰዎች የሚያስተናግዱ አዳራሾች አሉ፡፡ 2000፣ 3000፣ 4000፣ 7000፣ … አልጋዎች ያላቸው ሆቴሎች ናቸው እዚያ ያሉት። ወደ መኝታ ቤት ስትሄድ፣ በዚህ አልፈህ፣ ይህን አቋርጠህ፣ ወደ ግራ ዞረህ፣፣ ወደ ቀኝ ታጥፈህ፣ … ነው ክፍልህን የምታገኘው ተብሎ የምታነበው ካርታ ይሰጥሃል፡፡
በቅርቡ በወጣው መረጃ መሰረት፤ በዓለም ብዙ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች የምታካሂደው አሜሪካ ናት። 2ኛ ጀርመን፣ 3ኛ ፈረንሳይ፣ 4ኛ ስፔይን ናቸው። እነዚህ አገሮች ሥራዬ ብለው በዓለም የሚካሄዱ ስብሰባዎችን የሚከታተል ቡድን ወይም መ/ቤት አላቸው፡፡ መ/ቤቶቹ ስራቸው ስብሰባዎችንና ኤግዚቢሽኖችን ማሳደድ ወይም በየአገሩ የሚካሄዱ ኤግዚቢሽኖችን ፕሮሞት በማድረግ ብዙ ሰዎች እንዲሳተፉ መቀስቀስ ነው፡፡
ኤክስፖ ሲዘጋጅ ሆስትድ ባየርስ (ተጋባዥ ገዢዎች) እናመጣለን፡፡ እነዚህ ሰዎች ስብሰባዎች የት እንደሚካሄዱ የሚወስኑ ናቸው፡፡ የስብሰባ ተሳታፊዎች 10ሺህ ወይም 50 ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ዓመታዊ የማኔጅመንት ስብሰባው የት መካሄድ እንዳለበት የሚወስኑ የህዝብ ግንኙነትና የማኔጅመንት አባላት አሉ እንበል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ስብሰባ ለማካሄድ ወስኖ 1000 ሰው የሚይዝ አዳራሽ እንዲዘጋጅላቸው ሲጠይቁ፣ የህዝብ ግንኙነት ክፍሎች ሎካል ሆስት ባየርስ ይባላሉ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ቢል ጌትስ ለ2017 አንድ ቢሊዮን ዶላር መድቦ፣ በ500 ሚሊዮን ዶላሩ አፍሪካ ውስጥ ስብሰባ አዘጋጁ ቢል፣ የህዝብ ግንኙነት አባላቱ አፍሪካ ውስጥ ስብሰባ ማድረግ የሚቻለው የት ነው? በማለት ቦታ የሚፈልጉበት ሀገር ወይንም የሚመርጡት በማይስ ኤክስፖ ላይ ነው፡፡ ለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ ደቡብ አፍሪካን ያገኛሉ፤ ቀጥሎ ኬንያን፣ ከዚያም ሞሮኮን፡፡ በዚህ ኤክስፖ ላይ የሚካፈሉትን ሀገራት ያገኛሉ፤ ይደራደራሉ፡፡
በእንደዚህ ዓይነቱ ፎረምና ኤክስፖ ላይ ካልተገኘን ሁሉ ነገር ከእጃችን ያመልጣል። ከዚህ በተሻለ ደግሞ በቋሚነት የኤክስፖ አዘጋጁ ሀገር ከፍተኛውን ጥቅም በእጁ ያስገባል፡፡ ገዢዎቹ እኛ በደቡብ አፍሪካ ኤክስፖ የምንሳተፍ ከሆነ፣ የመወዳደር ዕድል ልናገኝ እንችላለን፡፡ ሁለቱን ብናይ መወሰን እንችላለን ብለው አዲስ አበባ አምጥተው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንዲወያዩ፣ እነዚህን ዓለም አቀፍ ሆስት ባየሮች ስናመጣ ወጪያቸውን በሙሉ እኛ እንችላለን፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚዘጋጀው ማይስ ኢስት አፍሪካ 2016፣ ከ50 እስከ 100 የሚደርሱ ባየሮችን እናመጣለን ብለን አቅደናል፡፡ ለምሳሉ ከ50ዎቹ ገዢዎች 5 እንኳ ስብሰባዎች በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ቢወስኑ፣ 2000 ተሰብሳቢዎች በቀን 600 ዶላር ሂሳብ  ለ5 ቀን የሚቆዩበትን ወጪ ያደርጋሉ፡፡
በዚህም በቀላል ስሌት ሀገሪቷ የአየር ትኬትን ሳይጨምር ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይፈጥርላታል፡፡ ለዚህ ነው የውጪ ምንዛሪን ችግር ፈቺ ቢዝነስ ማይስ መሆን ጀምሯል የሚባለው። ታሪካዊ ቦታዎችን በመጎብኘት የሚደሰቱት ቱሪስቶችና የቢዝነስ (ማይስ) ተሰብሳቢዎችን ብናነፃፅር፣ ቱሪስቶች በቀን 100 ዶላር ሲያጠፉ፣ የማይስ ተሰብሳቢዎች በቀን ከ500 - 600 ዶላር እንደሚያጠፉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ስለዚህ ማይስ ከ5 እጥፍ በላይ ገቢ የሚያስገኝ አዲሱ የቢዝነስ አቅጣጫ ነው፡፡
ለዚህ ንግድ ደግሞ መሰረታዊ የሚባሉ ቴክኒኮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የመሰብሰቢያ ቦታ (መሰረተ ልማት) ነው፡፡ መሰረተ ልማት የሚባሉት የመሰብሰቢያ ቦታ፣ ሆቴሎች እና የመሳሰሉት ናቸው። በኛ በኩል እነዚህ ችግሮች እየተቀረፉ ነው። ሌላው መንግሥት ራሱን የቻለ የኮንቬንሽን ቢሮ ማቋቋም አለበት፡፡
ይህን ቢሮ አሰራሩ በሚፈቅደው መሰረት ማቋቋም ተገቢ ነው፡፡ ቢሮው ለትርፍ ያልተቋቋመ ይሆናል፡፡ ዘርፉ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን በዚህ የሚቲንግ ኢንዱስትሪ የተጠቀሙ ሀገሮች ልምድ ያሳያል፡፡ የዚህ ቢሮ ወይንም ኤጀንሲ ዋና ተግባራት የሀገሪቱን ዋና ዋና ኤቨንቶች፣ የስብሰባ ኢንዱስትሪ መረጃዎችን ማስተዋወቅ፣ ጥናት ማድረግ፣ አቅጣጫ ማስያዝ ይሆናል፡፡ ይህ ሲሆን የተቀናጀ አሰራርን ይፈጥራል፡፡ በዚህም ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡
ሌላው ቴክኒክ ደግሞ ሀገሪቷ ይህንን የሚቲንግ ኢንዱስትሪ በቋሚነት የምታስተዋወቅበት ዓመታዊ ፎረምና ኤክስፖ ማዘጋጀት ነው፡፡ ኤክስፖ ማዘጋጀት የየእለት ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች ከጀርባው ስላሉ፣ በግሉ ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎች ናቸው፡፡ እኛም ይህንን መነሳሳት ወስደን በሀገሪቷ የመጀመሪያውን የማይስ ፎረምና ኤክስፖ በ2008 ዓ.ም በመጨረሻው ዓመት አጋማሽ ለመክፈት ዝግጅቱን አጠናቀናል፡፡
ለዚህም አስፈላጊ የሆኑ ፕሮሞሽንና ስምምነቶችን ተፈራርመናል። ይህ የማይስ ፎረምና ኤክስፖ በተለያዩ ወገኖች ድጋፍ የሚሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ቁምነገር፤ተከታታይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡   

Read 2569 times