Saturday, 18 July 2015 11:51

ፈረሰኛው ፍቅር!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

እሳሩ ቤት፣ምድጃ ዳር ተቀምጦ፣ ያለ ወትሮው ቢላ በሞረድ ሲስል ያዩት አያቱ ደስ አላላቸውም። “የመድኃኒዓለም ያለ! አንተ የምን ቢላ ነው የምትስለው!” ሲሉት ድንገት ቀና ብሎ አያቸውና መልሶ አቀረቀረ፡፡ እማማ ዝናብዋ ከቤተክርስቲያን መመለሳቸው ነው፡፡
“ስማ እንጂ ጉልላት…አትናገርም እንዴ?” አሉ ነገሩ ስላልገባቸው፡፡ ዐውደ አመት አይደለ፤ የታቦት ንግስ የለ!...እና ቢላ መሳልን ምን አመጣው በሰንበት!...
“አይ፤ ዝም ብዬ ነው፡፡” አለና ብድግ ብሎ ወደ ውጭ ወጣ፡፡ የሳር ቤትዋ በር እያስጎነበሰችው ነው፡፡ የዛሬ ሶስት ዓመት ከጂማ ሲመጣ እንዲህ አልነበረም። ሳያጎነብስ እንደ ልቡ ወጥቶ ይገባ ነበር።
አያቱ ከቤተክርስቲያን ሲመለሱ እሳቸውን ተከትለው አባ ሲርመታ፣ ጋሽ አሰፋና ሌሎችም አዛውንቶች ይመጣሉ፡፡ ይህ በየሳምንቱ የተለመደ፣ የየሳምንቱ የሕይወት ቀለበት ነው፡፡ ቀኑ እንደሆነ ዞሮ ይመጣል - ይሄዳል፡፡ ክቡ አያልቅም። የሰውን የሩጫ ዙር እያስጨረሰ፣ እያደከመ አሸንፎ ይቀጥላል፤ ሰው ነው አለክልኮ የሚያበቃው፡፡ ይኸው ጉልላት ከመጣ እንኳ በየሳምንቱ እሁድ በተስኪያን ይሄዳሉ፣ ይመለሳሉ፤ ከዚያ ቡና ይጠጣሉ፤ በየወሩ ደግሞ የመድሃኔዓለምን ጥዋ ይጠጣሉ፡፡ …ቀኑ ያው ነው….
“ሁኔታህ አላማረኝም!” አያቱ፡፡  ድምፃቸው ተከተለው፡፡ ውጭው ለስላሳ አረንጓዴ ምንጣፍ መስሏል፡፡ ሲያዩት ብቻ ሳይሆን ሲረግጡት ይመቻል፡፡ በስተቀኝ ትንሽ ራቅ ብሎ፣ ከጐጆዋቸው ጀርባ ያለችው ግራር ዛፍ መሬት ላይ ክንፎችዋን እንደ ጃንጥላ  ተክላለች፡፡
ጓሮው በደረሰ እሸት በቆሎ ግጥም ብሏል፡፡ ራቅ ሲል ከዚህች ተራራ ሥር ዙሪያውን ያሉት ሜዳማ ስፍራዎች ሁሉ፣ አረንጓዴ ቀለምና የዝርግ ውሃ ውበት ጠግበዋል፡፡ ሁሉም ነገር ያምራል፡፡ ማዶውን የነጭ ፈረስ ጭራ መስለው በሩቅ የሚታዩት ሁለት ፏፏቴዎች ልብን ይጣቀሳሉ፡፡
ሰፈራቸው የሚኖሩት ሰዎች በአብዛኛው ክርስቲያኖች ስለሆኑ ሠፈሩ ጭር ብሏል፡፡ ከነርሱ ጐጆ የሜዳውን ክብ ተሻግሮ ያሉት ወይዘሮ ተዋበች - ድንገት ከወደ መድሃኔአለም ብቅ ሲሉ ሰላም ላለማለት ቀኙን በነፉንጐ ቤት ጐን ታጠፈ፡፡
እሁድ ባይሆን ኖሮ ይሄኔ ወፍጮ ላይ አጐንብሳ እህል እያጐረሰችው፣ መጁን ስትነዳ የምታንጐራጉረው ዜማ ልቡን ያማስለው ነበር። ዛሬ ግን የለችም፤ አባትዋ መምሬ ካሳ ሰንበትን ቤተክርስቲያን እንድታሳልፍ ነግረዋታል፡፡
የእርሱ እያት ዝናብዋም እሁድ በተስኪያን ቢስምላቸው ደስ ይላቸዋል፡፡ የልጃቸው ልጅ ሳይጦር ሳይቀበራቸው ሃይማኖቱን እንዲቀይር አይፈልጉም፡፡ ለዚህም ሁሌ ቸሩ መድኃኒዓለምን እንደጐተጐቱ ነው፡፡ ቸሩ መድኃኒዓለም የላንፉሮ ታቦት ነው፡፡ ላንፉሮ ደግሞ የደጃች ባልቻ ርስትና መንደር ናት፡፡
የመድኃኒዓለም ደብር ዙሪያውን በከበባት ዝርግ መልክዐ-ምድር መሀል ላይ እንደ መሶበወርቅ ጉብ ባለው የላንፉሮ ሻኛ ላይ ተሰይሞ፣ ግራና ቀኙን ቁልቁል የሚያይ ነው የሚመስለው፡፡
ጉልላት ወዲያ ወዲህ ተንጐራደደና የሳለውን ቢላ ወስዶ አድባሩ ዛፍ ሥር ሸጐጠው፡፡
“ዛሬ ያለወትሮው ሊጨክን ነው፡፡
“ጉ-ሌ አንተ” ተጣሩ ዝናብዋ፡፡
“እሜት!” ሲል ተቆጡ፡፡ “እዚያ ደግሞ ምን ታደርጋለህ?...ና ውጣ! በሽታ ለይ እንዳትወድቅ እዚያ አትሂድ አላልኩህም?”
“ቤዛንኩሉ ዓለም - ቤዛንኩሉ ዓለም - ተወልደ…እህህህ…ኦሆ - ኦሆ ኦሆ”
ልቡ ደረቱን ሰንጥቃ፣ አየር ላይ የበረረች መሰለው፡፡ የሚጣፍጥ - ድምፅ የሚነካ ዜማ ፉንጐ ናት፡፡ ፉንጎ ከቤተክርስቲያን እንደመጣች የሰማችውን ዜማ አወረደችው፡፡
 መንፈሳዊ ቅኔ ምን እንደሆነም አያውቅ!...ከማረቆ ነው የመጣው፡፡ ከጂማ ከመጣ በኋላ ለአንድ ዓመት ማረቆ የመኪና ጭራ ሲከተል ቆይቶ ነበር፡፡ እዚያ የኖረው ከታላቅ እህቱ ጋር ነበር፤ ለሃይማኖት እምብዛም ነው፡፡ እንዲያውም ወደ ዘፈን ያደላል፡፡ ማምሻ-ማምሻ ጨረቃ የወጣች ሰሞን ከቤታቸው ፊት ለፊት ካለችው ዛፍ ሥር ቆሞ በፉጨት ሲዘፍን፣ ፉንጐ እቤት ውስጥ ሆና ስቅስቅ ብላ ታለቅሳለች፡፡ ዘፈኑ ይሁን ፍቅሩ ግን አልገባትም፡፡ እሱ በድምጽዋ፣ እሷ ደሞ በፉጨቱ ተጠላልፈዋል፡፡
እሷማ ጭፈራም ስትችልበት ለብቻ ነው፡፡ ላሌ-ሄቦላሌ ቦላሌ ስትል ከሠማይ ከዋክብት የሚረግፉ ይመስላል፡፡ ጨረቃም መቀነትዋን ፈትታ አብራት የምትጨፍር ይመስላል፡፡
እማማ ዝናብዋ ደሞ ሞያዋን ያደንቁላታል። “አቤት የምትሠራው ወጥ!…የዘመዶችዋን ይዛ…አባትዋ ከመንዝ ነው የመጡት፣ እናትዋ ያገራችን ሰው ናት…ትንሽ የማልወድላት እንደ ወንድ ፈረስ መጋለብዋ ነው፡፡” ይላሉ፡፡
ይሄኔ ፍቃዱ ይብስበታል፡፡ አንዳንዴ እርሱ ከብቶች ሊያሰማራ ወደ ዓባያ ሀይቅ ሲሄድ እርሷ ከቡሬ ውሃ ቀድታ ስትመጣ ይገናኛሉ፡፡ ንቁ ናት፡፡ ሰማያዊ ጀርሲ ቀሚስዋን በአዘቦት ቀን አትለብስም። የመድሃኔዓለም ንግስ ወይም የጥምቀት ቀን ነው የምትለብሰው፣ የክት ናት፡፡ አዘውትራ ቀይ ሻማ ውስጥ ልብስዋን ነው የምትለብሰው፡፡ ታዲያ ሁሌም ሲያገኛት ዘፈንዋን እንዳቀለጠችው ነው፡፡ መዝፈን፣ መጨፈር ትወዳለች፡፡ ሠርግ ቤት፣ ጥምቀት በዓል ላይ፣ ሰው ሁሉ ቆሞ ያያታል፡፡
“ፉንጐዬ”  ይላታል፡፡
“አቤት ጉሌ!”
አይንዋን ያያታል፣ ጐንበስ ትላለች፡፡
“ሰው እንዳይመጣ!”
“ይምጣአ!”
“እማማ ዝናብዋ ቢመጡስ?”
“ምንም አይሉኝም፡፡”
“ውሸታም!”
“እኔ ልሙት!” የእጅዋን መዳፍ በእጁ መዳፍ ይመታና፣ በሰበቡ መሀል መዳፍዋን ይስማታል፡፡
“ኧረ ተው” ትለዋለች፡፡ ፈገግታዋ ግን ከልብ እንዳልሆነ ያስታውቃል፡፡ …የእጅዋ መዳፍ ግን በስራ የደደረ ነው፡፡ ቢሆንም የልብዋ ልስላሴ ያንን ያስረሳዋል፡፡
ፉንጎ ፀጉርዋን በስልጤ ብሔረሰብ ባህል መሠረት ሲጃ ተሠርታ፣ ከፊት - ለፊት እንደ እርከን የቆመ ፀጉርዋ ላይ የተለያዩ ቀለማት ያሉዋቸው አዝራሮች ደርድራለች፡፡
“አንቺን ነው የማገባው!” ሲላት ደስታዋ ደመና ጠራርጐ እንደሚሸኝ ንፋስ የፊትዋን ገጽ ይገፋዋል፡፡ ጠይም ፊቷ ፀሐይ ብልጭ ይልበታል፡፡
ዛሬ ገና ሲለያዩ “አሁን ሁሉም ነገር  በቃ! አንቺን ተነጥቄማ አልኖርም!” አለ ለራሱ፡፡ ከዚህች ቀየ፣ ከዚህች ሠፈር መለያዬ ደረሰ፡፡ ዓባያ ሀይቅ ዳር ሄጄ ከብት ማሠማራቴ ፣ ከጓደኞቼ ጋር የነበረኝ ጨዋታ፣ የምወደው ወይፈን የመጋልም ግሳት፣ ሊያበቃ ነው…” ብሎ አይኖቹ እንባ አቀረሩ፡፡
ከዚህች ከሚኖርባት ላንፉሮ ተራራ ግርጌ ዓባያ ሀይቅ አለ፡፡ ያ ሀይቅ ደግሞ የእርሱና የጓደኞቹ የፌሽታ ቦታ ነው፡፡ ከብቶች እያገዱ፣ አንዳንዴም ፈረስና አህያ እየጋለቡ ይጫወታሉ፡፡ ከየቤታቸው ያመጡትን ቂጣና እንጀራ፣ በቡድን እየተሻሙ ይበላሉ፡፡ አንዳንዴም ከሀይቁ ዳር አልፎ አልፎ ካሉት ግራሮች ሥር ተቀምጠው ገበጣ ይጫወታሉ፡፡
እዚህ ደግሞ ጋራው ላይ ከፉንጐ ጋር ዓይን-ላይን፣ ልብ-ለልብ ይሠራረቃሉ፣ ዘፈንዋን ያዳምጣል። ጨለምለም ካለ ደግሞ አንገትዋ ሥር ይስማታል፡፡ አያቱን ቡና ልትጠራ ስትመጣ፣ ሰው ከሌለ እቅፍ ያደርጋታል፡፡ በእርሷ ምክንያት ሕይወት ደስ ይለዋል፡፡ ኑሮ ይጣፍጠዋል፡፡ አሁን ግን በቃ፣ ሞት ፊት ለፊቱ ቆሟል፡፡
“ጉ - ሌ.” ጠሩት አያቱ፡፡ ከተቀመጠበት ሜዳ መጣና ጎንበስ ብሎ ገባ፡፡ አባ ሲርመታ፣ ጋሽ አሰፋና ሌሎችም የጎረቤት ሰዎች አሉ፡፡
“በል ሰላም በል!” አሉት አያቱ፡፡
ሁሉንም በየተራ ሰላም አላቸው፡፡
“አንተ በተስኪያን አትሥምም!...” አሉት አባ ሲርመታ ቆጣ ብለው፡፡ አባ ሲርመታ ብዙ ጥርሶቻቸው ስለወለቁ ጉንጫቸው እየጎደጎደ፣ሲናገሩ አፋቸው ይኮላተፋል፡፡
አጎንብሶ ዝም አለ፡፡ ጋቢያቸውን ትከሻቸው ላይ አስተካከሉና፤ “ይህ‘ኮ የባልቻ አባነፍሶ ሀገር ነው፡፡ … አለማወቅህ እንጂ! … ጀግና የከተመበት የክርስቲያን ሀገር ነበር! ..” አሉና እንደመቆጨት አሉ፡፡
“ተወው እባክህ… ልቡን ሲገዛ ወደ ፈጣሪ ራሱ ይመጣል፡፡” አሉ ጋሽ አሰፋ፡፡ ጋሽ አሰፋ ቦላሌ አይታጠቁም፡፡ ጉልበቱ ላይ የተቆረጠ ቦላሌ  የመሰለ ነገር እስከ ባታቸው ነው የሚለብሱት፡፡
“በል ተቀመጥ!” አሉት፤ ተቀመጠ፡፡
“ዛሬ አንተ ልጅ ሁኔታህ ጥሩ አይደለም!” አሉ አያቱ፡፡
“ምንም አልሆንኩ!” ብሎ አጉተመተመ፡፡
“ከጎረመሥክ ሚስት እድርሃለሁ፡፡” ሲሉት እንደማፈር አለና አቀረቀረ፡፡
የቡና ቁርስ ተሰጥቶት ቡናውን ከጠጣ በኋላ ሀሳቡን ለመፈጸም ተነሳ፡፡ መጀመሪያ ከዓባይ ሀይቅ ከፍ ብሎ ወዳለው ኩሬ ሄደ፣ እዚያ ሲደርስ ፉንጎ ውሃዋን ቀድታ ማሰሮዋን እግርዋ ሥር አስደግፋ ተቀምጣለች፡፡ እንደደረሰ እጅዋን አንጠልጥሎ ወደ ዓባያ ወሰዳት፡፡
ትንፋሽ እስኪያጥራት እያጣደፈ አደረሳት፡፡
ዓባያ ደርሶ ግራና ቀኝ ሲያይ እረኞች ራቅ ብለው ግራር ዛፍ ስር ተኝተዋል፡፡ ጠረኑን የለመደው መጋል “እምቧዋ” አለ - ሲያየው፡፡ መልስ አልሰጠውም፤ ሆዱ ግን ባባ፡፡ አንገቱን ሲያሻሸው ዝቅ ብሎ ስሩ መግባት ለምዷል፡፡
 ኮቱን አውልቆ “ያዢልኝ” አላት ፉንጎን፡፡ ከዚያ ፈረሱ ላይ አስቀመጣት፡፡
“ጉሌ፤ - ካገኙን ይገድሉናል፡፡”
“እነማን?”
“እኔን ለማግባት የጠየቀኝ ልጅ ቤተሰቦች!”
“እኔ በሶ ጨብጫለሁ!”
“አሁን ወዴት ነው የምትወስደኝ?”
“ወደ ማረቆ”
“ማረቆ ወዴት ነው?”
“ተከተይኝ!”
ፊትዋን ነጠላ አከናነባት፡፡ እርሱም ጭንቅላቱ ላይ ጨርቅ ጠመጠመ፡፡ ዓባያን ዳርዳር ይዘው በገርቢ በር ገበያ በኩል ሜዳውን ይዘው በየፈረሶቻቸው ይጋልቡ ጀመር፡፡ “ጥሩ ሰንጋ ፈረሶች ናቸው፡፡” አላት፡፡ እሷ ግን ከቀልቧ አልነበረችም፡፡ መምሬ ካሣ ምን ይሉ ይሆን? እያለች ልቧ ይመታል። ጉሌን ግን ትወደዋለች፡፡
“ጉልዬ … መሸ!”
ከኪሱ እሸት በቆሎና ስልቅጥ የተጋገረ ቂጣ ሰጣትና በላች፡፡
“አይዞሽ!... እንደርሳለን…”
“ጅብ የለም?!” ጠየቀችው፡፡
“ይኑራ!”
ጅቡን የጠራችው ይመስል ወዲያው ድምፅ ተሰማ፡፡ ገና ባዶ ምድረበዳ ላይ ናቸው፤ የሰዎች መኖሪያ ሰፈር አልደረሱም፡፡ ደነገጠች፡፡
“የሚጮኸው ከሩቅ ነው!” አላት እንዳትፈራ፡፡
ሌላ ቅልጥ ያለ ጩኸት ድንገት ከፊታቸው ተሰማ፡፡
 “ም-ን-ድ-ነ-ው?” አለች፡፡
“ምንም የለም አትፍሪ… እሺ!”
ብዙ ፈረስ የያዙ ሰዎች ማረቆ መግቢያ አካባቢ ይተራመሳሉ፡፡
“ቁም! … ቁም!..ማ-ነ-ህ? ማነህ?” አሉ፡፡
“እንዲህ ጉድ ታደርጊኝ ልጄ!...እንዲህ ጉድ ትሰሪኝ!” መምሬ ካሳ ናቸው፡፡ ፉንጎ ሰማይ ምድሩ ዞረባት፡፡
ጉልላት ግን መሰናክል ሆኖ ፊቱ የተጋረጠበትን በድፍረት ተጋፍጦ ሽምጥ ጋለበ ወደ - ማረቆ፡፡
ጩኸቱ ቀለጠ፡፡
“ገደለው --- ገደለው!”
 “ያ-ሳ-ዝ-ና-ል! ቢላዋ ሰክቶበት ሄደ፡፡” ወደ ኋላ ቀረት ብላ የነበረችው ፉንጉ፤ በደመነብስ ያባትዋን ፈረስ ለቀም አድርጋ ጉልላትን ተከተለችው፡፡
“ጉ-ሌ!... ጉሌ!” ዘወር ብሎ አያት፡፡
ሁለቱ ፈረሶች ጩኸቱን ከኋላቸው አስቀርተው ወደፊት ሸመጠጡ፡፡
“በርቺ!” አላት፡፡ ሜዳውን ሽምጥ ጋለቡ፡፡ ጨረቃ ገና አልሳቀችም፤ክዋክብት ፊታቸውን በብርሃን አልታጠቡም፡፡ ሰቀቀንና ፍርሃት ልቦቻቸው ላይ እስክስታ እየመቱ ነው፡፡ ከበሮ መደለቃቸውን ቀጥለዋል፡፡
ድ-ን-ገ-ት “ጉ---ድ----ጓ----ድ!” አለ ጉልላት፡፡
ፉንጎ ዘወር ብላ ስታይ ጉሌ የለም፡፡ ፈረስዋን አዞረችው፡፡ ጉድጓዱ ውስጥ ድምጽ ሰማች፡፡ “ተ---በ---ላ---ሁ!” የሚል፡፡ ከፈረስዋ ወረደች፡፡…ፈረሱን ትታ ወደ ጉድጓዱ ዘለለች፡፡
የሲቃ ድምጽ….ተስተጋባ፡፡….  

Read 2055 times