Saturday, 18 July 2015 11:43

የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኮሎምቢያ እየተካሄደ ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ለቤጂንግ 44 አትሌቶች ያሉበት የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ቡድን ታውቋል
                               
           9ኛው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኮሎምቢያዋ ከተማ ካሊ ባለፈው ሐሙስ ሲጀመር ኢትዮጵያ የመጀመርያ የወርቅ ሜዳልያዋን በ3ሺ ሜትር በማስመዝገብ ጥሩ አጀማመር አሳይታለች። የወርቅ ሜዳልያውን ያገኘችው አትሌት ሹሩ ቡሎ ስትሆን በ3ሺ ሜትር ሴቶች ያሸነፈችው የሻምፒዮናውን ፈጣን ሰዓት በ9 ደቂቃዎች  ከ01.12 ሰከንዶች አስመዝግባ ነው፡፡ በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ 10 ሴትና 10 ወንዶች ባካተተ ቡድኗ የምትሳተፍ  ሲሆን ሻምፒዮናው ነገ ሲጠናቀቅ ቢያንስ  9 ሜዳልያዎች ሶስት ወርቅ፤ 3 የብርና 3 የነሐስ እንደምትሰበስብ ግምት አለ፡፡ በዓለም የታዳጊዎች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በሁለቱም ፆታዎች የወከሉት 20 አትሌቶች አሰላ ላይ ለሶስተኛ ጊዜ በተደረገው የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመሳተፍ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸውን ያስታወቀው ፌደሬሽኑ የወደፊት የአገሪቱን ኮከብ አትሌቶች ለማግኘት ዓለም አቀፍ ውድድሩ ወሳኝ እንደሆነ አምኖበታል። በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የሚዘጋጀው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ በ16 እና 17 ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በ40 የውድድር መደቦች ይሳተፉበታል።  ከ800 እስከ ሁለት ሺህ ሜትር  የሩጫና እርምጃ  ውድድሮች የሻምፒዮናው አካል ናቸው፡፡ ከ2 ዓመታት በፊት በዩክሬኗ ከተማ ዶኔትስክ ላይ ተደርጎ በነበረው 8ኛው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ቡድን  ሶስት የወርቅ፣ ሶስት የብር እና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ በመሰብሰብ ከዓለም ሶስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ከወር በኋላ በቻይናዋ ከተማ ቤጂንግ ለሚደረገው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ለሚወክለው ቡድን የተመለመሉ አትሌቶች  ጊዜያዊ ስም ዝርዝርን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኮሙኒኬሽን ክፍል አስታወቀ።  በነሐሴ ወር አጋማሽ  በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያ በ800 እና 1500 ሜትር መካከለኛ ርቀት፤ በ3ሺ ሜትር መሰናክል፤ በረጅም ርቀት 5ሺ እና 10ሺ ሜትር እንዲሁም በማራቶን ውድድሮች በምትሳተፍበት ቡድን 44 አትሌቶች በጊዜያዊ ስም ዝርዝሩ ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኮሙኒኬሽን ክፍል ሐምሌ 9/2007 ዓ. ም. ይፋ ያደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን ጊዜያዊ ቡድን የአትሌቶች  ስም ዝርዝር ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡
በ800 ሜትር በወንዶች መሃመድ አማንና ጀና ኡመር እንዲሁም በሴቶች ሃብታም አለሙ፣ ባይህ ጫልቱ ሹሜ ረጋሳና ኮሬ ቶላ ነገሆ
በ1500  ሜትር በሴቶች ዳዊት ስዩም ፣ ሰንበሬ ተፈሪ ፣አክሱማዊት እምባዬና ጉዳፍ ፀጋዬ እንዲሁም በወንዶች ሱር አማን ወጤ እና መኮንን ገ/መድህን
በ5 ሺ ሜትር ዘጠኝ እንዲሁም በ10ሺ ሜትር ስምንት አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በጊዜያዊ ዝርዝሩ ተካትተዋል፡፡ በ5ሺ ሜትር ወንዶች ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ ሐጐስ ገ/ህይወት ደጀን ገ/መስቀልና የኔው አላምረው ሲሆኑ በሴቶች ደግሞ  አልማዝ አያና፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ አለሚቱ ሃዊ  አዝመራ ገብሩ
በ10 ሺ ሜትር ወንዶች ሙክታር አድሪስ፣ ኢማነ መርጊያ፣ ሞስነት ገረመውና  አዱኛ ታከለ፤ በሴቶች ደግሞ ገለቴ ቡርቃ፣ አለሚቱ ሃሮዬ ፣በላይነሽ ኦልጅራ እና  ማሚቱ ዳስካ
በ3000 ሜትር መሠናክል በሁለቱም ፆታዎች ስምንት አትሌቶች ሲያዙ በሴቶች ሕይወት አያሌው፣ ሶፊያ አሰፋ፣ ብርቱካን ፋንቴና ትዕግስት ጌትነት  እንዲሁም በወንዶች ጂክሳ ቶሎሳ፣ ኃ/ማርያም አማረ፣   ታፈሰ ሰቦቃና  ጫላ በዩ
በማራቶን በሴቶች   ትርፌ ፀጋዬ፣ ማሬ ዲባባ፣ ትዕግስት ቱፋ፣ ብርሃኔ ዲባባ  ተይዘው፤ በወንዶች ደግሞ ሌሊሳ ዲሳሳ ፣ የማነ ፀጋዬ፣ ለሚ ብርሃኑ እና እንደሻዉ ካሳ

Read 3409 times