Saturday, 18 July 2015 11:40

በአሜሪካ ያለው መሃመድ አማን በቤጂንግ ክብሩን ሊያስጠብቅ ይፈልጋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ዘንድሮ በአሜሪካዋ ከተማ ዩጂን የሚገኝ ክለብን በመቀላቀል ተቀማጭነቱን በዚያው ያደረገው አትሌት መሃመድ አማን በቤጂንግ የዓለም ሻምፒዮና ክብሩን የማስጠበቅ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ፡፡
መሃመድ አማን ሰሞኑን ስፓይክስ በተባለ የአትሌቲክስ ድረገፅ ላይ የአማን ዓለም በሚል በወጣ ዘገባ  በረጅም ርቀት ታላላቅ አትሌቶች ትታወቅ የነበረችው ኢትዮጵያን በ800 ሜትርም ምርጥ አትሌቶች ለማፍራት አቅም እንዳላት ያሳየ አትሌት ተብሎ ተደንቋል፡፡
በስፓይክ መፅሄት ዘገባ ላይ መሃመድ በሰጠው አስተያየት ‹‹አሰልጣኜ፤ አባቴም ሳይቀር በ5ሺ እና በ10ሺ መሮጥ እየቻልክ ለምን በ800 እየሮጥክ ግዜህን ታባክናለህ ይሉኝ ነበር›› ብሎ  ‹‹ ሁሌም ግን በመካከለኛ ርቀት እንደሚሳካልኝ በማመን ባደረግኩት ጥረት  እንደሚሳካልኝ አልጠራጠርም ነበር›› ሲል ተናግሯል፡፡ የ21 ዓመቱ አትሌት መሃመድ አማን፤ ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ካደረገ በኋላ ስልጠናው እና ኑሮውን እየለመደ መምጣቱን የገለፀው ስፓይክ መፅሄት አሜሪካ መኖር ከጀመረ በኋላ በአሜሪካ ፉትቦል እና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች መማመረክ መጀመሩንም አትቷል፡፡በአይኤኤኤፍ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች በሁለት የውድድር ዘመናት አሸናፊ በመሆን  ከፍተኛ ትኩረት ከሚያገኙ አትሌቶች አንዱ የሆነው መሃመድ አማን ዘንድሮ በርቀቱ ለሱስተኛ ጊዜ ለማሸነፍ ሰፊ እድል እንዳለው ይገለፃል፡፡ በዩጂን እና በሮም የተደረጉ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን በማሸነፍም ግምቱን ለማሳካት በጉዞ ላይ ነው፡፡
አትሌት መሃመድ ፤ በ800 ሜትር ሶስት የዓለም ሻምፒዮንነት ክብሮች ሲኖሩት ሁለቱ በዓለም የአትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድር የተመዘገቡ እንዲሁም ዋንኛው ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ800 ሜትር የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃበት ናቸው፡፡ በ800 ሜትር የኢትዮጵያ ሪከርድን የጨበጠው መሃመድ አማን በርቀቱ 9ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጠውን የምንግዜም ፈጣን ሰዓትም አስመዝግቧል፡፡ በ800 ሜትር ፈጣን ሰዓቱ 1 ደቂቃ ከ42.37 ሰከንዶች ነው፡፡
እንደ ስፓይክ መፅሄት ሀተታ መሃመድ አማን አሁን ትኩረቱ በቤጂንግ በሚደረገው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ800 ሜትር  የሻምፒዮንነት ክብሩን በማስጠበቅ በውድድሩ ታሪክ ሶስተኛው ሰው የመሆን ፍላጎቱን ማሳካት ነው፡፡ በዓለም ሻምፒዮና ታሪክ በ800 ሜትር አከታትለው የወርቅ ሜዳልያ የወሰዱት ሁለት አትሌቶች  ብቻ ሲሆኑ ቢሊ ኮንቼላህ እና ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕኬተር ናቸው፡፡

Read 1836 times