Saturday, 18 July 2015 11:31

በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚጋብዙ 10 ምርጥ ምክንያቶች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የኧርነስት ኤንድ ያንግ የኢትዮጵያ ማኔጂንግ ፓርትነርና ትራንሲሽን አድቫይሰሪ ሰርቪስ (TAS) ኃላፊ ናቸው፡፡ በ3ኛው ፋይናንስ ለልማት ዓለም አቀፍ ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ ገበያ እየፈጠረ ያለውን አስገራሚ ዕድገትና የኢንቨስትመንት አማራጮች አስመልክተው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚጋብዙ 10 ምርጥ ምክንያቶች በሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እኛም Investing in Emerging Ethiopia በሚል ርዕስ በጁላይ 2015 በታተመ መጽሔት የቀረቡትን 10 ምርጥ ምክንያቶች በዚህ መልኩ አቅርበናል፡-
1.የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፡- ኢትዮጵያ ከሰሐራ በታች ካሉ አገሮች ከደቡብ አፍሪካ፣ ከናይጀሪያና ከአንጐላ ቀጥላ አራተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካላቸው የዓለም አገራት አንዷ ስትሆን እ.ኤአ በ2017 ከአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ 3ኛ ለመሆን እየሠራች ነው፡፡ በ2013 የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከ250 በመቶ በላይ የጨመረ ሲሆን አንድ ቢሊዮን ያህሉ ካደጉትና በማደግ ላይ ካሉ አገራት የመጣ ነው፡፡
ከፍተኞቹ ኢንቨስተሮች ቻይና፣ ሕንድ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ፣ እንግሊዝና ኔዘርላንድስ ናቸው። በኤርነስት ኤንድ ያንግ ትንበያ መሠረት፤ የኢትዮጵያውያን የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ2014 እስከ 2025 በየዓመቱ 18 በመቶ እያደገ መካከለኛ ገቢ ትደርሳለች ከተባለበት ጊዜ አንድ ዓመት ቀድማ በ2024 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ትሰለፋለች፡፡ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚጠቁሙ ሌሎች ነጥቦችም በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
2. የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፡- የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ከፍተኛ ሲሆን ወጣቶችና መሰልጠን የሚችል ሕዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አማካይ ዕድሜ ከ20 ዓመት በታች ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ የመሥራት አቅም ያላቸው የሰው ኃይል ማለት ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2070 የናይጀሪያ ሕዝብ ቁጥር 639 ሚሊዮን ቢደርስም ኢትዮጵያ 225 ሚሊዮን ሕዝብ በመያዝ ከአፍሪካ ሁለተኛ እንደምትሆን ዋሽንግተን ፖስት ጁላይ 2013 ባወጣው ሪፖርት ተንብየዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን አማካይ በሕይወት የመኖር ዕድሜ (Life expectancy) ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ትልቅ ነው፡፡ በ2012 የኢትዮጵያውያን በሕይወት የመኖር ዕድሜ 63 ዓመት ሲሆን፤ የኬንያ 61፣ የታንዛንያ 61፣ የደቡብ አፍሪካ 56፣ የናይጀሪያ 52፣ የአንጐላ 52 ዓመት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ያላት አየር መንገድ ከአፍሪካ አገሮች ትልቁና እጅግ አትራፊ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የሚመራ ነው፡፡ የአፍሪካ አየር መንገዶች ትርፍ አንድ ላይ ቢደመር እንኳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፍ በጣም ይበልጣቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ብዙ አውሮፕላኖች አሉት፡፡  ከአፍሪካ አየር መንገዶች ለ6 ተከታታይ ዓመት እጅግ ፈጣን ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሪምላይነር 787 አውሮፕላን በማብረር ቀዳሚ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፍ በ2013 ዓ.ም 143 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን የደቡብ አፍሪካ 42 ሚሊዮን ዶላር፣ የኬንያ ኤርዌይስ 92 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡
3. ፈጣን የከተሞች ዕድገት፡- ከተሞች የዓለም የዕድገት ኃይል ምንጭ ናቸው፡፡ በ2030 ከዓለም 50 ምርጥ ከተሞች ውስጥ ግማሾቹ ፈጣን ዕድገት ካላቸው አገሮች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ በ2025 ዓ.ም 6.1 ሚሊዮን ሕዝብ በመያዝ፣ ብዙ ሕዝብ ከሚኖራቸው ከተሞች 5ኛ እንደምትሆን ተተንብዮአል፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ትራንስፖርት ከሰሐራ በታች ካሉ አገሮች የመጀመሪያው ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢኮኖሚ ዕቅዱ ውስጥ ለከተማ ማዕከላት ዕድገት ቅድሚያ ሰጥቷል፡፡ ትላልቅ የከተማ ሰፈሮች መፈጠር ኢንቨስትመንት ከመሳቡም በላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ይጨምራል፡፡ ከ300ሺህ ሕዝብ በላይ  የሚኖርባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች በ2030 በጣም ብዙ እንደሚሆኑ ተገምቷል፡፡
4. የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል፡- አሁን ባለው ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ በ2025 ከአህጉሩ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከሎች ከደቡብ አፍሪካ፣ ከናይጀሪያና ከኬንያ ቀጥላ እንደምትሆን የኧርነስት ኤንድ ያንግ ጥናትና ትንታኔ እንዲሁም ከተለያዩ የውጭ ምንጮች የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እሴት በሚጨመርባቸው ጉልበት በሚፈልጉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች፣ በሸቀጣሸቀጦች፣ በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳ፣ በኮንስትራክሽን ማቴሪያልስ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ እሴት በሚጨመርባቸው ጥሬ ዕቃዎች… የአህጉሩ ምርጥ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለመሆን እየሠራች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለተወዳዳሪነት ከፍተኛ ዋጋ ባለው የማኑፋክቸሪንግ የጉልበት ዋጋ ከዓለም ዝቅተኛው ክፍያ የሚፈፀምባት አገር ናት፡፡ የአሜሪካ ዓለምአቀፍ የሠራተኞች ስታቲስቲክስ በ2013 ባወጣው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ ለአንድ የማኑፋክቸሪንግ ሠራተኛ በሰዓት የሚከፈለው 0.41 የአሜሪካ ሳንቲም ነው፡፡ ማኑፋክቸሮች ተወዳዳሪ የሚሆኑበት አንዱ መንገድ የኤሌክትሪክ ዋጋ ዝቅተኛነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በዓለም የኤሌክትሪክ ዋጋ ክፍያ ርካሽ የሆነባት አገር ኢትዮጵያ ነች፡፡
5. መሠረት ልማት፡- በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ እየተጧጧፈ ነው፡፡ ኧርነስት ኤንድ ያንግ ከ2010 እስከ 2025 በመንገድ፣ በባቡር፣ በቴልኮም፣ በኃይል፣ በውሃ፣  የአውሮፕላን ግዢን ጨምሮ ከ101 ቢሊዮን በላይ በመሠረተ ልማት ዘርፍ ወጪ እንደሚደረግ ገምቷል፡፡ የኢንዱስትሪ ዞኖች ግንባታ ማኑፋክቸሪንግን ለማሳደግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በሰሜን አዲስ አበባ 5 የኢንዱስትሪ ዞኖች ለናሙና የሚገነቡ ሲሆን በመላው አገሪቱ ደግሞ 15 ዞኖች ይሠራሉ፡፡ በዚህ ዓመት በአዲስ አበባ ለሚገነባው ሁለተኛው የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ የዓለም ባንክ 250 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቅዷል፡፡
ኢትዮጵያ በ2023 ሁለተኛዋ ትልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርተር በመሆን ከቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደምታገኝ እንዲሁም በአፍሪካ ከናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ቀጥላ 3ኛዋ ትልቅ የቴሌኮም ገበያ እንደምትሆንና 5ሺህ ኪ.ሜትር የኤሌክትሪክ ባቡር አዲስ እንደምትገነባ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ትልቁ የዕቃ መጫኛ ካርጎ እንዳለው ተገልጿል፡፡
6. ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብት፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የዘይት፣ ጋዝና የማዕድን ቁፋሮ ተጀምሯል፡፡ የቻይናው ኩባንያ፣ ከካሉብና ከሂላላ የጋዝ ጉድጓዶች ጋዝ ወደ ኤስያ አገሮች ለመላክ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ ወደብ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ እየዘረጋ ነው፡፡ የሩሲያ፣ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ… የማዕድን አሰሳና ፍለጋ ለማካሄድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ፕላቲኒየም ታንታለም፣ ብረትና የፖታሽ ማዕድን አላት፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብቸኛዋ ኦፓል አምራች አገር ናት፡፡
7. እርሻ፡- ኢትዮጵያ ትልቅና ያልተነካ እምቅ የእርሻ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ ኢትዮጵያ 74 ሚሊዮን ሄክታር ያልታረሰና 15 ሚሊዮን ሄክታር የታረሰ የእርሻ መሬት አላት፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትልቋ የስንዴ አምራች ስትሆን በዓለም ትልቋ የጤፍ አምራች ናት፡፡ ጤፍ በካልሲየም ብረትና ፕሮቲን የበለፀገ ሲሆን አለርጂ ከሚያስከትለው ጉለቲን ማልያ ነፃ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ለመካከለኛ ምስራቅ ለአውሮፓ፣ ለኤስያና ከዚያ ወዲያ ላሉ አገሮች ኤክስፖርት ለማድረግ አመቺ ናት፡፡ ኢትዮጵያ በቡና ምርት ኤክስፖርት ከብራዚል፣ ቪየትናም፣ ኢንዶኔዥያና ኮሎምቢያ ቀጥላ 5ኛ ናት፡፡ ስታር ባክስ የኢትዮጵያን ቡና ገምግሞ ከ5 ነጥብ 4.8 ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ የወይን አምራችና ላኪ አገርም ሆናለች፡፡
8. ቱሪዝም፡- ስለኢትዮጵያ የቱሪስት መስህቦች ሲኤንኤን ስለሰሜን ተራራ “ከመሞትህ በፊት ማየት ያለብህ ስፍራ” (Place to see before you die) በማለት ገልጿል፡፡ ሁፍንግ ፖስት የተባለው ደግሞ ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሲገልጽ፤ “መታየት ያለባት ከተማ” (City to Visit) ብሏታል። “Over looked and under - visited, Ethiopia is Africa’s best kept secret” - 1000 place to see before you die ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በርካታ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የቱሪስት መስህቦች ያላት አገር ናት፡፡ ኒውዮርክ ታይምስ በ2014 ባወጣው ሪፖርት፤ በዓለም ከተጎበኙ አገሮች ኢትዮጵያን ከምርጥ 52 የዓለም የቱሪስት መዳረሻዎች በ13ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡
9. በቢዝነስ አመቺነት፡- የዓለም ባንክ በ2014 ባወጠው ሪፖርት መሰረት፤ ኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካ አገሮች በቢዝነስ ምቹነት ከደቡብ አፍሪካና ከጋና ቀጥላ 3ኛ ናት፡፡
10. የስትራቴጂ አቀማመጥና ነፃ ገበያ፡- ኢትዮጵያ ለ3.5 ቢሊዮን ሰዎች ቅርብ የገበያ መዳረሻ ስትሆን በ8 ሰዓት ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ከጂዳ 2፡45፣ ከዱባይ 3፡35፣ ከአቡጃ 4፡40፣ ከጆሃንስበርግ 5፡30፣ ከኢስታንቡል 5፡25፣ ከዴልሂ 6፡40፣ ከፍራንክፈርት 7፡20 ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡   

Read 3230 times