Saturday, 11 July 2015 12:42

ለረከሰ ፍርድ ሚዛን ሲሰፈርለት

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

      ጽልመት በለበሰ እልፍ አዕላፍ የሰው ዘር ላይ እንደ መርግ ለመጫን የሚንደረደር ብይን መስጫ መዶሻ ከመጽሓፉ ልባስ ላይ ታትሟል፡፡ የልባሱ ገጽታን ተመልከተን የሚፈጠርብን ብዥታ የለም። አንዴ ገርመም አድርገን የፍሬ ነገሩ መቋጫን ለመተንበይ ብዙ መራቀቅ አይጠበቅንብም፡፡
መንደርደሪዬ የአለማየሁ ገበየሁ የረከሰ ፍርድ በኢትዮጵያ መጽሐፍን ይመለከታል፡፡ መጽሐፉ በ189 ገጾች  የተቀነበበ ሲሆን በውስጡ ካቀፋቸው አስራ አራት አጫጭር ታሪኮች ፣ መጣጥፎች እና ዘገባዎች የፊትአውራሪነትን ካባ የለበሰው አንሳርማ የተባለው የፋንታሲ አጻጻፍ ስልትን የተከተለ ምናባዊ  ፈጠራ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የአጻጻፍ ዘይቤ የጆርጅ ኦርዌልን Animal farmን ያስታውስናል፡፡
አንሳርማ ገና ከጅምሩ ጠንከር ባለ መፈክር ነው የሚቀበለን፡፡
‘ከአሳማዎች አስተዋይ አመራር ጋር ወደ ፊት’
ከእልፍኙ እንደዘለቅን በገጽ 24 ላይ ራዞር የተባለው አሳማ አስገራሚ ዲስኩሩን ይጋብዘናል፡-
“ጓዶች! እንደምታውቁት ሕገ መንግሥታችን የተዋቀረው ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው በተባለው ፍልስፍና ላይ ነው፡፡ ይህ መርህ መቼም ቢሆነ አይሸራረፍም፡፡ ኾኖም ይህን ድፍን ሐሳብ እንደ አትላስ ተሸክሞ ሥራ ማከናወን አይቻልም። ለዚህም ነው ለረጅም ጊዜ ስንሠራ የቆየነው፡፡ የከተማችን ስያሜ፣ባንዲራችንና ብሔራዊ መዝሙራችን እስካሁን የሠራናቸው የማስፈጸሚያ ስልቶቻችን አካላት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በዋናነት ደግሞ የአፈጻጸሙ መመሪያ “ሁሉም እንሰሳት በመርህ ደረጃ እኩል ናቸው፤ነገር ግን አንዳንድ እንስሳት ከሌሎች ከእኩል በላይ ሊሆኑ ይችላሉ” ተብሎ መደንገጉን ሳበስር በደስታ ነው፡፡”
አንሳርማ እና የጆርጅ ኦርዌል “አኒማል ፋርም” የሚያስተላለፉት ጭብጥ፣ የሚንደረደሩበት መላምት እና የሚደርስቡት ድምዳሜ ኩታገጠም ነው፡፡ አንሳርማም ሆነ አኒማል ፋርም ዙሪያ ጥምጥም አይሄዱም፡፡ በአሳማ ዝርያ የተመሰለን አጓጉል ሰብዕናን በጥበብ ሾተል እየዋጋጉ የተደራሲያንን ንቃት ከከፍታ ላይ ለመስቀል ተፍ ተፍ ይላሉ፡፡ ከአሳማ ዘር ጋር በአንድ ማሕጠን የተኙት ራስ ወዳድ እንደራሴዎች በእዚህ ዓይነቱ የጥበብ አውድ ላይ ሲበለቱ ማየት ለአንባቢው የሚፈጥረው ስሜት የላቀ ነው፡፡
ደራሲው በአንሳርማ ምህዋር ላይ እንድንሽከረከር ምናባዊ መንኮራኮር ፈብርኮልን ነበር፡፡ ግና አመስግነነው ከአፋችን ሳንጨረስ ምናባዊው ጉዞው እክል ገጥሞት ቁልቁል ያምዘገዝገናል። የተከናነብነው የጥበብ ጃኖ ከላያችን ላይ ተገፎ በቅጽበት በቆፈን እንኮማተራለን፡፡
ተዓምረኛው የቅንጅት ምልክት  በሚለው ታሪክ ሥር አቧራ የጠገቡ ችኮ ዘገባዎች የአንሳርማን ሙቀት ተሻምተው ከፊት ለፊታችን ገጭ ይላሉ፡፡ ፀሐፊው የታሪኩ አሰላለፍ ብዙም ግድ የሰጠው አይመስልም። በአንሳርማ እግር የተተካው ታሪክ ፍዝነቱ የበዛ ነው። ጭልጥ ካለ ምናባዊ ፈጠራ ወደ አረጀ አፈጀ ደረቅ ዘገባ በመንደርደራችን የተነሳ በጋመው ስሜታችን ላይ ቀዝቃዛ ውኃ ይቸለሳል፡፡ የመጽሐፉ ገዢ ርዕስ የአንሳርማን እግር ተከታይ ቢሆን ኖሮ ሚዛናዊ ስሜት በመፍጠሩ ረገድ የሚታማ አይሆንም ነበር። አንሳርማ እና የረከሰ ፍርድ ሰም እና ወርቅ ናቸው። አንሳርማ “ስክሪፕት”፣ የረከሰ ፍርድ ተውኔት ነው፡፡ እነዚህ ተደጋጋፊ ታሪኮች እግር በእግር እንዳይከታተሉ የይለፍ ፍቃድ ተነፍገዋል፡፡
ደግነቱ ደራሲውን ብዙም ሳናማው መልሶ ይክሰናል፡፡ በጥበብ ማጀቱ ከቋጠረው ጥሪት ያለ ስስት እያቃመሰን የዳመነውን  ገጽታችንን ለማፍካት ይተጋል፡፡ የግብዣ ማግደርደሪያውን በገጽ 52 ላይ እናገኛለን፡-
“ማስታወሻ ደብተሬን በገለበጥኩ ቁጥር ፊቴ ፈገግ፣ቅጭም ይል ነበር፡፡ ገጹን እንዲህ የሚቀያይረው አስደሳች፣አስገራሚና አሳዛኝ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በጉዳዮቹ ውስጥ ደግሞ መረጃ የሚሰጡ ሰዎችና የሚጠይቁ ጋዜጠኞች አሉ፡፡ በዜና ካበጡ በርካታ መረጃዎች ውስጥ የንባብ ብርሃን ያላገኙትን ጥቂቶቹን መራርጬ እነሆ እንድታነቧቸው ጋበዝኳችሁ፡፡”
በአለፍ ገደም የተቃረሙት እውነታዎች በእርግጥም የባለሙያ እጅ የጎበኛቸው ክሽኖች ናቸው፡፡ አንዳንዴም ፊታችንን ቅጭም እያደረገን አንዳንዴም በፈገግታ እየተደነቃቀፍን ከገበታው እንቋደሳለን፡፡ ገጽ 54 ላይ ይህ ግርምት ተከትቧል፡-
“ቦታው አዲስ አበባ ነው፡፡ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ አጠቃላይ ስብሰባ ጠርቶ በተለያዩ ርዕስ ጉዳዮች ላይ አባላቱ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ አንዳንዴ ከዋና ርዕስ ያፈነገጡ አንዳንድ ጉዳዮች ሳይታሰብ ቦግ ብለው ይወጣሉ፡፡ አንዳንድ አባላት አስተያየት ከሚሰጡበት ዋና ጉዳይ አስቀድመው እንደ አፍ ማሟሻ ይሁን ነገር ማጣፈጫ በስሜት የሚናገሯቸው ቃላት ትኩረት ሳቢና ፈገግታ ጫሪ ናቸው፡፡
አንድ ታሳታፊ እድሉ ከተሰጣቸው በኋላ የተናገሩት ስለካድሬ ነበር ”ካዴሬ” አሉ ሰውዬው፣ቃሉን ጠበቅ አድርገው፣ ”ካድሬ የሚለውን የኢህአዲግ ቋንቋ መጠቀማችን ያስንቀናል፡፡ ካድሬ የሚለው ቃል ፊታውራሪ፣ዲያቆን ወይም ስልጡን ተብሎ እንዲተካ እጠይቃለሁ።” ጥያቄው በወቅቱ አስቆኝ ስለነበር ምላሽ ይሰጠው ይሆን በሚል ተጠባበቅኩ፣ መድረክ መሪዎቹ ጉዳዩ አላስጨነቃቸውም ወይም ከግምት በታች ሆኖባችው ነው መሰለኝ ቅርጫት ውስጥ ሲወረውሩት ተመለከትኩ“
የረከሰ ፍርድ በመጽሐፉ ገዢ ርዕስነት መመረጡ አይበዛበትም፡፡ አንድን ሃገር እንደ ካስማ ተሸክሞ አስተማማኝ መደላደል ላይ የሚያቆመው የሕግ ልዕልና ነው፡፡ የሕግ ልዕልና በነጠፈበት ሃገር የአገዛዙ መርህ ጉልበት ይሆናል፡፡ በሕግ አራዊት መርህ /Mighty is right/ የተቃኘ ሥርዓት ፍትህን ያጓድላል፣ብይን ያረክሳል፤ በእዚህም ምክንያት ሃገር በውድቀት ተዳፋት ላይ እንድትንደረደር ጥርጊያውን ያመቻቻል፡፡ የረከስ ፍርድ ጭብጥም ከእዚህ ብዙ ፈቀቅ ያለ አይደለም፡፡ በእየዘመኑ ሰለባ የሆኑትን ሰማዕታት እማኝ እያደረገ የውድቀቱን ሸለቆ መጠቆም ዋንኛ ዓላማው ነው፡፡
የረከሰው ፍርድ ትዕይንት በታላቁ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ ቡራኬውን በእዚህ መልኩ ይጀምራል፡-(ገጽ 75)
“ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉ?” ሲል አንደኛው ገዳይ ጠየቃቸው
“ይህ የአንት ሥራ ነው!” ሲሉ በተረጋጋ መንፈስ መለሱ፡፡ መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱስ ተሳለሙ፡፡ የያዙትን መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ፡፡ የኪሳቸውን ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከተቱት”
ከአቡነ ጴጥሮስ የጀመረን ልክፍት እያንደረደረ ከእዚህ ዘመን ላይ ያደርሰናል፡፡ ደራሲው ለፍርድ መራከስ እንደ እማኝነት ከወሰዳቸው ንጹሓን መካከል የጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ የፍርድ ሁኔታ በተለይ አቅጣጫ መታየት ነበረበት፡፡ ጀኔራሉን ለፍርድ መራከስ ዋቢ ለማድረግ የሕግ-መርህን መጣስ የግድ ይኖርበታል፡፡ በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ወራራ ላይ በጀግንነት ሲዋደቁ የነበሩት አርበኞች በንጉሱ ባለሟልነት ተፈርጀው አንደዋዛ ጭዳ የሆኑት በጀኔራሉ እጅ ነበር፡፡ ታዲያ ለጠፋው ነፍስ ተመጣጣኝ ብይን መስጠት ምኑ ላይ ፍርድን የሚያርክስው? በአንጻሩ ይህንን ብይን ቸል ማለት ከሕግ መርህ ጋር ፊት ለፊት የሚያላትም፣ የማያመልጡት ደረቅ እውነታ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ እዚህ ጋ ለክርክር ከሚጋብዘው የጀኔራል መንግሥት ንዋይ የሞት ፍርድ ይልቅ የጀግናው በላይ ዘለቀ ኢፍትሃዊ ብይን መካተት ቢችል ኖሮ መልካም  ጎኑ የበዛ ይሆን ነበር፡፡ በርሃ ለበርሃ ለእናት ሃገሩ ሲማስን የኖረው ጀግናው በላይ ዘለቀ፣ ከባንዳዎች ቀድሞ ክንዱን እንዲንተራስ የተፈረደበት ታሪካዊ ክስተት ከሁሉም ልቆ ዓይን የሚገባ የሕግ ክሽፈት ነው፡፡
ፀሐፊው የረከሰ ፍርድን የመሰለ ቋጥኝ ቁምነገርን ባነሳበት እጁ የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም  ወርቃማ ሐሳቦችን እንደ ጭብጦ ጨብጦ ከአንጀታችን የሚጠጋ ጉርሻ ያቀብለናል፡፡ እስቲ ይህንን ውስጥን የሚበረብር የፕሮፌሰሩን ወርቃማ ሐሳብ ከገጽ 103 ላይ እንቃኝ፡- “ኢትዮጵያዊነት ከጎሰኝነት በላይና ውጭ የሆነ አጠቃላይ ማንነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የደጋው ብርድና የቆላው ሙቀት የሚገናኙበት፣የደጋው ዝናብ ከቆላው ወንዝ ጋር የተዛመደበት ኃይል ነው። ኢትዮጵያዊነት ለሙሴ፣ለክርስቶስና ለመሐመድ የሚጨሰው እጣን በእርገት መጥቆ የሚደባለቅበት እምነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በቄጤማ ጉዝጓዝ ላይ የሚታየው መተሳሰብና መፈቃቀር ነው። ኢትዮጵያዊነት የአስተዋይነት፣ የሚዛናዊነትና የጨዋነት ባህርይ ነው፤ ረጅምና ተጽፎ ያላለቀም ታሪክ ነው”
 ደራሲ አለማየሁ ገበየሁ ስሜቱ ስስ የሆነበትን ሥፍራ አንባቢ ላይ ለማጋባት በብርቱ የተውተረተበት ክፍል ይህ የፕሮፌሰሩ ወርቃማ ሐሳቦች ታሪክ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥም በፕሮፌሰሩ ወርቃማ ሐሳቦች ላለመነደፍ ፀጉረ ልውጥ፣ ባዕድ፣ሳላቶ፣ባንዳ፣”ፋሺስት” መሆንን ይጠይቃል፡፡     የረከስ ፍርድ ጅማሮ እንጂ መቋጫ አይመስለኝም፡፡ አለማየሁ ገና ብዙ የሚናገራቸው ወይም የሚተነፍሳቸው ቁጭቶች፣ትዝብቶች እና ስላቆች እንዳሉት ከእያንዳንዱ ታሪክ ጀርባ የመሸጉ እውነታዎች ሹክ ይሉናል፡፡ ለአሁኑ ግን እጅ ብንነሳው አይበዛበትም፡፡   

Read 1464 times