Saturday, 11 July 2015 12:22

በአውሮፓ የዝውውር ገበያው ከግዢና ሽያጭ ይልቅ ወሬ በዝቶበታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(6 votes)

      በአውሮፓ እግር ኳስ የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ከተከፈተ ሁለት ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ ዘንድሮ የዝውውር መስኮቱ ከተግባራዊ ግብይት ውጭ በገበያው አነጋጋሪ ሆነው በሰነበቱ ወሬዎች  የተሞላ መስሏል። ከተጨዋቾች ሰርጂዮ ራሞስ፤ አርዳም ቱራም፤ ራሂም ስተርሊንግ እና ፖል ፖግባ የዝውውር ገበያው አበይት ወሬ ሆነው ሰነባብተዋል፡፡ ከክለቦች በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የተጨዋቾች የዝውውር ህገ ደንብ ተቀጥተው የነበሩት ፓሪስ ሴንትዠርመን፤ ቼልሲ እና ባርሴሎና ወደ ገበያው መመለሳቸው ሲያነጋግር እንደ ሊቨርፑል አይነት ክለቦች ደግሞ ከበርካታ የዝውውር ወሬዎች ጋር ስማቸው ሲነሳ አሳልፈዋል፡፡  በሌላ በኩል የጣሊያን ሴሪ ኤ ክለቦች ወደ ዝውውር ገበያው በንቁ ተሳትፎ መግባታቸው ሰፊ ሽፋን እያገኘ ነው፡፡ ከ2 ሳምንት በፊት የተጀመረው የዝውውር ገበያው ከ48 ቀናት በኋላ የሚዘጋ ይሆናል፡፡
የስፔኖቹ ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና፤ የእንግሊዞቹ የማንችስተር ከተማ ክለቦች እና ቼልሲ እንዲሁም የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንትዥርመን ባለፉት የውድድር ዘመናት በዝውውር ገበያው ያደርጉት የነበረው ንቁ ተሳትፎ ዘንድሮ የቀዘቀዘ ይመስላል፡፡ በዘንድሮ ገበያ ግን ባልተለመደ ሁኔታ ትልልቅ ተጨዋቾችን እያሳደዱ እያስፈረሙ የሚገኙት የጣሊያን ክለቦች ሆነዋል። በተለይ ባለፈው የውድድር ዘመን በሴሪኤው እስከ 3 ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት ጁቬንትስ፤ ኢንተርሚላንና ሮማ በገበያው እያንዳንዳቸው ከ3 ተጨዋቾች በላይ በመግዛት ተጠናክረዋል፡፡ የጣሊያን ክለቦች ቢያንስ ላለፉት 5 የውድድር ዘመናት በብድር፤ ያለዝውውር ዋጋ በሚለቁ ተጨዋቾች እና በአውሮፓ ደረጃ በቀነሰ የፉክክር ደረጃቸው ተዳክመው ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ባለፈው ዓመት ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በመድረስ ጁቬንትስ ባገኘው ስኬት በመነቃቃት ላይ ናቸው፡፡ አዳዲስ ባለሃብቶች  በጣሊያን ክለቦች ላይ ፍላጎት በማሳደር ኢንቨስትመንታቸውን ማጠናከራቸው ገና ከጅምሩ ለውጥ በመፍጠር ላይ ነው፡፡ በወቅቱ የዝውውር ገበያ የሴሪኤ ክለቦች በሁለት ሳምንታት ውስጥ እስከ 262 ሚሊዮን ዩሮ አውጥተዋል፡፡
በተያያዘ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በሁለቱ ክለቦች ማን ሲቲ እና ፒኤስጂ የተጨዋቾች የዝውውር ወጪ እና የቡድን ስፋት የጣለውን ገደብ ማንሳቱ አበይት መነጋገርያ እየሆነ መጥቷል፡፡ ማንችስተር  ሲቲ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በተጣለበት እግድ በሻምፒዮንስ ሊግ በ21 ተጨዋች እንዲሳተፍ እና ወጪው ከፍተኛው በ45 ሚሊዮን ዩሮ እንዲገደብ ተወስኖ ለሶስት የውድድር ዘመን 49 ሚሊዮን ፓውንድ ተቀጥቶ ነበር፡፡ በአውሮፓ የእግር ኳስ ማህበር አማካኝነት በፋይናንስ ጨዋነት ደንብ ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት ተግባራዊ በመሆኑ የአህጉሪቱ ትልልቅ ክለቦች እዳ ከ1.7 ቢሊዮን ዩሮ ወደ 487 ሚሊዮን ዩሮ ሊወርድ ችሏል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ደንቡን ተግባራዊ በማድረግ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ23 ክለቦች ጋር በተለይ ሲቲ፤ ፒኤስጂ ፤ ኢንተርሚን እና ከመሳሰሉት ጋር በቅርበት ይሰራ ነበር፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ሰሞኑን ይህን መመርያ መጠነኛ መሻሻል አድርጎበት ለሚቀጥሉት ሶስት የውድድር ዘመናት ክለቦች አጠቃላይ ኪሳራቸው ከ45 ወደ 30 ሚሊዮን ዩሮ እንዲወርድ አድርጓል፡፡በአምስቱ ታላቅ ሊጎች የሚወዳደሩ 98 ክለቦች ባለፈው የውድድር ዘመን በተካሄዱ የዝውውውር ገበያዎች በድምሩ እስከ 8.6 ቢሊዮን ዩሮ ያወጡ ሲሆን ይህም በአንድ ክለብ አማካይ 87.7 ሚሊዮን ዩሮ ይሆናል፡፡
ከእንግሊዝ ክለቦች በዝውውር ገበያው ንቁ ተሳትፎ በማድረጉ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሚሆነው እስካሁን አምስት ተጨዋቾች ያስፈረመው ሊቨርፑል ነው። በተለይ ብራዚላዊው ሮበርቶ ፊርሚኖ ያዛወረበት የ41 ሚሊዮን ዩሮ ሂሳብ የፕሪሚዬር ሊጉ ትልቁ ክፍያ ሲሆን እውቁን የክለቡ አምበል ስቴቨን ጄራርድ ወደ አሜሪካ ያሰናበተበት ሁኔታ አበይት ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ ስተርሊንግ የዝውውር ገበያው አበይት መነጋገርያ ሊሆን የበቃ ነው፡፡ ተጨዋቹ ከክለቡ ሊቨርፑል እንደሚለቅ መወራት ከጀመረ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ማን ሲቲ ዋና ፈላጊው ሲሆን በመጀመርያ 25 ከዚያ 30 እንደገና 35 ሚሊዮን ዩሮ ሂሳብ በማቅረብ ሊያዛውረው ቢታገልም አልተሳካለትም፡፡ ሲቲ አሁን የዝውውር ሂሳቡን ከሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ጋር ወደ 40 ሚሊዮን ፓውንድ አሳድጎታል፡፡
አርሰናል ባልተገለፀ የዝውውር ሂሳብ ከቼልሲ ፒተር ቼክን ማዛወሩና ሉካስ ፖዶልስኪ ለፌነርባቼ መሸጡን ጨምሮ አምስት ተጨዋቾች ማሰናበቱ፤ ራዳሜል ፋልካኦን በውሰት ከሞናኮ አስመጥቶ ድሮግባ እና ፒተር ቼክን ጨምሮ አምስት ተጨዋቾችን የለቀቀው ቼልሲ፤  ማንሲቲ በግብይቱ ከመወራቱ በቀር የጎላ ዝውውር አለማድረጉ፤ ማን ዩናይትድ ከሆላንዱ ፔኤስቪ ሜምፊስ ዴምባይን በ30 ሚሊዮን ዩሮ በማዛወር የፈፀመው ግብይት ዋናዋናዎቹ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የዝውውር ክንውኖች ናቸው፡፡ በሌሎች የአውሮፓ ሊጎች ባለፉት 15 ቀናት ከተፈፀሙ ግብየቶች ዳኒሎ በ23 ሚሊዮን ፓውንድ ከፖርቶ ወደ ሪያል ማድሪድ፤ ዣቪ ከባርሴሎና በነፃ ዝውውር ወደ አልሳድ፤ ሳሚ ከዲራ ከሪያል ማድሪድ ወደ ጁቬንቱስ በነፃ፤ ካርሎዝ ቴቬዝ ከጁቬንትስ ወደ አርጀንቲናው ክለብ ቦካ ጁኒዬርስ በነፃ እንዲሁም አንድሬ ፒርሎ ከጁቬንትስ ወደ አሜሪካው ኒውዮርክ ሲቲ በነፃ ያደረጓቸው ዝውውሮችም ይጠቀሳሉ፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ ምርጥ ግዢ የሚባለው ከ20 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የዝውውር ሂሳብ የሚከፈልበት ግብይት ነው፡፡በሊቨርፑልና በአርሰናል ክፉኛ ቢፈለግም ከፖርቱጋሉ ኤፍሲ ፖርቶ ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ በ35 ሚሊዮን ዩሮ የተዛወረው ጃክሰን ማርቲኔዝ ፤ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ወደ ጣሊያኑ ጁቬንትስ በ19 ሚሊዮን ዩሮ ሂሳብ የገባው ማርዮ ማንዱዚክ፤ ከፈረንሳዩ ክለብ ማርሴይ ወደ ኤፍሲ ፖርቶ የዞረው ጂያኔሊ ላምቡላ፤ ከፈረንሳዩ ሞናኮ ወደ ኢንተርሚላን በ35 ሚሊዮ የተሻገረው ጄዮፍሪ ኮንዶጊባ፤ ከጀርመኑ ክለብ ባየር ሌቨርኩዘን ወደ ሌላው የጀርመን ክለብ ቦርስያ ዶርትመንድ የሄደው ጎንዛሎ ካስትሮ ምርጥ ዝውውሮች ተብለዋል፡፡
ትራንስፈርማርከት ተቀማጭነቱን በጀርመን አድርጎ በስምንት የአውሮፓ አገራት ቋንቋዎች የሚሰራጭ እና ከተመሰረተ 15 ዓመታት ያስቆጠረ ድረገፅ ነው፡፡ ድረገፁ ስለ ዓለም እግር ኳስ የተለያዩ የውጤት መረጃዎች፤ ጥቆማዎች እና ዜናዎች እንዲሁም የዝውውር ገበያ ምልከታቸውን በይዘቱ ያካትታል። ትራንስፈርማርኬት የተጨዋቾች የዝውውር ገበያን በመላው ዓለም በመከታተል በሚያደርጋቸው ጥጭናቶች የሚያቀርባቸው ግምታዊ ስሌቶች እና የገበያ ግምገማዎች በትክክለኛነታቸው ከፍተኛ ተዓማኒነት አትርፈውለታል።
በ5ቱ ታላላቅ ሊጎች የተጨዋቾች ዋጋ ተመንና የመጤዎች ብዛት
ከዚህ በታች የቀረበው የአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጎች ውስጥ በሚወዳደሩ ክለቦች የሚገኙ ተጨዋቾች ብዛት ፤ አጠቃላይ የዋጋ ተመን እንዲሁም ከተለያዩ አገራት በየሊጎቹ የሚጫወቱ መጤ ፕሮፌሽናሎችን ብዛት ይጠቁማል፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 20 ክለቦች፤ 551 ተጨዋቾች፤ 3.8 ቢ.ዩሮ፤ 375 መጤ ተጨዋቾች
የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ 20 ክለቦች፤ 551 ተጨዋቾች፤ 3.8 ቢ.ዩሮ፤ 168 መጤ ተጨዋቾች
የጣሊያን ሴሪኤ 20 ክለቦች፤ 592 ተጨዋቾች፤ 2.42  ቢ.ዩሮ፤ 304 መጤ ተጨዋቾች
የፈረንሳይ ሊግ 1 20 ክለቦች፤ 527 ተጨዋቾች፤ 1.38 ቢ.ዩሮ፤ 237 መጤ ተጨዋቾች
የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 18 ክለቦች፤ 513 ተጨዋቾች፤ 2.34 ቢ.ዩሮ፤ 246 መጤ ተጨዋቾች
አዳዲስ ዋጋ የወጣላቸው
የወቅቱ የዝውውር ገበያ ያወጣቸው እና አዳዲስ ዋጋ የወጣላቸው 5 ተጨዋቾች ከዚህ በታች የቀረቡት ናቸው። ተጨዋቾቹ በአመዛኙ የደቡብ አሜሪካ አገራትን የወከሉ እና በቅርቡ ተካሂዶ ከነበረው ኮፓ አሜሪካ ጋር በተያያዘ ትኩረት ያገኙ ናቸው፡፡ ከመካከላቸው አንድ የአልጄርያ ዜግነት ያላው ተጨዋችም አለ፡፡ ደቡብ አሜሪካዊያኑ  ተጨዋቾች በሁለቱ የፖርቱጋል ክለቦች ቤነፊካ እና ኤፍሲ ፖርቶ የሚጫወቱ ናቸው፡፡ የተጨዋቾቹ ሙሉ ስም፤ የሚጫወቱበት ስፍራ፤ ዜግነታቸው፤ እድሜያቸው፤ ክለባቸው እና የዋጋ ተመናቸው በቅድመ ተከተል እንደቀረበው ነው፡፡
ኒኮላስ ጋይቴን ፤ ግራ ክንፍ ፤አርጀንቲናዊ፤ እድሜ 27 ፤ቤነፊካ፤ 27 ሚሊዮን ዩሮ
ዊልያም ካርቫልሆ፤ የመሃል ተከላካይ፤ ፖርቱጋላዊ፤ እድሜ 23 ፤ስፖርቲንግ ሊዝበን ፤ 26 ሚሊዮን ዩሮ
ቶቶ ሳልቪዮ፤ ቀኝ ክንፍ ፤ አርጀንቲናዊ ፤እድሜ 24 ፤ቤነፊካ ፤22 ሚሊዮን ዩሮ
አሌክስ ሳንድሮ ፤ግራ ተመላላሽ ፤ብራዚላዊ፤ እድሜ 24 ፤ኤፍሲ ፖርቶ፤ 20 ሚሊዮን ዩሮ
ያሲኒ ኢብራሂሚ ፤ግራ ተመላላሽ፤ አልጄርያዊ ፤እድሜ 25፤ኤፍሲ ፖርቶ፤ 18.5 ሚሊዮን ዩሮ
ዋጋቸው የጨመረላቸው
ከዚህ በታች የቀረቡት አምስት ተጨዋቾች በዝውውር ገበያው አስቀድሞ ከነበራቸው ዋጋ ጭማሪ ያሳዩ ናቸው። ከመጀመርያዎቹ አራት ተጨዋቾች  ሶስቱ በስፔኑ ሪያል ማድሪድ፤ አንዱ በባርሴሎና የሚገኙ ናቸው፡፡
አንጄል ዲማርያ ፤ቀኝ ክንፍ ፤አርጀንቲናዊ፤ እድሜ 27 ፤ያሳየው የዋጋ ጭማሪ 116.7 በመቶ ፤የወቅቱ ዋጋ 65 ሚሊዮን ዩሮ
ጄምስ ሮድሪጌዝ ፤የአጥቂ አማካይ ፤ኮሎምቢያዊ፤ እድሜ 23 ፤ያሳየው የዋጋ ጭማሪ 71.4 በመቶ ፤የወቅቱ ዋጋ 60 ሚሊዮን ዩሮ
ክርስትያኖ ሮናልዶ፤ ግራ ክንፍ፤ እድሜ 30፤ ያሳየው የዋጋ ጭማሪ 20 በመቶ ፤የወቅቱ ዋጋ 120 ሚሊዮን ዩሮ
ኔይማር፤ ግራ ክንፍ፤ ብራዚላዊ፤ እድሜ 23፤ ያሳየው የዋጋ ጭማሪ 33.3 በመቶ፤ የወቅቱ ዋጋ 80 ሚሊዮን ዩሮ
ኮኬ፤ ግራ ክንፍ፤ ብራዚላዊ፤ እድሜ 23፤ ያሳየው የዋጋ ጭማሪ 66.7 በመቶ፤ የወቅቱ ዋጋ 50 ሚሊዮን ዩሮ
ዋጋቸው የወረደባቸው
በእድሜያቸው መግፋት፤ በብቃታቸው መውረድ እና ተፈላጊነታቸው እየቀነሱ በመምጣቱ ትልልቅ ተጨዋቾች ዋጋቸው እየወረደ መጥቷል፡፡ በዘንድሮ የተጨዋቾች የዝዝዝውር ገበያ አስቀድሞ ከነበራቸው ዋጋ የቀነሰባቸው 5 ተጨዋቾች የሚከተሉት ናቸው፡፡
አንድሬስ ኢንዬስታ የመሃል አማካይ፤ ስፔናዊ፤ እድሜ 37፤ በ20 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋው ቀንሶ የወቅቱ ግምቱ 35 ሚሊዮን ዩሮ
ኤዲሰን ካቫኒ የመሃል አጥቂ፤ ኮሎምቢያዊ፤ እድሜ 28፤ በ18 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋው ቀንሶ የወቅቱ ግምቱ 42 ሚሊዮን ዩሮ
ሮቢን ቫንፒርሲ የፊት አጥቂ፤ ሆላንዳዊ፤ እድሜ 31፤ በ15ሚሊዮን ዩሮ ዋጋው ቀንሶ የወቅቱ ግምቱ 25 ሚሊዮን ዩሮ
ራዳሜል ፋልካኦ የፊት አጥቂ፤ ኮሎምቢያዊ ፤እድሜ 29፤ በ15ሚሊዮን ዩሮ ዋጋው ቀንሶ የወቅቱ ግምቱ 45 ሚሊዮን ዩሮ
ማርዮ ባላቶሊ የፊት አጥቂ፤ ጣሊያናዊ፤ እድሜ 24፤ በ15 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋው ቀንሶ የወቅቱ ግምቱ 15 ሚሊዮን ዩሮ
ከአምስቱ ተጨዋቾች ሌላ  በገበያው ዋጋቸው የወረደባቸው ሌሎቹ ተጨዋቾች  ዝላታን ኢብራሞቪች ከ28 ወደ 15 ሚሊዮን ዩሮ፤ ሽዋንስታይገር ከ40 ወደ 28 ሚሊዮን ዩሮ፤ ቶሬስ ከ19 ሚሊዮን ወደ 7 ሚሊዮን ዩሮ፤ ላሳና ዲያራ ከ16 ወደ 4 ሚሊዮን እንዲሁም ሉካስ ፖዶልስኪ ከ33 ወደ 12 ሚሊዮን ዩሮ ተመናቸው አሽቆልቁሏል፡፡
ከፍተኛ የዝውውር ዋጋዎች
በትራንስፈር ማርኬት ድረገፅ  በዓለም እግር ኳስ የተመዘገቡ ከፍተኛ የዝውውር ዋጋዎችን በሶስት ዘርፎች መድቦ መክፈል ይቻላል፡፡ 120 ሚሊዮን ዩሮ የተተመኑት ሁለት ተጨዋቾች ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስትያኖ ሮናልዶ ናቸው፡፡ በሚሊዮን ዩሮ ዋጋቸው የተተመነላቸው  አራት ተጨዋቾች ጀምስ ሮድሪጌዝ፤ ኔይማር ጋሬዝ ባሌ ሲሆኑ አንጄል ዲማርያ በ65 ሚሊዮን ዩሮ፤ ፈረንሳዊው ፖል ፖግባና ጀርመናዊው ቶማስ ሙለር በ55 ሚሊዮን ዩሮ ከፍተኛ ዋጋቸው ይጠቀሳሉ፡፡ እስከ 10ኛ ደረጃ የሚሰጣቸውን ከፍተኛ የዝውውር ዋጋዎችም በትራንስፈርማርከት ድረገፅ ተመዝግበዋል፡፡ ማርዮ ጎትዜ፤ ኮኬ፤ ዲያጎ ኮስታ፤ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ፤ ማርኮ ሬውስ፤ ቶኒ ክሮስ፤ ሉካ ሞድሪች ሰርጂዮ አጉዌሮ ካሪም ቤንዜማ እና ሴስክ ፋብሪጋስ በ50 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋቸው ሲጠቀሱ፤ እነ አሌክሲ ሳንቼዝ፤ ሰርጂዮ ቡስኬትስ፤ ፋልካኦ በ45 ሚሊዮን ዶላር የዋጋ ከተማን የገበያውን ውድ ዋጋ ያገኛሉ፡፡
በትራንስፈርማርከት ድረገፅ ከላይ የተዘረዘሩት ተጨዋቾች በከፍተኛ የዝውውር ዋጋቸው ቢጠቀሱም ሲአይኢኤስ የተባለ የዓለም እግር ኳስ መረጃ አሰላሳይ ተቋም ባወጣው ጥናት በሚሰጣቸው የዋጋ ግምት የዘረዘራቸው ተጨዋቾች፤ ዋጋቸው እና ደረጃቸው ከዚህ የሚከተለው ነው፡፡ የተጨዋቾቹን ዋጋ ለማስላት ተቋሙ ከ2009 እኤአ ጀምሮ የተፈፀሙ ግብይቶችን አገናዝቧል።
ሊዮኔል ሜሲ 220 ሚሊዮን ዩሮ
ክርስትያኖ ሮናልዶ 133 ሚሊዮን ዩሮ
ኤዲን ሃዛርድ ቼልሲ 99 ሚሊዮን ዩሮ
ዲያጎ ኮስታ ቼልሲ 84 ሚሊዮን ዩሮ
ፖል ፖግባ ጁቬንትስ 72 ሚሊዮን ዩሮ
ሰርጂዮ አጉዌሮ ማን ሲቲ 65 ሚሊዮን ዩሮ
ራሂም ስተርሊንግ ሊቨርፑል 63 ሚሊዮን ዩሮ
ሴስክ ፋብሪጋዝ ቼልሲ 62 ሚሊዮን ዩሮ
አዘሌክሲ ሳንቼዝ አርሰናል 61 ሚሊዮን ዩሮ
ጋሬዝ ባሌ ሪያል ማድሪድ 60 ሚሊዮን ዩሮ
በዝውውር ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ተጨዋቾች
ዝላታን ኢብራሞቪች በ7 ዝውውሮች 169.1 ሚሊዮን ዩሮ
ጄምስ ሮድሪጌዝ በ4 ዝውውሮች 132.63
ኒኮላስ አኔልካ በ8 ዝውውሮች 127.36
ሄርናን ክሬስፖ በ4 ዝውውሮች 119.27
ሴባስትያን ቬሮን በ6 ዝውውሮች 116
አንጄል ዲማርያ በ3 ዝውውሮች 116
ሊውስ ስዋሬዝ በ4 ዝውውሮች 115.8
ፋልካኦ በ4 ዝውውሮች 113.03
ሮናልዶ በሁለት ዝውውሮች 111.5
ጋሬዝ ባሌ በ2 ዝውውሮች 108.7
በዝውውራቸው ከፍተኛ ትፍ ያገኙ ተጨዋቾች
ጋሬዝ ባሌ 79.3 ሚሊዮን ዩሮ
ሮናልዶ 76.5
ዚነዲን ዚዳን 70 ሚሊዮን ዩሮ
ሊውስ ፊጎ 57.5
ሪካርዶ ካካ 56.75
ሊውስ ስዋሬዝ 54.5
ኤድሰን ካቫኒ 52.5
ሄርናን ክሬስፖ 51
ኢብራሞቪች 44.7
አንጄል ዲማርያ 42

Read 6274 times