Saturday, 11 July 2015 12:20

ዋሊያዎቹ ከ2 ሳምንት በኋላ ወደ ዝግጅታቸው 2ኛ ምእራፍ ይገባሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫና ለ4ኛው የቻን ውድድር ለማለፍ በሚደረጉ ማጣርያዎች አመርቂ ውጤት ያስመዘገበው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 2ኛ ምእራፍ ዝግጅቱን ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚቀጥል ታውቋል። በሁለቱ አህጉራዊ ውድድሮች ዋልያዎቹ  ሦስት ጨዋታዎች በማድረግ በሁለቱ አሸንፈው በአንዱ አቻ ወጥተዋል፡፡ በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በምድብ 10 ከአልጄርያ፤ ሌሶቶ እና ሲሸልስ ጋር የሚገኙት ዋልያዎች በምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታቸው ሌሶቶን በሜዳቸው 2ለ1 በማሸነፍ   በ3 ነጥብ በግብ ክፍያ በአልጄርያ  ተበልጠው መሪነቱን ተጋርተዋል፡፡ በቻን ቅድመ ማጣርያ ደግሞ ባለፈው ሰሞን ናይሮቢ ላይ ከኬንያ አቻቸው ጋር 0ለ0 ከተለያዩ በኋላ በ2ለ1 የደርሶ መልስ ውጤት ጥለው በማለፍ ለመጨረሻው ማጣርያ አልፈዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ቀጣይ ተጋጣሚያቸው ከሜዳ ውጭ ሲሸልስ ስትሆን በቻን የመጨረሻ ማጣርያ ደግሞ በደርሶ መልስ ከብሩንዲ ጋር ይገናኛሉ፡፡
ዋልያዎቹ ከሁለት ሳምንት ዕረፍት በኋላ ወደ ዝግጅታቸው ሁለተኛ ምእራፍ እንደሚገቡና  ለቀጣዩ ግጥሚያዎቻቸው መስራት እንደሚጀምሩ እና  በነሐሴ ወር ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ አቋማቸውን እንደሚፈትሹ ይጠበቃል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሜዳው ላይ እና ከሜዳው ውጭ የወዳጅነት ጨዋታዎች ለማድረግ የሚፈልጉ አገራት መበርከታቸውን ከፈዴሬሽኑ የሚወጡ መረጃዎች ይገልፃሉ፡፡
በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ከኢትዮጵያ ጋር ከተደለደሉት ቡድኖች በቻን ማጣርያቸው ሲሸልስ ስትወድቅ፤ ሌሶቶ ግን አልፋለች፡፡ ሲሸልስ በሞዛምቢክ 9ለ1 በሆነ የደርሶ መልስ ውጤት ተሸንፋ ስትወድቅ ፤ ሌሶቶ ደግሞ ቦትስዋናን ጥሎ በማለፍ ለመጨረሻ ዙር ማጣርያ በቅታለች፡፡ በመጨረሻ ዙር የቻን ማጣርያ የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የሆነችው ብሩንዲ በቻን ውድድር ለመጀመርያ ጊዜ በ2014 ተሳትፋ የነበረ ሲሆን ሱዳንን በመለያ ምቶች 4ለ3 ጥላ በበማፍ ነበር፡፡ በ2009 እኤአ በደርሶ መልስ ማጣርያ ብሩንዲን ያሸነፈችው ሩዋንዳ ስትሆን በ2011 እኤ ደግሞ ኡጋንዳ ነበረች፡፡ ሲሸልስ በ2017 አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ 2ኛ ጨዋታ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በሜዳዋ ከመገናኘቷ  በፊት ጠንካራ ዝግጅት ለማድረግ ወስናለች፡፡ አሰልጣኙ ማቲዮት ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ቡድናቸው ዛሬ እና ነገ ወደ አልጄርያ በማቅናት  የሁለት ሳምንት ዝግጅት በካፕ ተቀምጦ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ዝግጅት በኋላም በኢንድያን ኦሽን ጌምስ በመካፈል ከማዳጋስካር ፤ ከማልዴቪስና  ከማዮቴ ደሴት ብሄራዊ  ቡድኖች ጋር በምድብ ማጣርያ ይጫወታል፡፡

Read 1860 times