Saturday, 11 July 2015 12:00

ረመዳን እና ነብዩ ሙሐመድ

Written by  ኑርሁሴን
Rate this item
(22 votes)

    በረመዳን ወቅት የነበሩትን የነብዩ ሙሐመድ ተግባሮች ምን እንደሚመስሉ ብንገምት ምን አልባት ከባድ አድርገናቸው ሊሆን ይችላል፡፡ እውነት የነብዩ የረመዳን ተግባሮች ከባድ ነበሩ?
አምላክ ነብያትን ከራሳቸው ህዝብ መካከል መርጦ ሲልክ÷ህዝቦችን ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲያስገቡና የአምላክ ተገዢዎች እንዲያደርጓቸው በሚል ነው፡፡ ነብያቶች እንደ ሁላችንም ሰዎች ናቸው፡፡ ራእይ መቀበላቸው ወይም በነሱ እና በአምላክ መካከል አንድ ቅዱስ መንፈስ መኖሩ ከኛ የተለዩ ያደርጋቸዋል። ከአምላክ የተቀበሉት ራእይ (ህጐች)፤ በሰው አቅም የሚቻል መሆኑን ለማስተማር፣ በተግባር አሳይተው ለኛ አርአያነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡
ነብዩ ሙሐመድ ልክ እንደ ማንኛውም ሰው ይበላሉ፣ ይተኛሉ፣ ሚስት አግብተው ወልደዋል፣ ማንም የሚያደርገውን ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን የሰው ልጆች አርአያ መሆናቸውንም አሳይተዋል፡፡ ነብዩ አርአያነታቸውን ሲያሳዩ ከተሰጣቸው መመሪያ ውጭ ሆነው አይደለም። የአምላክን ራእይ በተግባር ማሳየታቸው፤ የአምላክ መመሪያዎች በሰው ልጅ አቅም መከወን እንደሚችሉ ለመጠቆም ነው፡፡
ነብዩ ተግባር ላይ አውለው ካሳዩን የአምላክ ትሩፋቶች መካከል አንዱ የረመዳን ፆም ነው፡፡ አማኞች በረመዳን ወቅት የነበረውን የነብዩ የህይወት እንቅስቃሴዎች የመከተል ግዴታ አለባቸው፡፡ ነብዩ በሚስታቸው አኢሻ “የሚራመድ ቁርአን”  መባላቸው አጠቃላይ ህይወታቸው የቁርአን ትርጓሜ በመሆኑ ነው፡፡
ፆም በአማኞች ላይ ግዴታ መሆኑን አምላክ በቁርአን ውስጥ እንዲህ ይገልፀዋል፡-  
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ፆም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት ህዝቦች ላይ እንደተፃፈው ሁሉ፣ በናንተም ላይ ተፃፈ (ተደነገገ)፣ ልትጠነቀቁ ይከጀላልና (መልካም እንድትሆኑ ለማድረግ)፡፡”
(አል - በቀራ፣183)
በተቀደሰው የረመዳን ወር ላይ የአምላክ በረከቶች የተትረፈረፉ ናቸው፡፡ ነብዩ መሐመድ እንዲህ ይሉናል፡-
“የረመዳን ወር ሲጀምር የገነት በሮች ይከፈታሉ፤ የሲኦል በሮች ይዘጋሉ፡፡ እንዲሁም ሰይጣኖች ይታሰራሉ።”
እንደ እስልምና ጠበብቶች ከሆነ፣ እኛ ሰዎች ደካማ ፍጡር በመሆናችን ለአለማዊ ጥቅም፣ ሐብት፣ ውድድር፣ አሉባልታዎችና ለሌሎች ፈተናዎች ቶሎ እንሸነፋለን፡፡ ነገር ግን የረመዳን ወርን በአግባቡ በመፆምና በመተግበር ተሸናፊ ስሜታችንን እስከወዲያኛው ማሸነፍ እንችላለን ይላሉ፡፡ ለመሆኑ ነብዩ ሙሐመድ በረመዳን ወቅት የነበራቸው ህይወት ምን ይመስላል? የሚከተለውን እንመልከት፡፡
ስግደትና ፍጥሪያ በረመዳን
ለሊቱ ከመንጋቱ በፊት ነብዩ ፆማቸውን ያስራሉ (ይበላሉ)፡፡ ነብዩ የምግብ እጥረት ባለበት ወቅት ቀርቶ የተትረፈረፈ ሲገኝ እንኳን የሚበሉት በጥቂቱ ነው፡፡ የጨጓራችን 1/3ኛ ለምግብ፣ 1/3ኛ ለውሐ፣ ሌላው 1/3ኛ ለአየር መዋል አለበት ብለዋል፡፡ የነብዩን የእግር ኮቴ እንደመከተላችን መጠን፣ በረመዳን የምናግበሰብሰውን ብዙ ምግብ ቀንሰን ምንም ለሌላቸው ምስኪኖች ማካፈል እንዳለብን እስልምና ይመክራል፡፡
ነብዩ የፈጅር (ጐህ ሊቀድ ሲል) ሶላት ከሰገዱ በኋላ አይተኙም፡፡ ከሶላታቸው በኋላ ዚክር (አምላክን ማስታወስ) የማድረግ ልምድ ነበራቸው፡፡ በተጨማሪም ቁርአንን ያነበንቡ ነበር፡፡ ቤተሰቦቻቸው በዚህ ተግባር ላይ አብረዋቸው እንዲሳተፉ ያደርጉም ነበር፡፡ ሙስሊሞች 30 ቀን በሚውለው የረመዳን ወር ላይ፣ 30 ጁዝ ያለውን ቁርአንን፣ በቀን አንድ ጁዝ በመቅራት እንዲያጠናቅቁ ይመከራል፡፡ ነብዩ በኢማም አህመድ ሐዲስ ውስጥ እንዲህ ብለዋል፡-
“ፆምና ቁርአን በፍርድ ቀን ከአላህ ጋር የሚያማልዱን ናቸው፡፡ ፆማችን “ጌታ ሆይ! ይህን ሰው ከምግብና ከሌሎች ፍላጐቶች አቅቤዋለሁ፡፡ እባክህን አማላጅ ልሁንለት?” በማለት አላህን ይጣራል፡፡ ያነበብነው ቁርአን ደግሞ “ይህን ሰው ማታ ከመተኛት ከልክዬዋለሁና እባክህን ላማልደው?” ይልልናል፡፡ የሁለቱም ጥያቄ በአላህ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል”
ጧት ፀሐይ ከወጣች በኋላ አማኞች ግዴታ ያልሆኑ (ሱና) ሁለት የፀሎት (ዱአ) ስግደቶችን አድርሰው ወደ እለት ስራቸው፣ ወደ ት/ቤት ወይም ወደ ቤት ስራቸው መሰማራት እንዳለባቸው የነብዩ ተግባሮች ይመሰክራሉ። ባጠቃላይ በረመዳን ወር የነበረው የነብዩ ህይወት በሶላቶች የተሞሉ መሆናቸውን ሐዲሶች ይናገራሉ፡፡
በረመዳን ወር የማፍጠር (ፆም የመስበር) ጉዳይ ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ ነብዩ ቀኑን ሙሉ ጾመው አንዳንድ ጊዜ የሚያፈጥሩት በአንድ ቴምር ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ በርሳቸው ጊዜ ምግብ እንደ ልብ ስለሌለ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ ብዙ ምግብ ሲያገኙ እንኳን ከላይ የጠቀስነውን 1/3ኛ ብቻ ነበር ወደ ሆዳቸው የሚያስገቡት፡፡ ሐኪሞች ቀኑን ሙሉ የፆመ አንጀት ብዙ ምግብ ከወሰደ የአንድ ሰው ጤና እንደሚታወክ ከነገሩን በተጨማሪ፣ ምግብ ማግበስበስ ከነብዩ የህይወት ፈለግ ጋር የሚጣረስ ነው፡፡
ፀሐይ ጠልቃ ፆማችንን ከሰበርን (ካፈጠርን) በኋላ ተራዊህ የተባለ መስጂድ ውስጥ በጋራ የሚሰገድ ሶላት አለ፡፡ ተራዊህ 23 ረከአ ያሉት የሱና (የፍቃደኝነት) ሶላት ነው፡፡ በተራዊህ ሶላት ሙስሊሞች በአንድ መስጂድ ውስጥ ከመሰባሰባቸው በላይ፣ አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ያለውን ግንኙነት በእጅጉ የሚያጠናክርበት ነው፡፡
ምፅዋት በረመዳን
ነብዩ ሙሐመድ በረመዳን ወር በጣም ለጋስ ናቸው። በቡካሪ ሐዲስ ውስጥ ኢብን አባስ እንደዘገቡት፡- “ነብዩ ካለነው ሰዎች መካከል በጣም ለጋስ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በረመዳን ወር የበለጠ ለጋስ ነበሩ…”
በተጨማሪ በቡካሪ ሐዲስ ውስጥ ያለው የነብዩ ንግግር ይህን ይመስላል፡-
“በየቀኑ ፀሐይ ስትወጣ በማንኛውም ሰው መገጣጠሚያ ወይም አጥንት (እጅና እግሩ ላይ)” ሰደቃ (ምፅዋት) አለ፡፡ ሁለት ሰዎችን በፍትሐዊነት መዳኘት ሰደቃ (ምፅዋት) ነው፡፡ አንድን ሰው በመጓጓዣ እንስሳው ላይ እንዲወጣ ማገዝ ወይም እቃውን መጫን ሰደቃ ነው። መልካም ንግግር ሰደቃ ነው፡፡ ለስግደት የምናደርገው እያንዳንዱ እርምጃ ሰደቃ ነው፡፡ ከመንገድ ላይ እንቅፋቶችን ማስወገድ ሰደቃ ነው፡፡” በሌላ ሐዲስ ላይ ደግሞ “ፈገግታ በራሱ ሰደቃ ነው” ብለዋል፡፡
ምስጋና በረመዳን
አማኞች ሁልጊዜም ቢሆን አመስጋኞች መሆን አለባቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በረመዳን ወር የምስጋናቸው መጠን ከፍ ማለት አለበት፡፡ በአል-አልባኒ ሐዲስ ውስጥ ነብዩ ይህን ተናግረዋል፡-
“በእርግጥም ምግብ የበላና ውሐ የጠጣ አንድ ሰው፣ ለአላህ የሚያቀርበው ምስጋና ከፆመኛ ሰው እኩል ምንዳ ያስገኝለታል፡፡”
አላህ በቁርአን ውስጥ እንዲህ ይለናል፡-
“ጌታችሁም፡- ብታመሰግኑ በእርግጥ እጨምርላችኋለሁ፣ ብትክዱም እቀጣችኋለሁ፤ ቅጣቴ በእርግጥ ብርቱ ነውና በማለት ባስታወቀ ጊዜ አስታውሱ።”
(ኢብራሒም፣ 7)
ምስኪኖችን፤ ቤተሰቦችንና ወዳጆችን መጠየቅ
ነብዩ በረመዳን ወር ቤተ - ዘመዶችን የመጠየቅ እና እንግዶችን ለፍጥሪያ የመጋበዝ ልምድ ነበራቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ምንም የሌላቸውን ምስኪኖች በረመዳን ወር ያበሉ ነበር፡፡ አላህ በቁርአን ውስጥ እንዲህ ይላል፡-
“ሰይጣን እንዳትለግሱ ድህነትን ያስፈራራችኋል፤ በመጥፎም ያዛችኋል፤ አላህም ከእርሱ የሆነን ምህረትና ችሮታን ይቀጥራችኋል፤ አላህም ችሮታው ሰፊ፣ አዋቂ ነወ፡፡”
(አል - በቀራህ፣ 268)
ምህረት መሻት
አላህ የነብዩን ሐጢአት ሰርዞ ጀነትን ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ ነገር ግን ነብዩ ሁልጊዜም ቢሆን የአላህን ይቅርታ ከመለመን ቦዝነው አያውቁም፡፡ በተለይ ደግሞ የበረከትና የምህረት በር ለሁሉም አማኞች በሚከፈትበት የረመዳን ወር ላይ፣ ከሌላው ጊዜ የበለጠ የአላህን ምህረት ይጠይቃሉ፡፡ አላህ በቁርአን ውስጥ እንዲህ ይላል፡-
“ከጌታችሁ ወደ ሆነችው ምህረት፤ መጠኗ እንደ ሰማይና ምድር ስፋት ወደሆነችው ገነት ተሽቀዳደሙ፤ ለነዚያ በአላህና በመልእክተኞቹ ላመኑት ተዘጋጅታለችና። ይህ የአላህ ችሮታ ነው፤ ለሚሻው ሰው ይሰጠዋል፤ አላህ የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው፡፡”
(አል - ሐዲድ፣ 21)
ረመዳን ከሌላው ወር የተለየ የሚያደርገው የውስጥ ፍላጐታችን እንዲሟላ ለአላህ ፀሎትና ልመና የምናደርስበት ወር በመሆኑ ነው፡፡ ነብዩ ሙሐመድ በኢብን ማጃህ ሐዲስ ውስጥ እንዲህ ይሉናል፡-
“የእያንዳንዱ ፆመኛ ጸሎት በእያንዳንዱ ማፍጠሪያ ሰዓት ላይመለስ ያገኛል፡፡”
ባጠቃላይ በረመዳን ወር የነበረው የነብዩ ህይወት ይህን ይመስላል፡-
ቁርአንን መቅራት (ነብዩ ማንበብና መፃፍ ስለማይችሉ በአእምሯቸው ውስጥ ያለውን ነው የሚያነበንቡት)
ለሶላቶች ትኩረት መስጠት
ተጨማሪ የሱና ሶላቶችን መስገድ
የለሊት ሶላቶችን ማድረስ (ቂያሙል ለይል)
ምፅዋቶችን መስጠት
ከቤተሰብ ጋር ማሳለፍ
ምስኪኖችንና እንግዶችን ቤት መጋበዝ (ማስፈጠር)
ከአላህ ምህረት መሻት (መጠየቅ)
ዱአ (ፀሎት) ማድረግ
በመጨረሻ በነብዩ የአጐት ልጅ፣ አሊ ኢብን ጣሊብ ንግግር እንሰነባበት፡፡ አሊ በአል - ባይሐቂ ሐዲስ ውስጥ ነብዩን እንዲህ ጠየኳቸው ይለናል፡-
“የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! በረመዳን ወር ምርጥ የተባለው ተግባር ምንድነው?” ነብዩ እንዲህ መለሱ፡- “አንተ አቡ ሐሰን ሆይ! በዚህ ወር ምርጥ የተባለው አላህ ከከለከለው ነገር መራቅ ነው፡፡”
በዚህ ቅዱስ ወር የአላህ ሰላም፣ በረከት እና ፍቅር በሐገራችን ላይ ይውረድ! አሚን፡፡

Read 14498 times