Saturday, 04 July 2015 11:36

የሜዲትራኒያን ባህር ስደተኞች ቁጥር ክብረ ወሰን አስመዝግቧል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ባለፉት ስድስት ወራት 137
ሺህ ስደተኞች አውሮፓ ገብተዋል
- በባህር ጉዞ የሞቱ ስደተኞች
ቁጥር ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሯል

   ባለፉት ስድስት ወራት አፍሪካን ጨምሮ ከተለያዩ የአለማችን አገራት በመነሳት የሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ የተጓዙ ስደተኞች ቁጥር በታሪክ ታይቶ በማይታወቅበት ደረጃ ላይ መድረሱንና በስደት ጉዞ ላይ ሳሉ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥርም ከሶስት እጥፍ በላይ መጨመሩን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ባለፉት ስድስት ወራት የሚዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ ግሪክ፣ ጣሊያን፣ ማልታ እና ስፔን የገቡ ስደተኞች ቁጥር 137 ሺህ የደረሰ ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅና አዲስ ክብረወሰን ያስመዘገበ ነው፡፡
አብዛኞቹ ስደተኞች ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት ያለባቸው አገራት ዜጎች መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በተጠቀሰው ጊዜ ባህር አቋርጠው ወደ ጣሊያንና ግሪክ ከገቡት ስደተኞች መካከል አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት በጦርነት የምትታመሰዋ ሶርያ ዜጎች እንደሆኑ ገልጧል፡፡ ከሶርያ በመቀጠል የበርካታ ስደተኞች መነሻ የሆኑት አገራት፣ በግጭት ውስጥ ያለችው አፍጋኒስታንና ጨቋኝ ስርዓት የገነነባት ኤርትራ ናቸው ያለው ሪፖርቱ፣ ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ በርካታ ስደተኞች መነሻ የሆኑት ሌሎች አገራትም ሶማሊያ፣ ናይጀሪያ፣ ኢራቅና ሱዳን መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ሃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስም እንደገለጹት፣ አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ አውሮፓ የሚጓዙት የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ሳይሆን በአገራቸው ያለውን ግጭት፣ ጦርነትና ስቃይ ለመሸሽና ህይወታቸውን ለማዳን በማሰብ ነው ብለዋል፡፡ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ወደ አውሮፓ የገቡ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ቁጥር 75 ሺህ እንደነበር ያስታወሰው የተመድ ሪፖርት፣ ይህ ቁጥር ባለፉት ስድስት ወራት የ83 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 137 ሺህ ደርሷል ብሏል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥር፣ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሯል ያለው የተመድ ሪፖርት፣ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 1ሺህ 867 ስደተኞች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት ጣሊያን 67 ሺህ 500፣ ግሪክ 68 ሺህ ስደተኞችን እንደተቀበሉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የስደተኞቹ ቁጥር  በቀጣዮቹ ስድስት ወራትም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡


Read 1627 times