Saturday, 04 July 2015 10:43

ኢትዮጵያ በጥራጥሬ ምርቶች ላይ ብታተኩር የምሥራቅ አፍሪካ መዳረሻ ትሆናለች ተባለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ሰሞኑን በሂልተን ሆቴል በተካሄደ ወርክሾፕ ላይ የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ እኛ እንደማባያ (ወጥ) የምንጠቀማቸው ጥራጥሬዎች በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ተፈላጊነታቸውና ዋጋቸው መጨመሩን አመለከተ። ኢትዮጵያ ለእነዚህ ምርቶች ተስማሚ አየር ንብረትና አመቺ ሁኔታ ስላላት፣ በብዛትና በጥራት እያመረተች ለዓለም ገበያ ብታቀርብ፣አሁን ከምታገኘው ከሁለትና ሦስት እጥፍ በላይ ገቢ እንደምታገኝ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡  
ወርክሾፑን ያዘጋጀው በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል Supporting Indian Trade and Investment for Africa (SITA) ከ2014 – 2020 የህንድና የአምስት የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ኢንቬስትመንት፣ ኤክስፖርት ስትራቴጂና የተወዳዳሪነት አቅም በማጎልበት ለመደገፍ የተቋቋመ ፕሮጀክት ተቋም ነው፡፡
በእንግሊዝ ህዝብና በሰሜን አየርላንድ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ሲታ ፕሮጀክት ዓላማ፤ እንደ ህንድ ዓይነት በመበልፀግ ላይ ያሉ አገራት ዓለም አቀፍ የዕድገት ሰንሰለት  ወደ ምስራቅ አፍሪካ አገሮ እየተስፋፋ ስለሆነ በህንድ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳና ታንዛኒያ----ንግድና በኢንቨስትመንት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ድህነት ቅነሳ የሚደረገውን እንቅስቃሴ መደገፍ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ፣ በአሁኑ ወቅት ህንድ የደቡብ ደቡብ ነፃ የንግድ ግንኙነት ቀጣና በሰጠችው ነፃ የታሪፍ ተጠቃሚነት ዕድል፣ በማደግ ላይ ያሉ ከአምስቱ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ወደ ህንድ የሚገቡ ምርቶች 98 በመቶ ከቀረጥ ነፃ የታሪፍ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በወጪ በጥራጥሬ ንግድ ላይ ለተሰማሩ የኢትዮጵያ ድርጅቶች፣ ለመንግሥት ኃላፊዎችና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ለሁለት ቀን የተዘጋጀውን ወርክ ሾፕ የመሩት በተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከልና የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንዲሁም የንግድ ድጋፍ ማጠናከሪያ ተቋም ሲታ አማካሪ ሚ/ር አማን ጎል ኃላፊነታቸው፣ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ንግድና ኢንቨስትመንት ለማቀላጠፍ በሦስት ደረጃ ላሉት ተሳታፊዎች ስልጠና እንደሰጡ ጠቅሰው፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ለጥራጥሬ የንግድ ዘርፍ አመቺና ተስማሚ የሆነ ፖሊሲ እንዲቀርፁ፣ በአገር ውስጥና በውጭ ንግድ የተሰማሩ ድርጅቶች የአቅም ግንባታና በጥራጥሬ ንግድ ለመሰማራት ፍላጎቱ እያላቸው አሰራሩን ለማያውቁ ግለሰቦች ትምህርት መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለጥራጥሬ ምርት አመቺ የሆነ እምቅ ሀብት፣ እውቀትና ልምድ ቢኖራትም ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ በዘርፉ በውጭ ንግድ ተሰማርታ ማግኘት የሚገባትን ጥቅምና ገቢ አላገኘችም ያሉት ሚ/ር ጎል፣ ህንድና ሌሎች ገበያዎች የእነዚህ የእርሻ ውጤቶች ፈላጊ ናቸው፡፡ በውጭ ንግድ የተሰማሩ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ገበያው (በአሜሪካና በአውሮፓ) በሚፈለገው የጥራት ደረጃና መጠን ለማቅረብ የአቅም፣ የቴክኖሎጂ፣ የእውቀት ውሱንነት አለባቸው፡፡ የህንድ ፍላጎት፣ ለጥራጥሬ የወጪ ንግድ አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎችና እውቀት ከአሜሪካና ከአውሮፓ አምጥቶ፣ ኢትዮጵያ እንድታመርትበትና በአገሪቷ በጥራጥሬ ምርት ዘርፍ ኢንቬስት ማድረግ ነው። በርካታ የህንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ወርክሾፕም ሁለት የህንድ ኢንቬስተሮች ተገኝተዋል፤ በማለት የሲታን አስፈላጊነት አብራርተዋል፡፡
ህንድ የምትፈልገው የምርት ብዛት ብቻ ሳይሆን ዓይነቱ በዝቶና እሴት ተጨምሮበት ኤክስፖርት እንዲደረግ ነው፡፡ በቀጣይ 5 ዓመት የተሻለ ነገር እንደምናይ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጥራጥሬ ምርት ለዘመናት የካበተ ልምድና እውቀት አላት፡፡ አሁንም‘ኮ እያመረተች ነው፡፡ ነገር ግን ከሚመረተው ውስጥ ከ70 እስከ 75 በመቶ ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚውል ተገንዝቤአለሁ፡፡ መንግስትም ምርቱ ለውጭ ገበያ ቢቀርብ ጠቃሚነቱ የጎላ መሆኑን አምኗል። አሁን የምናደርገው ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ያሟላ ምርት ለማግኘት፣ በእርሻ ወቅትና ከእርሻ በፊት በዝግጅት ወቅት መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ፣ ከምርት በኋላ ምርቱ ለገበያ እስኪቀርብ ድረስ የሚፈጠረውን ብክነት፣ ዋጋ እንዲንር የሚያደርጉ አቀባባዮች የሚቀነሱበትን መንገድ መፈለግ፣ አምራቾችና  ነጋዴው ፊት ለፊት ተገናኝተው የሚገበያዩበትን ዘዴ መፍጠር ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች በዓለም በጣም ምርጥ ከተባሉ ዝርያዎች አንዱ ስለሆኑ የህንድ ነጋዴዎች የኢትዮጵያን ምርት ለመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አማካሪው ተናግረዋል፡፡ አንድ ቅሬታ ግን አላቸው፡፡ በህንድ ገበያ ሽንብራ፣ ምስር፣ የእርግብ አተር ማሾ ተፈላጊ የሆኑት ጥራጥሬ ምርቶች ሲሆኑ ህንዶች የሚፈልጉት የሽንብራ መጠን ትልልቅ ሲሆን የኢትዮጵያ ምርት ግን ትንንሽ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግስት አካላት ጋር ተናጋግረናል፡፡ መንግስት በጣም ተባባሪ ከመሆኑም በላይ በዚህ ወርክሾፕም እየተሳተፈ ስለሆነ ችግሩ የሚወገድበት መንገድ እንደሚቀየስ እምነቴ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡
ሚ/ር አማን በጥራጥሬ ምርት የሚታዩ ችግሮችንም ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለዓለም ገበያ ከሚቀርቡ 12 ዓይነት ምርቶች ውስጥ ከፍተኛውን ደረጃ፣ ከሶስት እጅ ሁለቱን ወይም 2/3ኛ የያዙት ሶስት ምርቶች፡- ባቄላ፣ ሽንብራና አተር ናቸው፡፡ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በዓይነት እንዲበዙ ይፈለጋል፡፡ የምርት ጥራትና ብዛት ማነስ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ የትራንስፖርት፣ የፓኬጂንግ ጉድለት፣ የአመራረት ችግር፣ መንግስትና የግሉ ዘርፍ ተቀናጅቶ ያለመስራት፣ አዳዲስ ገበያዎችን ያለመፍጠርና ሌሎች በርካታ ችግሮች ተጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ የተመሰረተው በእርሻ ውጤቶች ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ቡና 28.02 በመቶ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ቀዳሚ ነው፡፡ የቅባት እህሎች 14.69 በመቶ፣ ጥራጥሬ ደግሞ 6.33 በመቶ ድርሻ በመያዝ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡
ቻይና፣ ሶማሊያ፣ ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኔዘርላንድና አሜሪካ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ምርት ገዢ አገሮች ሲሆኑ ወደ ጀርመን፣ የተባበሩት አረብ ኢመሬትስ፣ ሱዳን፣ እስራኤልና ኢጣሊያ ለማስፋፋት ዕቅድ ተይዟል። በፈጣን እድገት ላይ ካሉ አገሮች የኢትዮጵያን ምርት የሚፈልጉት ሰርቢያ፣ ሊቢያ፣ ቪየትናም፣ ጆርጅያ፣ ኩዌትና ጊኒ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትና አግሪ ቢዝነስ ዘርፍ ለጥራጥሬ ምርት አመቺ ስለሆነ በጥሩ የሎጅስቲክስና የማከፋፈያ አውታሮች ቢታገዝ አገሪቱ የምስራቅ አፍሪካ የጥራጥሬ ማዕከል መሆን ትችላለች ተብሏል፡፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ጥራጥሬ አስተማማኝና የማያቋርጥ መሆን እንዳለበት የተጠቀሰ ሲሆን ከጎረቤት ጥራጥሬ አምራች አገሮችም ጋር መወዳደር እንዳለባት ተነግሯል፡፡   

Read 2111 times