Saturday, 04 July 2015 10:34

የረመዳንን ክብር ያጐደፈው የአይሲስ አረመኔያዊ ተግባር

Written by  ኑርሁሴን
Rate this item
(4 votes)

ረመዳን በሙስሊም አማኞች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የተከበረ የፆም ወር ነው፡፡ በረመዳን ሁሉም አማኝ ከምግብ፣ ከመጠጥና ከሌሎች ነገሮች ራሱን አቅቦ መንፈሳዊ አለሙን የሚያንፀባርቅበት ቅዱስ ወር ነው፡፡
ለአምላክ መፀለይ እና በፅኑ መስገድ፣ ለሌሎች ሰዎች መልካም ስነ - ምግባሮችን ማሳየት፣ ምፅዋቶችን መለገስ ከረመዳን መገለጫዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። በአዘቦት ቀናት የማይሰግዱ ሰዎች እንኳን በረመዳን የአምላክ በረከቶች እንዲያመልጧቸው አይፈልጉም፡፡
የረመዳን ወር ህዝቦች ክፉና በጎውን እንዲለዩ አምላክ መመሪያ ያወረደበት ነው፣ ቁርአንን፡፡ ሰዎች ከአምላካቸው ጋር ያላቸውን ዝምድና እንዲያጠናክሩ ቁርአንን ሲልክ ፈጣሪ የመረጠው የረመዳንን ወር ነው፡፡
እንደ ነብዩ መሐመድ ምክር ከሆነ፣ በረመዳን ፆም ወቅት ሰዎች መጮህ ወይም ለሰደባቸው ሰው መልስ መስጠት የለባቸውም፡፡ ከዚህ ይልቅ “ፆም ይዤያለሁ፤ ፆም ይዤያለሁ” በማለት ከሁከት መራቅ አለባቸው፡፡
የረመዳን ወር ዋንኛ ዓላማ ሰዎች ቀኑን ሙሉ ከምግብ ተከልክለው፣ ስጋቸውን በማዳከም፣ ከአምላክ ጋር ያላቸውን መንፈሳዊ ግንኙነት እንዲያጠናክሩ ነው፡፡ የረመዳን ትሩፋቶችን ተግባራዊ በማድረግ ሰዎች ውስጣዊ ማንነታቸውን መፈተሽ ብቻ ሳይሆን የልቦናቸውን መንፈሳዊነት ማሳደግ አለባቸው፡፡ በፆም ውስጣዊ ተፈጥሯችንን ማዳመጥ ካልቻልን የረመዳን ወር ክብርነት ትርጉሙን ያጣል፡፡ ነብዩም ያስጠነቀቁት ይሄንኑ ነው፡- “ብዙ ሰዎች ከመፆም ምንም ነገር አያተርፉም፤ መራብና መጠማትን ቢሆን እንጂ፡፡” የዘንድሮው የረመዳን ወር እንደጀመረ ሙሐመድ አድ አድናኒ የተባለው የአይሲስ ቃል አቀባይ ከላይ የጠቀስነውን መንፈሳዊነት የሚቃረን አዋጅ ተናገረ፡- “እናንተ ሙጃሒዲኖች ሆይ! በረመዳን ጦርነት በማድረግ ለኢ-አማኞች ወሩን አስቀያሚ አድርጉባቸው፡፡” ይሔው የአይሲስ ቃል - አቀባይ “ማንኛውም አምልኮ ከ(ወታደራዊ) ጂሐድ አይበልጥም” የሚል መግለጫ ከሰጠ በኋላ በረመዳን ሁለተኛው ጁምአ ላይ በኩዌት፣ ቱኒዚያና ፈረንሳይ ውስጥ አሰቃቂ ጥቃቶች ተፈፀሙ፡፡ (የፈረንሳዩን እስከ አሁን ድረስ ኃላፊነቱን ባይወስዱም) ይህ አረመኔ ቡድን፣ በሶሪያ ኮባኒ ውስጥ 145 ንፁሐንን መግደሉን ስንሰማ፣ አይሲስ በቅዱሱ የረመዳን ወር እንኳን የሚራራ ልብ እንደሌለው እንገነዘባለን፡፡ አይሲስ እስልምናን የማይወክል ብቻ ሳይሆን የእስልምናን መለኮታዊ አላማ አፈር ድሜ እያስጋጠ የሚገኝ የጋጠ ወጥ ቡድን ነው፡፡
ፆማችንን የሚመለከተውና የሚፈርደው አንዱ አምላክ ብቻ ነው፡፡ አይሲስ ግን በሳማራ ውስጥ ተደብቃችሁ በልታችኋል ያላቸውን ሁለት ታዳጊዎች፣ እጃቸውን ጠፍሮ አሰቃቂ ግርፋት አድርሶባቸዋል፡፡ በዚህ የረመዳን ወር ሙስሊሞች ሁለ ነገራቸውን ለአምላክ አስገዝተው ባሉበት ወቅት አይሲስ ግን የአማኞች ፀጥታን በማደፍረስ እውነትም የረመዳንን ወር አስቀያሚ አድርጎባቸዋል። አይሲስ እየፈፀመ ባለው ክፉ ተግባር (በረመዳን ወር) የተነሳ ብዙ የእስልምና አዋቂዎችን በቡድኑ እስላማዊነት ላይ ጥርጣሬ እንዲገባቸው አድርጓቸዋል፡፡ አል-ቃኢዳና ታሊባን እንኳን በረመዳን ወር የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ያወግዛሉ፡፡ አይሲስ ግን የረመዳን ፀጥታ መደፍረስ ሳያሳስበው እያደረሰ ያለው እልቂት ብዙዎቹን የእስልምና አለማት ግራ አጋብቷል፡፡ አንድ ነገር ማወቅ ያለብን ከፍጥሪያ በኋላ ያለው የረመዳ ምሽት ለሙስሊሞች የክብረ - በዓል ዓይነት መንፈስ ያለው ነው፡፡ ጎዳናዎች ፆመው በዋሉ አማኞች ይሞላል። ከሽብርተኞች ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ ወይም ተባባሪ ሰዎች እንኳን ረመዳን ምሽትን በሰላማዊ መንፈስ ነው የሚያሳልፉት፡፡ አይሲስ ግን በዚህ የረመዳን ወር በሚፆሙ ሙስሊሞች ላይ የጭካኔ ተግባር ፈፅሞባቸዋል። የአይሲስን ተግባር የሚደግፉ አንዳንድ ሰዎች እንኳን በጿሚ ሙስሊሞች ላይ በደረሰው አሳዛኝ ነገር በጣሙን ተቆጭተዋል፡፡
በዲትሮይት ዋይን ስቴት ዩኒቨርስቲ ውስጥ የእስልምና ታሪክ ተመራማሪ የሆነው ሰኢድ ሐሰን በሰነዘረው አስተያየት፡- “በጁምአ ቀን በኩዌት መስጂድ ውስጥ የደረሰው ጥቃት በጣም የሚዘገንን ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ምንም ውጊያ ውስጥ የሌሉ ንፁሐን መሆናቸውና በረመዳን  ወር ላይ መፈፀሙ ድርጊቱን የማይታሰብ ያደርገዋል፡፡”
አይሲስ አሁንም እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው፡፡ በዋናነት ያነገበው የእስልምናን ሸሪአ በአለም ላይ ማስፈን የሚል አላማ ነው፡፡ ነገር ግን ጥንታዊ የእስልምና ሐገሮችንና ቅርሶችን እያወደመ መሆኑን ስንመለከት “የሸሪአ ህግ ማስፈኑን” ተወው እንዴ የሚያስብል ነው፡፡
በእርግጥ በእስልምና የኋላ ታሪክ ውስጥ በረመዳን ወር ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ ለምሳሌ በ624 ዓመት የበድር ጦርነት በረመዳን ወር በመነሳቱ ነብዩ ሙሐመድ ይህን ጦርነት መርተዋል፡፡ የጦርነቱ ድል የሙስሊሞች ነበር፡፡ በረመዳን ወር ሌሎች ጦርነቶችም መካሄዳቸው በታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጦርነቶች የህልውና ጦርነቶች ነበሩ፡፡ ሙስሊሞች በጣኦታውያን ላለመደምሰስ ያደረጉት የሞት-ሽረት ጦርነቶች ናቸው፡፡
አይሲስ ያሳየው ፀብ -ጫሪነትና በሌሎች (ባልታጠቁ ንፁሐን) ላይ የሰነዘረው ጥቃት ግን ከላይ ከጠቀስነው ጦርነቶች በእጅጉ ይለያል፡፡ አይሲስና ተከታዮቹ ስለነብዩ ታሪክና ስለቁርአን ማወቃቸው አጠራጣሪ የሆነውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
አይሲስ እንደሚለው፤ ረመዳን የግድያ ማስፈፀሚያ ወር ነው፡፡ መንፈሳዊ ጥንካሬ፣ ደስታ፣ ለጋስነት እና የአላህ በረከት የተትረፈረፈበት የረመዳን ወር እድሜ ለዚህ አረመኔ ቡድን ክብሩን አጥቷል፡፡ እስልምና ለአእምሯችን እውነታን የምንመግብበት፣ ልቦናችንን በአምልኮ ስርአቶች የምናረካበት ሰላማዊ ሐይማኖት ነው፡፡ የረመዳን ወርን የጭካኔ ማስፈፀሚያ ማድረግ ስህተት ብቻ ሳይሆን የማይታሰብም ጭምር ነው፡፡
ሐይማኖት የእምነት ወይም የስነ-ስርዓት መገለጫ ብቻ አይደለም፡፡ የጠራ ማህበረሰብ መፍጠሪያና እውቀቶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ የምናስተላልፍበት ውብ ነገር ነው፡፡ የአንድ ሐይማኖት መንፈሳዊነት፣ ፍልስፍና ወይም እውነታ ከብዙ ሺ ዓመት በፊት ሲወርድ ሲዋረድ ለትውልድ እየተላለፈ የሚመጣ እንጂ ዛሬውኑ የምንፈጥረው አስተምህሮት አይደለም፡፡ በሐይማኖት ውስጥ የዚህ ዓይነት ልማዶችን መገንዘብ አማኞች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማንም አይነግራቸውም፤ ራሳቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ወይም ደግሞ ይህን ለምን ፈፀምኩት? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አያቅታቸውም፡፡
የአይሲስን አካሄድ በደንብ ካጤነው ግን ለትውልድ እየተላለፈ ከመጣው ትሩፋት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው እንረዳለን፡፡ የኋላ ትሩፋቶችን ከእውነት ጋር አጥብቆ ያልያዘ ትውልድ ደግሞ እጣ-ፈንታው መጥፋት ብቻ ነው፡፡ መሰረት የሌለው ግንብ ማለት ነው፡፡ እኛ ግን አሁንም ቢሆን ይህ ግንብ እስኪፈርስ ድረስ ደመ-ከልብ ለሆኑትና ለሚሆኑት ንፁሐን ሰዎች ከልብ ማዘናችንንና ፀሎት ማድረሳችንን አናቆምም፡፡  

Read 2557 times