Saturday, 04 July 2015 10:28

ዘመናዊነት የማይተካቸው ማህበራዊ እሴቶች

Written by  ሂሮዬ ሺማቡኩሮ
Rate this item
(3 votes)

     ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ከ13 ዓመት በፊት ነበር - በሙያ መምህርነት ለማገልገል። ተማሪዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዩኝ ጃፓናዊ መሆኔ ትኩረታቸውን ሳይስበው አልቀረም፡፡ በዚህም የተነሳ ስለራሴና ስለጃፓን የማይጠይቁኝ ነገር አልነበረም። የሚገርማችሁ ያን ጊዜ በቦሌ መንገድ ላይ እንኳን ብዙ የውጭ ዜጐች አይታዩም ነበር፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎትና ሳተላይት ቲቪ አልነበረም፡፡ እናም ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው ለተማሪዎቼ ስለ ጃፓን በማውራት ነበር፡፡  
በኋላማ የጃፓን ባህልን የማስተምርበት ክፍለ ጊዜ (Cultural class) ሁሉ ጀምሬ ነበር - ስለጃፓን የበለጠ ለማወቅ ጉጉት ያላቸውን ሰዎች ፍላጐት ለማርካት፡፡ ምክንያቱ ባይገባኝም  ተማሪዎቼ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ሰዎች እኔን ከሌላ ፕላኔት እንደመጣሁ አድርገው የመመልከት አዝማምያ ይስተዋልባቸው ነበር፡፡ ብዙዎቹ የምለውን ነገር ለመስማት ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው፡፡ አንዳንዴ በማደርጋቸው ነገሮችም ጭምር ይገረሙ ነበር። ምናልባት ከኢትዮጵያ ባህልና ወግ የተለየ ሆኖባቸው ሊሆን ይችላል፡፡   
ያን ጊዜ በአዲስ አበባ አብዛኛው ሰው የመስመር ስልክ ተጠቃሚ ሲሆን ሞባይል ስልክ እንደብርቅ ነበር የሚታየው፡፡ ሰዎች በህዝብ ስልክ ለመደወል ወረፋ መያዝ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ያኔ መዲናዋም እንዲህ በትራፊክ አልተጨናነቀችም፡፡ ረዣዥም ህንፃዎችም በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡
ሁሌ ትዝ የሚለኝ ፈረንጅ ጓደኞቼ በሳምንቱ የእረፍት ቀናት (ቅዳሜና እሁድ) የምንዝናናበት አጣን እያሉ ያማርሩ እንደነበር ነው፡፡ ለነገሩ እውነታቸውን ነበር፡፡ ያን ጊዜ እቃ ለመሸመት እንኳን የሚጐበኙ ትላልቅና ዘመናዊ የገበያ አዳራሾች የሉም ነበር፡፡ የሚያወላዱ የመዝናኛ ሥፍራዎችም አልነበሩም! የአሁኖቹ እነ ደምበል፣ ፍሬንድሺፕ፣ ኤድናሞል… መች ነበሩ! (ኤድናሞል የተሰራበት ሥፍራ ባዶ ሜዳ ነበር)
ያኔ…አዳዲስ የወጡ የሆሊውድ ፊልሞችን መመልከቻ ሲኒማ ቤት አልነበረም፡፡ አምባሳደር ደግሞ ምናልባት የህንድ ፊልሞችን ቢያሳይ ነው፡፡ እንደነ ቦስተን ያሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የውበት ሳሎኖች፣ ሳውናዎችና ማሳጅ ቤቶችም አልነበሩም … እነዚያ ፈረንጅ ጓደኞቼ ታዲያ ፀጉራችንን የት እንሰራ? የት ማሳጅና ሳውና እናድርግ? ምናምን እያሉ ሲነጫነጩ ትዝ ይለኛል፡፡
ያኔ ካልዲስንና ቤሉስን የመሳሰሉ ምርጥና ዘመናዊ ካፌዎችን አስሶ ማግኘት ዘበት ነበር፡፡  ብዙዎቹ ደረጃቸው ዝቅ ያለ ተራ ካፌዎች ሲሆኑ በአብዛኛው የድለላ ሰራተኞችና ጎልማሶች አንድ ስኒ ቡና ይዘው ለሰዓታት የሚቀመጡባቸው ቦታዎች ነበሩ፡፡ በዚህ የተነሳ ማኪያቶ እየጠጡ ዘና ማለት እንኳን መከራ ነው በተለይ ለፈረንጅ ጓደኞቼ፡፡
ለእኔ ግን ሁኔታው ፈጽሞ የተለየ ነበር፡፡ ባይገርማችሁ… የሳምንቱ የዕረፍት ቀናት ለእኔ አስደሳችና አዝናኝ ነበሩ፡፡ ለምን መሰላችሁ? ኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ ቤት ተጋብዤ ስለምሄድ፣ ከወዳጅ ዘመዶቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ጋር ምሳ እንበላና ቡና ተፈልቶ እየጠጣን እናወጋለን፡፡ ቡናው ሲያከትምም በወቅቱ የነበረውን ብቸኛ የቲቪ ቻናል (ኢቲቪን) ለረዥም ሰዓት አብረን እንመለከታለን፡፡ አንዳንዶቹ የቲቪ ፕሮግራሞች አሰልቺ ቢሆኑም ዝም ብለን እናያቸው ነበር፡፡ በእውነቱ ያ ጊዜ ለእኔ ልዩ ትዝታን ጥሎብኝ አልፏል፡፡
ከ13 ዓመት በፊት ጃፓንን ከመሰለ የሰለጠነ ዓለም ለመጣ ሰው፣ አዲስ አበባ በጊዜ ሃዲድ የኋሊት ተንሻትታ የጥንት ዘመን ላይ የቆመች ነበር የምትመስለው፡፡ መዲናዋ ከብዙ ነገሮች አንፃር የድሮ ጊዜ ላይ ነበረች ማለት ይቻላል። ለእኔ ግን ግሩም ትውስታዎችን በውስጤ ማስቀረት የቻልኩበት ወቅት ነበር፡፡ ቡና እየጠጡ ማውጋት… ከኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ጋር መብራት ጠፍቶ በጨለማ የበቆሎ ጥብስ መብላት፣ መንገድ ላይ የወደቀ ሰው ለመርዳት መረባረብ የመጐራረስና እንብላ የማለት ባህል፣ እርስበርስ ለመረዳዳት መትጋት …ይሄ ቀላል ግን በጃፓን እምብዛም የማይገኝ የበለፀገ የማህበራዊ ህይወት ተሞክሮ ነው፡፡
በአገሬ ጃፓን ሰዎች ስለሌላው ሰው ብዙም ደንታ የላቸውም፡፡ የሰዎች ግንኙነትም ቢሆን ግልብ ነው። ሁሉም በግል ህይወቱ ምሕዋር ነው የሚሽከረከረው።  በዚህ የተነሳ በአዲስ አበባ ያስተዋልኩት ድንቅ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ባህል እንዲሁም ግሩም ማህበራዊ ህይወት በውስጤ ታትሞ ቀርቷል፡፡
ይሄ ሁሉ ከ13 ዓመት በፊት የነበረ ታሪክ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ነገሮች እንዴት በፍጥነት እንደተለወጡ ለእናንተ አልነገራችሁም፡፡ አዲስ አበባ በእጅጉ ተጨናንቃለች - በሰውና በተሽከርካሪ፡፡ በእርግጥ ሰዎች  በኮንዶሚኒየም ቤቶች ውስጥ መኖር ጀምረዋል፡፡ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ በርገር ቤቶችና ማሳጅ ቤቶች በየቦታው ተከፍተዋል፡፡
አሁን የሞባይል ስልክ ለአዲስ አበቤ ብርቁ አይደለም፡፡ በህዝብ ስልክ ለመደወል ወረፋ መያዝም ቀርቷል፡፡ የቤት ሰራተኛና ጥበቃ ሳይቀሩ የሞባይል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደ ድሮው አንድ ቻናል ሳይሆን በርከት ብሏል፡፡ በዚያ ላይ የሳተላይት ቲቪ እንደልብ ሆኗል፡፡ እናም ሰዎች የምዕራብ አገራትን ፊልሞች እያማረጡ ይኮመኩማሉ፡፡ ምን ይሄ ብቻ… የኮርያና የቱርክ ተከታታይ የቲቪ ድራማዎችን ከሳተላይት የቲቪ ቻናሎች ላይ አድነው የሚመለከቱ ወጣቶች አሉ፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢንተርኔት መስፋፋት በሰዎች ህይወት ላይ ጉልህ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለመረጃ ቅርብ ሆነዋል፡፡ በፌስቡክ አማካኝነት ከጃፓናውያን ጋር ጓደኝነት የመሰረቱ ጥቂት አይደሉም፡፡ አሁን ሰዎች ስለጃፓን ማወቅ የሚፈልጉት ነገር ቢኖር እንደድሮው እኔን መጠየቅ አያስፈልጋቸውም። ከ Wikipedia ላይ ያሻቸውን መረጃ ያለ ስስት የማግኘት ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
ከ13 ዓመት በፊት ሴቶች ለብቻቸው እንኳንስ ባርና የምሽት ክለቦችን ሊያዘወትሩ ቀርቶ ካፌና ሬስቶራንት የሚገቡትም ከስንት አንድ ነበሩ፡፡ በተለይ በምሽት ሴት መጠጥ ቤት ከታየች ሌላ ስም ይሰጣት ነበር፡፡ ይሄ ግን አሁን ተለውጧል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ሴቶች የወንድ አጃቢ ሳያስከትሉ ወደ ምሽት ክለቦች ጎራ ብለው ሲዝናኑና ሲደንሱ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡  በአብዛኛው የፈረንጆች መናኸሪያ የነበሩት እንደነሸራተን ያሉ ውድ ሆቴሎች አሁን በኢትዮጵያውያን ደንበኞች መሞላት ጀምረዋል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያውያን የቢዝነስ ሰዎች በእጅጉ በስራ ከመጠመዳቸው የተነሳ ሰው ሲቀጥሩ እንደ ድሮው በደፈናው “ነገ ብቅ በይ” ማለት ትተዋል፡፡ የምትመጡበትን እቅጯን ሰዓት ካልተናገራችሁ እሺ ብለው ቀጠሮ አይሰጧችሁም፡፡ አሁን የቢዝነስ ሰዎች የጊዜ  ጥቅም እየገባቸው መጥቷል፡፡  
በአዲስ አበባ ባለፉት 13 ዓመታት የተለወጡትን ነገሮች ዘርዝሬ የምጨርሰው አይመስለኝም፡፡ ከፈጣኑ ለውጥ ጋር በርካታ ነገሮች አብረው  መጥተዋል፡፡ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በርካታ መረጃዎች ማግኘት ችለዋል፡፡ ብዙ የሚሰሩ ቢዝነሶች… ብዙ የሚገዙ ነገሮች ብዙ የሚጐበኙ ቦታዎች …ብዙ ማህበራዊ ግዴታዎች… ብዙ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች… ተፈጥረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አዲስ አበቤ ቀን ተሌት ባተሌ ሆኗል፡፡ ማታ ተሰባስቦ ቡና የሚጠጣበት ሰዓት እንኳን እየጠፋ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የአዲስ አበባ ሱፐር ማርኬቶች እንደ አገሬ ጃፓን ጣጣውን የጨረሰ የቡና ዱቄት (Instant Coffee) ማቅረብ ሁሉ ጀምረዋል፡፡ ያ የምወደው ባህላዊ የቡና አፈላል ሥርዓት ቀስ እያለ እንዳይጠፋ እሰጋለሁ። ለነገሩ አሁንም ጐረቤት ቡና መጠራራት በእጅጉ ቀንሷል። እንደምዕራብ አገራት ከጐናቸው ያለውን ነዋሪ (ጐረቤት) ማንነት የማያውቁ አዲስ አበቤዎች በርክተዋል፡፡ ህይወት ሩጫ ሆናለች፡፡ መሮጥ …መሮጥ… መሮጥ… ትልቅ ትንሹ ባተሌ ሆኗል፡፡
ወላጆች እንዲህ በኑሮና በሥራ ተወጥረው ሲዋከቡ ህፃናትን የሚያስታውሳቸው ይጠፋል፡፡ ብዙ ህፃናት በሞባይል ጌም ወይም በቲቪ ጌም ተጠምደው ነው የሚውሉት፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ወደ ቲቪ ላይ አሊያም የአኒሜሽን ፊልሞች ላይ አፍጥጠው ይውላሉ፡፡ እኒህ ጥሩ ምልክቶች አይመስሉኝም፡፡ የኢትዮጵያውያን የዳበረ ማህበራዊ አኗኗርና የመረዳዳት በጐ ባህል ፈጽሞ በዕድገትና ሥልጣኔ መደፍጠጥ የለበትም፡፡ በተገኘችው ጊዜ ሁሉ ቡና ተሰባስቦ መጠጣትና ማውጋት፣ የተቸገረን መርዳት፣ ልጆች ታላላቆቻቸውን እንዲያከብሩ ማስተማር አስፈላጊ ነው፡፡
ዘመናዊነት የማይተካቸው እሴቶች እንዳሉ ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ ለዕድገት ስትተጉ ባህላችሁንም አትዘንጉ!!


Read 2423 times