Saturday, 27 June 2015 09:38

ሐያሲ አብደላ እዝራ “ያልታየው ተውኔት”ን እንዴት አየው?

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(3 votes)

ወጣት ገጣምያን ሰቆቃ ላይ ማተኮራቸው አሳስቦታል

   ከአንድ ሳምንት በፊት ረቡዕ ምሽት ነበር ገጣሚ ደምሰው መርሻ “ያልታየው ተውኔት” የተሰኘውን በሙዚቃ የተቀናበረ የግጥም ሲዲ በሒልተን ሆቴል ያስመረቀው፡፡ በግጥም ሲዲዎች ምረቃ ላይ ባልተለመደ መልኩ ሥራዎቹን በአንጋፋው የሥነ ፅሁፍ ሐያሲ በአብደላ እዝራም አስተንትኗል። ሃያሲው ወደ ትንተናው ከመግባቱ በፊትም የሚከተለውን መንደርደርያ አስቀድሟል፡፡  
*   *   *
ደምሰው መርሻን የመተዋወቅ ዕድል ያገኘሁት በጓደኛዬ በአለማየሁ ገላጋይ በኩል የዛሬ ሁለት ዓመት ነበር፡፡ ያን ጊዜ አንብቤው ከሁለት ዓመት በኋላም ያልረሳሁት ብቻ ሳይሆን በቃሌ የያዝኩት አንድ የደምሰው ግጥም አለ፡፡ “የደሀ እናት ተስፋ” ይላል ርዕሱ፡፡ የደሀ እናት ተስፋዋ ለሚካኤል፣ ለማርያም መሳል አሊያም ፈጣሪዋን በፀሎት መለመን እንደሚሆን ነው  የምንገምተው። የደምሰው መርሻ ግጥም ላይ ያለችው እናት ግን አንድን ትንቢት ተከትላ ነው ተስፋ ያደረገችው፡፡
ካንዲት ደሀ እናት
ይወለዳል ንጉሥ
ይወለዳል ጀግና
መባሉን ሰምቼ
አምና ጀግና ወለድኩ
ርሀብ እየላሰኝ
ችግር ላይ ተኝቼ፡፡
እነሆ ዘንድሮም አረገዝኩ
ያለመጠራጠር ንጉሥ እንደሚሆን
በእምነቴ ፀንቼ፡፡
ይህን ግጥም ከሰማሁ በኋላ ልቤን ስለሰረሰረው ሒሳዊ ንባብ ጽፌበት ነበር፤ ዛሬ በሚመረቀው ሲዲ ውስጥም ታትሟል፡፡ ግጥም ሲነበብና ግጥም ሲደመጥ ልዩነት አለው፡፡ ሙዚቃ ያጀበው ግጥም ሌጣውን ሲቀርብ ግጥም ሆኖ ከተነበበ ጠንካራ ነው። ግጥሙ ያለሙዚቃ ሲነበብ ከፈዘዘ፣ ሙዚቃው ይሆናል ነፍስና ሕይወት የዘራበት፡፡ ግጥም በጃዝ ሙዚቃ ማቅረብ በአማርኛ የሥነ ግጥም ታሪክ አዲስ ነው፡፡ በዚህ መሰል መድረክ ለመሳተፍ ሰዎች ከተለያየ ጫፍ መጥተው መሰባሰባቸውም ድንቅ እርምጃ ነው፡፡
እንዲህም ሆኖ ለጥናትና ምርምር የሚጋብዙ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም፡፡ በጃዝ ሙዚቃ ታጅቦ ከሚቀርበው ግጥም የምንሰማው ሙዚቃውን ነው ወይስ ግጥሙን? ከአዳራሽ ከወጣን በኋላ አዕምሯችን ላይ የሚቀሩ ስንኞች አሉ? የግጥሙ እሳቦትስ በውስጣችን ይሰርፃል? ምንስ ትዝታ ይቀርልናል? አመጣጣችንስ ከእነ እከሌ ጋር ነበር ለማለት ነው ወይስ ግጥም አድናቂ ሆነን ነው የምንመጣው? አነጋጋሪ ጥያቄዎቹ እንዳሉ ሆነውም ግጥም በጃዝ በመጀመሩ ለአማርኛ ሥነ ግጥም ዕድገት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ለመግቢያ ያህል ይህን ካልኩ ዛሬ ወደሚመረቀው ሲዲ እንምጣ፡፡ ለግጥም ስብስቦቹ “ያልታየው ተውኔት” የሚለው የሲዲ ርዕስ የሚመጥነው አይደለም፡፡ ያንስበታል፡፡ አንድ ሰው ሲዲውን ታክሲ ውስጥ ጥሎት ቢወጣ፣ የሚያገኙት ሰዎች ርዕሱን አይተው ሊሉ የሚችሉት፤ “አዲስ የወጣ ፊልም ወይም ቴአትር” ነው፡፡
ይህ ርዕስ ለሲዲው በርዕስነት ለምን ተመረጠ ብለን ብንገምት፣ ከምናገኘው መልስ አንዱ በጃዝ በታጀበ የግጥም ንባብ መድረክ ብዙ ጭብጨባ ያገኘ ስለሆነ ይሆናል፡፡ በብዙ መድረኮች እንደሚታየው፣ በሚነበበው ግጥም ውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳይ ከተነሳ ጭብጨባው ይደምቃል፡፡ የሱቅና የቤት ኪራይ ያስጨነቀው፣ በፍርሀትና ስጋት ውስጥ ያለ፣ በመንገድ ትራንስፖርት ችግር መከራውን እየበላ ያለ ሰው ርዕሰ ጉዳያቸውን ፖለቲካ ላደረጉ ግጥሞች በጭብጨባ ድጋፍ ይሰጣል፡፡
ርዕሱ ለሲዲው ባይመጥነውም የሽፋን ስዕሉ ግን ውብ ነው፡፡ በሲዲው በስተቀኝ በኩል ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ፒጃማ ለብሰው፤ ከቤታቸው በርግገው የወጡ ዓይነት ሰው ሆነው ይታያሉ፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን “እኔ ለእኔ ኖሬ አላውቅም” የምትል ኃይለኛ ግጥም አላቸው፡፡ ስዕሏ ለተመልካች ብዙ ነገር የምታስታውስ ናት፡፡
“ያልታየው ተውኔት” ከማለት ይልቅ ለሲዲው በርዕስነት ሊመጥኑ የሚችሉና ጠንካራ መልዕክት ያላቸው የግጥም ርዕሶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ “ያሞራ አዳኝ ሚስት” የሚለው ግጥም ርዕስ እኔን ስቦኛል። ይህች ሴት የዝሆን፣ የአንበሳ፣ የጠላት አዳኝ ሚስት ብትባል የሚያኮራ ጉዳይ ነው፡፡ አሞራ ለማደን ጫካ የሚገባ ጀግና ያለ አይመስለኝም፡፡
ደምሰው መርሻ ግጥሙን በደንብ ይጽፍና ማወሳሰብና ማውጠንጠን ሲጀምር ባልታወቀ ምክንያት ይጠመዘዝና ፖለቲካ ውስጥ ይገባል፡፡ ከዚያ በኋላ ነገሩ ይፈራርሳል እንጂ እንደጀመረው ቢቀጥል የፖለቲካውን ጉዳይ አንባቢያን መጨመር ይችሉ ነበር፡፡
“ያልታየው ተውኔት” ውስጥ እነዚህ ድንቅ ስንኞች ቀርበዋል፡ -
ደንታ ቢስ አዘጋጅ ተመልካች የናቀ
ምንም አልከበደው እያለ ሲናገር
ቴአትር አለቀ፤
የዋሁ ተመልካች ለመጠየቅ ፈርቶ
ስንት ጊዜ ወጣ መጋረጃ አይቶ
ሕዝብ ያሳዝናል
ተስፋ ብቻ ሳይሆን
ወሬም ይርበዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ጥልቀት ያለው ግጥም መጨረሻው ላይ ወደ ፖለቲካው ዘው ብሎ ባይገባ ኖሮ እንደ ባለቅኔ ሥራ ዘመን የሚሻገር ሊሆን ይችል ነበር፡፡ “ያ ትውልድ” በመባል የሚታወቁት የ1960ዎቹ ገጣሚያን፣ ከዚያ ዘመን ሥራዎቻቸው ወደ ዛሬ ዘልቀው የምናስታውሳቸውና ዘመን ተሻጋሪ መሆን የቻሉት ቅኔያዊ የሆኑት የዮሐንስ አድማሱና መሰል ገጣሚያን ሥራዎች ናቸው፡፡ የጠወለጉት ግጥሞች ዘመን ያለመሻገራቸው ምክንያቱ ዘገባዊ ስለነበሩ ነው፡፡
ሆረስ የሚባል ፈላስፋ ብዙ አስተውሎ የፃፈው አንድ ነጥብ አለ፡- “ንፁሕ ውሃ ብቻ የሚጠጣ ባለቅኔ የተለየ ግጥም ሊፈጥር አይችልም፡፡ ንፁሕ ውሃ ብቻ የሚጠጡ ገጣሚያን ሥራዎች ለረዥም ጊዜ የሚመስጡ ወይም የዘመን ቃፊሩን የሚሻገሩ አይደሉም” ይላል፡፡ የዚህ መዕልክት ዋነኛ አንደምታ፤ ባለቅኔ ወይም ገጣሚ ተራ ሕይወት መኖር የለበትም፤ተገልሎ ሊኖርም አይገባም፡፡ ጉራንጉሩን፣ የውስጥ ሕይወትን፣ የሰውን ልብ ትርታ ተከትሎ ካልፃፈ በስተቀር ባለቅኔ አይሆንም የሚል ይመስለኛል፡፡ የ4 ትውልዶች ታሪክ የተቀበረበት መንደር በሆነው በካዛንችስ የተወለደው ደምሰው መርሻ፤ ከ18 የሲዲ ግጥሞቹ ሁለቱ ብቻ ናቸው በወንድና በሴት ፍቅር ዙሪያ ያጠነጠኑት፡፡ ይህ ብዙ ጥያቄን ሊያስነሳ የሚችል ነው፡፡
የካዛንችስ ልጅ ሆኖ ሕይወቱ ከፍቅር ይልቅ በፖለቲካው ለመነካት እንዴት ቻለ? በፍልስፍናና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቁምታዎች ላይ ትኩረቱን ያበዛበት ምክንያት ምንድነው? ሳያፈቅር፣ በሴት ሳይፈቀር፣ በፍቅር ሳይንገላታ አልፏል ወይ? ያሰኛል። ከፍቅር ነክ ግጥሙ አንዱ “ናፍቆት” የሚል ርዕስ አለው፡፡ በጣም የሚገርመው ግን በዚህም ግጥሙ፣ ፍቅረኛው ስለናፈቀችውና ስለወደዳት እንድትመጣ አይፈልግም፡፡
ብጓጓ ነው የኔ ዓለም
ዓይንሽ ቢርበኝ ነው ሕመሜ
አቅም ማጣቴ እሱ ነው
ናፍቆት ነው የጣለኝ ውዴ
የሞቱ ነፍሳት
በምን እንደሞትኩ ሲያስጠይቁኝ
አፌን ሞልቼ የምናገረው
የድፍረቴ ቃሌ
እንዳይበላሽ ናፍቆት ነው እንድል
አትምጪ የኔ ዓለም አልይሽ ፍቅሬ።
ይህንን ግጥም አድምጠን ስለ ፍቅር ገጠመ ልንል አንችልም፡፡ ነፍሱን ይማረውና የደበበ ሰይፉ ግጥም ትዝ ይለኛል፡፡ “ተይው እንተወው” የሚል ርዕስ ያለው ግጥም ጽፎ ነበር፡፡ ግጥም የፃፈላት ሴትና እሱም ኃይለኛ ፍቅር ላይ ወድቀው ፍቅራቸውን ለአጭር ጊዜ ካጣጣሙ በኋላ በሆነ ፖለቲካዊ ወይም ማሕበራዊ ጉዳይ አብረው መዝለቅ ባለመቻላቸው ነበር ግጥሙን የፃፈው፡፡
የዘመን ቃፊሩን ማለፍ አልቻልና
የዓለም ጥበቱ አልመጠነና
ተይው እንተወው
ውጥኑ ግብ ይሁን ጅማሬው ፍፃሜ
ቅጽበቷ ሙሉ ዕድሜሽ ወቅቷ ዘላለሜ፡፡
ደምሰው መርሻ በአብዛኛው ኮስተር ያሉ ጉዳዮች ላይ ነው የፃፈው፡፡ 6 ያህል ግጥሞቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቁምታዎች የወጡ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል፡- “ደመራና መስቀል”፣ “የጠንቋይ ቤት እውቀት”፣ “ፈጣሪና ፍጡር”፣ “መምህር ሆይ ስማኝ”፣ “ቃየልና ኦሪት”፣ “የክርስቶስ ሐሙስ” ተጠቃሽ ናቸው። ደምሰው መጽሐፍ ቅዱስን በጥሞና ያነበበ ሰው ነው፡፡ ይህንን ያደረገው ዲያቆን ለመሆን ወይም የቤተክርስቲያን ሹመት ለማግኘት አይደለም። እኛ የምናውቀው ደመራና እሱ የገጠመው ደመራ ይለያያል፡፡ ብዙዎቻችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስለምናውቅ የግጥሞቹ መልዕክት በቀላሉ ይገባናል እንጂ የአዕምሯችንን ስፋት ሊያበለጽገው አይችልም።
ደምሰው መርሻ ዘመናዊ ፍልስፍና፣ ኤግዚስተንሻሊዝም፣ አብሰርዲቲ ወይም የሊቃውንት ታሪክ -- ቢቀር ቢቀር ደግሞ የአማርኛ ልቦለዶችን ቢያነብ አዳም ረታ በ “መረቅ” ልቦለድ መጽሐፉ ሰብለወንጌል መሸሻን ሕይወት ዘርቶባት፣ ትዳር መሥርታ፣ ልጅ ወልዳ እንዳሳየን፣ ድልና ጀግንነትን ይተርክልን ነበር፡፡ ራስን በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ብቻ መቀንበብ ከዘመኑ ጋር ሊያስኬድ አይችልም። ወጣት ገጣሚያን የንባብ አድማሳቸውን አስፍተው ሳይኮሎጂ፣ ሶሲዮሎጂ…በስፋት ማንበብ ይኖርባቸዋል፡፡
የደምስ ግጥሞች ለጭቁኖች የሚያደሉት፤ ገጣሚው ለተጐሳቆሉ ልቡን ስለሰጠ፣ የካዛንችስ የጓዳ ገመና ልቡን ስለላጠው ሊሆን ይችላል፤ ጨለምተኞች ናቸው፡፡ መሸነፍ በውስጣቸው አለ፡፡ ብሶት ቢኖር፣ በደል ቢኖር፣ ሰው ያምፃል፡፡ መሣሪያ ያነግባል፡፡ ብዕሩን ይስላል፡፡ እንጂ እጆቹን ብቻ አጣምሮ መቀመጥ ይከብዳል፡፡
ማርክስ ትራንድ የሚባል ታዋቂ አሜሪካዊ ገጣሚ ስለ ሀዘን የፃፉ ሰዎች በዙበትና፤ “የስቃይ አረቄ በግጥም ሲወጣ፣ ብሶትም ዳግም አረቄ ሲሆን፣ በመጨረሻ ስቃዩ ሲያበቃ ደስታ ይሆናል” ብሏል፡፡ ወጣቶች እየተነሱ ስለ ሰቆቃ ብቻ የሚጽፉ ከሆነ፣ ማነው ስለ ደስታ መፃፍ ያለበት? በደሃው ቤት፣ የኩራዝ ጭላንጭል በሚታይበት ቤት--- ደስታ አለ፡፡ መፍካት አለ፡፡ ሽሮ እየበላ፣ ቆሎ እየቆረጠመ፣ ወዝና ደም ግባት ያለው ትውልድ አለ፡፡ ይህ እውነትና ተስፋ ሊጋረድብን አይገባም፡፡ ስለ ስቃይ ብቻ በምንገጥምበት ወቅት የስቃይ ሱስ የያዘን ይመስላል። ይህ ካልሆነ ሁሉንም ነገር በሚዛናዊነትና በእኩል ሁኔታ ማቅረብ ተገቢ ይሆናል፡፡
ለማጠቃለል እናቶቻችን ሽንኩርት ሲከትፉ የላይና የታቹን እየቆረጡ በመጣል መሐሉን እንደሚጠቀሙበት ሁሉ የደምሰው መርሻ ግጥሞችም ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውንና መሰል አላስፈላጊ ጉዳዮችን እየጣልን ካነበብናቸው (ካደመጥናቸው)፣ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች እንዳሉት እንረዳለን፡፡

Read 2771 times