Saturday, 27 June 2015 09:30

እድሳት እና ውሃ ልኮች

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

“Poor people were bad to each other, too – really bad to each other. My mother always says, if you are ugly the worst place to be ugly is around poor people. And what she means is that the people at the bottom always internalize the economy and are more deranged. We are likely to torture an ugly person than the people who taught us that we are ugly.”
Junot DIAZ


“አንድ ሰው የሰራው ቤት ያረጀ እንደሆነ ከመንገር ይልቅ ከጐኑ አዲስ ቤት ሰርተህ በማሳየት እንከኑን መግለፅ የተሻለ ነው” የሚል የአተያይ መንገድ አለ፡፡
እንግዲህ አሮጌው የሰውየው እውነተኛ ገፅታ ነው፡፡ ስለ አሮጌነቱ ወይንም አዲስነቱ ሰውየው የሚያውቅበት ማነፃፀሪያ አልነበረውም፡፡ ማነፃፀሪያ እንደማይፈልጉም አያውቅም ነበር፡፡ በቃ እራሱን መስሎ እና ሆኖ ህይወቱን እየገፋ ቆይቷል፡፡
ከዚህ በራሱ ማንነት ውስጥ ቅናት እና መንጠራራት ያልነበረው ሰው ጎን ሌላ ሰው መጥቶ … አዲስ ወይንም የተሻለ የተባለውን ቤት ቀለሰ፡፡
በመቀለሱ በአንድ ጊዜ ሁለት መለኪያዎችን ነው ያፀናው፡፡ አንደኛው መለኪያ “ውበት” ነው። ያለ ተቃርኖ ይኖር የነበረው የቀድሞው ሰው ቤት ጎን ውበትን ወይንም አዲስነትን የሰራው ሁለተኛው ሰው ውበትን ብቻ አይደለም የፈጠረው፡፡ በዚያው ቅፅበት አስቀያሚነትንም ፈጥሯል፡፡ አዲሱ ቤት ውበት እና አዲስነትን ይዞ ሲወለድ የቀድሞው ቤት አሮጌ እና አስቀያሚ መሆኑን መስክሯል፡፡
ከአሮጌው ቤት ጎን የተሰራው ቤት ይዞ የመጣውን ማንኛውንም እሴት ቀድሞ ቆሞ በቆየው ቤት ላይ እንዳልነበረ መስክሮበታል፡፡ በዚያ ቅፅበት የድሮው ቤት አሮጌ መሆኑ በአዲሱ ቤት ነፀብራቅ ውስጥ ይታያል፡፡ በመታየቱ ግጭት እና ተቃርኖ በቀድሞው አንድነት ፈንታ ይተካል፡፡ ይህ ተቃርኖን “abstraction” ብለው ምዕራባውያኑ ይጠሩታል። ምስራቃዊያኑ ደግሞ “መቼም መልሶ የማይገጥም የልዩነቶች መፈልፈያ የፓንዶራ ሳጥን ተከፍቶ ሰዎች ዝንተ አለም ወደ ማይስማሙበት መቀመቅ ከቷል” ይሉታል፡፡
አዲሱን ቤት የሰራው ሰው የውበትን እና የአስቀያሚነትን እውቀትም የሚያሳይ መስታወት ሰርቷል፡፡ በተራማጅ እና ኋላ ቀርነት መሀል ያለውን ክፍተት ፈጥሯል፡፡ የጥንቱ በአሮጌነቱ እንዲሸማቀቅ አዲሱ በጥንቱ ላይ እንዲሳለቅ ማድረጊያውን መስታወት ፈልስፏል፡፡
“መፍጠር መለየት ነው” የሚሉት እንዳሉ ሁሉ “መለየት መቃረን ነው” የሚሉም የዛኑ ያህል ማስረጃ አላቸው፡፡
እንግዲህ እነዚህ ሁለት አዋቂዎች አለምን ፈጥረዋታል፡፡ ወይንም አጥፍተዋታል፡፡ የውበትን ትርጉም በአዲሱ ቤቱ ላይ አስፍኛለሁ ብሎ የሰበከው ሰው ስብከቱ ተቀባይነት እስካገኘ ድረስ ብቻ የአሮጌውን ቤት አስቀያሚነት መመስከር ይችላል። ይህ ካልሆነ ግን፤ አዲሱም የተሻለ አይደለም .. አሮጌውም የባሰ  አይሆንም፡፡ አዲስ እና አሮጌ የሚፈጠሩት አዲስነት ከአሮጌነት የበለጠ ስለሆኑ የሚታወቅ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
ማነፃፀሪያ ከሌለ ልዩነት የለም፡፡ የአውሮፓ ፍልስፍና ከምስራቅ ፍልስፍና ጎን ህንፃውን ገንብቶ አዲስ እና የተሻለ ስለመሆኑ (በጉልበቱ) ባያሳምን ሁለተኛም ሆነ ሶስተኛ አለም የሚባሉ የአስቀያሚነት ማረጋገጫዎች ባልተፈጠሩ ነበር፡፡
በዚህ የእይታ መነፅር ከተመለከትን አሪስጣጣሊስ አለም፣ (የምእራባውያን እውቀት) ውበት ከአፍሪካውያን በልጦ የኖረበት ምክኒያት ለመረዳት አያስቸግረንም፡፡
በልጦ መኖር ማለት አዲስነቱን፣ ውበትነቱን፣ እውነትነቱን በአሮጌዎቹ ጎን ሰርቶ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ “ውበት ነኝ፤ እውነት ነኝ፤ እውቀት ነኝ” በማለት ብልጫውን ካፀናው ጎን የእሱ ተቃራኒ ይኖራል፡፡ አሮጌዎቹ፣ ኋላቀሮቹ አስቀያሚዎቹ፣ ደንቆሮዎቹ… ወዘተ፡፡
ከምዕራብ ጎን ምስራቅ አለ፡፡ ከአውሮፓ ጎን አፍሪካ፣ ከአሜሪካ ጎን ህንዶች …. ወዘተ፡፡ ውበትነቱን የሚያረጋግጠው ከአስቀያሚ ጎን በመቆም ነው፡፡ እውነትነቱን ያረጋገጠው በጉልበት ነው፤ አሮጌው ፅንሰ ሀሳብ ጎን አዲስ ፅንሰ ሃሳብ ገንብቶ አሮጌውን በማድከም፡፡ የደከመ ሁሉ አስቀያሚ ነው፡፡ የደከመ ሁሉ ኋላ ቀር ነው፡፡ ያዳከመ ሁሉ ደግሞ፣ አዲስ እና የተሻለ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይችላል። ስለዚህ የውበት ፅንስ ሲፈጠር በዚያው ቅፅበት የአስቀያሚነት ፅንሰ ሀሳብም ውሃ ልኩ ተቀምጧል፡፡
መስታወት የሚያሳየው (የሚያንፀባርቀው) ነገር ምንድነው? ካላችሁኝ፤ መልሴ ፅንሰ ሀሳብን ነው የሚል ይሆናል፡፡ ክርስቶስ ድህነትን በሰበከበት ዘመን ሀያል የነበሩት ሌሎች ናቸው፡፡ የእነ አሪስጣጣል ልጆች ያኔ መስታወቱን በአሪስጣጣሊስ ፊት ብትደቅኑት የእሱን መልክ የስልጣኔ፣ የአይሁዶቹን መልክ የወመኔ አድርጎ ይተረጉምላችሁ ነበር፡፡ እውነታው ሳይቀር ፅንሰ ሀሳቦች ተቀየሩ፡፡
የአሪስጣጣሊስ ወንበር ወድቆ የክርስቲያኖቹ ወንበር ተቃና፡፡ ውበትም በቀድሞው የሰውነት መስታወት ፊት ነፀብራቋ ተቀየረ፡፡ ድህነት ውበት እና እውነት ሆነ፤ ምክኒያታዊነት ደግሞ አሮጌው ቤት ሆነ፡፡ ሁለቱ ቤቶች ሁሌም ጎን ለጎን የቆሙ ናቸው። ዝንተ አለም አይነጣጠሉም፡፡ አንዱ ሌላውን ያስቀይማል፡፡ አንዱ በሌላው ድካም ተጠቅሞ ሀይሉን ያቋቁምበታል፡፡ ስለዚህ አፍሪካውያን ውብ መሆን የጀመሩለት እነማን በማስቀየማቸው ምክኒያት እንደሆነ ግልፅ ይሁንላችሁ፡፡ የሙስሊሞች መነቃቃት በነማን ማንቀላፋት እንደወጣ አይጥፋችሁ፡፡
አስቀያሚነታቸውን ማን ሰጥቶአቸው በልዋጭ የራሱን ውበት እንደፈለሰፈ እስኪገባቸው አስቀያሚዎች ስለራሳቸው አያውቁም፡፡ ይጨካከናሉ .. ውበታቸውን ያሸጣቸውን ለመምሰል ይጥራሉ። የንግስና ዘመኑ እስኪያበቃ፣ ለአስቀያሚዎቹም የውድቀት ጉድጓዳቸው የመውደቂያ ወለል ላይ አይደርሱም፡፡ አንዱ መውጣት መውጣት ብቻ … ሌላው መውደቅ መውደቅ ብቻ፡፡ … ይህ የውድቀት እና የኃያልነት ተቃራኒ ስፍራቸው ዘላለማዊ እስኪመስል ድረስ ለሺ አመታት ሊቀጥል ይችላል፡፡ ግን በስተመጨረሻ መቀየሪያው ይደርሳል፡፡
ቅድም መፃፍ ስጀምር … አዲስ ቤት ከአሮጌው ቤት ጎን ስለሰራው ሰው ያወራሁላችሁ ለመረዳት እንዲቀላችሁ ብዬ ነው፡፡ በመሰረቱ አዲስም አሮጌም ቤት የለም፡፡ ሁለቱም ቤቶች ከጥንት ጀምሮ ያሉ ናቸው፡፡ አዲስ ቤት የሰራ የመሰለንም ሰው ቤቱን አዲስ አስመስሎ ስላደሰው እንጂ በመሰረቱ አዲስ ነገር “ከሰማይ በታች የለም”። አንደኛው አዲስ አስመስሎ የቀድሞውን ቤት በአዲስ የፅንሰ ሀሳብ ይዘት ሳይሆን ቅርፅ ሲያድሰው … በተቃራኒው ያለው ቤት ባለመታደሱ አሮጌ መስሎ መቅረቱ … የእውነት እና ውሸትን ያህል ልዩነት ያላቸው አስመስሎ አለያያቸው እንጂ በመሰረቱ አንድ ናቸው፡፡
አስቀያሚ ያስመስላቸውም ሆነ ውብ ያደረጋቸው የሀሊዮት መስታወት እንጂ ጉልበታቸው እና ባለጊዜነታቸው የሚለዋወጥ ነው፡፡ ፀንቶ የሚኖር ማንነታቸው፣ ልዩነታቸውን ወደ አንድነት አይቀይርላቸውም፡፡ ከሁለቱ ቤቶች በላይ የሆነ ሦስተኛ እና ሁለቱን አንድ የሚያደርጋቸው ቤትም መቼም አይቀልሱም፡፡

Read 1357 times